ወላይታ ድቻ ከመመራት ተነስቶ በሁለቱም አጋማሾች የመጨረሻ ደቂቃዎች ባስቆጠራቸው ግቦች ወልዋሎ ዓ/ዩን 2ለ1 በመርታት በውድድር ዓመቱ የመጀመሪያ ድሉን አሳክቷል።

በዋና ዳኛ ሀብታሙ መንግሥቴ መሪነት 9፡00 ሲል በአ/አ ስታዲየም በተካሄደው ጨዋታ በመጀመሪያው አጋማሽ ተመጣጣኝ ፉክክር የተደረገበት ነበር። የመጀመሪያዎቹ ዒላማቸውን የጠበቁ ሙከራዎች በወላይታ ድቻ አማካኝነት የተደረጉ ሲሆን 20ኛው ደቂቃ ላይ ያሬድ ዳርዛ በሳጥኑ የግራ ክፍል ይዞ ገብቶ በግራ እግሩ ያደረገውን ሙከራ እና 23ኛው ደቂቃ ላይ መሳይ ሰለሞን ከሳጥን ውጪ ያደረገውን ሙከራ በተመሳሳይ ግብ ጠባቂው ሙታክብዋ ጆኤል መልሷቸዋል።
በኳስ ቁጥጥሩ ብልጫ ለመውሰድ በጥሩ ፉክክሮች ታጅቦ ነገር ግን ጠንካራ የግብ ዕድሎች ሳይፈጠሩበት ጨዋታው ቢቀጥልም 40ኛው ደቂቃ ላይ የመጀመሪያው ለጎል የቀረበ ሙከራ በወልዋሎ አማካኝነት ተደርጓል። ኪሩቤል ወንድሙ ከቅጣት ምት ያደረገውን ግሩም ሙከራ ቢኒያም ገነቱ አስወጥቶበታል። ያንኑ ኳስ ከማዕዘን ተሻምቶ ጌትነት ተስፋዬ በግንባር ገጭቶ ያደረገው ሙከራ ዒላማውን ሳይጠብቅ ቀርቷል።

ጨዋታው 45ኛ ደቂቃ ላይ ሲደርስ ቢጫዎቹ የመጀመሪያ ጎል አስቆጥረዋል። ከርቀት የተላከውን ኳስ ሀፊዝ ኮንኮኒ በግንባሩ ከገጨው በኋላ ያገኘው ያሬድ መኮንን ከሳጥን ጠርዝ ላይ በመምታት በጥሩ አጨራረስ ኳሱን መረቡ ላይ አሳርፎታል።
የመጀመሪያው አጋማሽ ሊጠናቀቅ የተጨመሩ 3 ደቂቃዎች አልቀው 45+4′ ላይ የጦና ንቦቹ የአቻነት ግብ አስቆጥረዋል። ከቅጣት ምት የተሻገረውን ኳስ ወልዋሎዎች በትክክል ሳያርቁት ቀርተው ከሳጥን አጠገብ ያገኘው ውብሸት ክፍሌ በድንቅ ሁኔታ በመምታት ግብ አስቆጥሯል።

ከዕረፍት መልስ ጨዋታው እጅግ ተቀዛቅዞ ሲቀጥል ዘለግ ላሉ ደቂቃዎች አንድም የጎል ዕድል ሳይፈጠር ከዘለቀ በኋላ 82ኛው ደቂቃ ላይ የወልዋሎው ፍቃዱ መኮንን ፈታኝ ባይሆንም ዒላማውን የጠበቀ ሙከራ ማድረግ ሲችል በሴኮንዶች ልዩነት ደግሞ ወላይታ ድቻዎች በአጋማሹ የመጀመሪያውን ለግብ የቀረበ ሙከራ አድርገዋል። መሳይ ሰለሞን ከግራ መስመር ያሻገረውን ኳስ ያገኘው ተቀይሮ የገባው ኢዮብ ተስፋዬ በግንባሩ ገጭቶ ያደረገው ሙከራ በግቡ አግዳሚ በኩል ለጥቂት ወጥቶበታል።

87ኛው ደቂቃ ላይ የወልዋሎው ኮንኮኒ ሀፊዝ እጅግ ያለቀለትን የግብ ዕድል ዒላማውን ባልጠበቀ ደካማ ሙከራ ካባከነ በኋላ 89ኛው ደቂቃ ላይ ወላይታ ድቻዎች የማሸነፊያ ጎል አስቆጠረዋል። ኪዳኔ አሰፋ ከረጅም ርቀት ያደረገውን ድንቅ ሙከራ ግብ ጠባቂው ሙታክብዋ ጆኤል ሲመልስበት ያንኑ ኳስ ያገኘው ከሁለት ደቂቃዎች በፊት ተቀይሮ የገባው ቅዱስ ቂርቆስ ኳሱን መረቡ ላይ አሳርፎታል። ጨዋታውም በወላይታ ድቻ 2ለ1 አሸናፊነት ሲጠናቀቅ ድሉም ለጦና ንቦቹ በውድድር ዓመቱ የተመዘገበ የመጀመሪያ ድል ሆኖ ተመዝግቧል።

