ሪፖርት | አዳማ ከተማ እና ነጌሌ አርሲ ድል ተቀዳጅተዋል

ሪፖርት | አዳማ ከተማ እና ነጌሌ አርሲ ድል ተቀዳጅተዋል

በሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ስታዲየም በተካሄዱ ጨዋታዎች አዳማ ከተማ ባህር ዳር ከተማን ፤ ነጌሌ አርሲ ደግሞ ኢትዮጵያ መድንን በተመሳሳይ 1ለ0 ውጤት አሸንፈዋል።

አዳማ ከተማ ከ ባህር ዳር ከተማ

የሰባተኛ ሳምንት የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ጨዋታዎች ዛሬ ሲጀምሩ 9:00 ሲል በሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ስታዲየም አዳማ ከተማን ከ ባህር ዳር ከተማ አገናኝቷል። ባሳለፍነው የጨዋታ ሳምንት ኢትዮ ኤሌክትሪክን በማሸነፍ ወደ ድል የተመለሱት የጣና ሞገዶች እንዲሁም በነገሌ አርሲ አስከፊ ሽንፈት ያስተናገዱትን አዳማ ከተማዎች ያገናኘው እና በኢንተርናሽናል ዋና ዳኛ ማኑሄ ወልደጻድቅ እየተመራ የተደረገው የዕለቱ ጨዋታ በኳስ ቁጥጥሩ ተመጣጣኝ የሚባል እንቅስቃሴን ያስመለከቱን ሲሆን በግብ ሙከራ ረገድ በአዳማ ከተማ በኩል አህመድ ሁሴን ካደረጋቸው እና ዒላማቸውን መጠበቅ ካልቻሉት ሁለት የሳጥን ውጭ ሙከራዎች በስተቀር ይሄ ነው የሚባል የግብ ሙከራን ሳያስመለክቱን የመጀመሪያው አጋማሽ ተጠናቋል።

ከዕረፍት መልስ ወደ ሜዳ እንደተመለሱ የባህር ዳር ከተማው ወንድወሰን በለጠ ከመስመር ከሄኖክ ይበልጣል የተቀበለውን ኳስ ወደ ግብ ሞክሮ የግቡን ቋሚ ገጭቶ የተመለሰበት ኳስ ለጣና ሞገዶች አስቆጪ የግብ ሙከራ ነበር። ቀስ በቀስ ወደ ጨዋታ የተመለሱት አዳማ ከተማዎች 75ኛው ደቃቃ ላይ መነሻውን ከማዕዘን ምት አድርጎ ዳዋ ሆቴሳ በቄንጥ ያቀበለውን ኳስ አቡበከር ሳኒ ወደ ግብነት መቀየር ችሏል። ጨዋታው ሊጠናቀቅ በተሰጡት ጭማሪ ደቂቃዎች የአዳማው ተጫዋች የሆነው ቢንያም ዐይተን ተጫዋቾችን ቀንሶ ወደ ሳጥን በመግባት የሞከረው ኳስ የግቡን አግዳሚ ገጭቶ የተመለሰ ሲሆን ከግቡ መቆጠር በኋላ ባህር ዳሮች ወደ ጨዋታ ለመመለስ ጥረት ቢያደርጉም ከአማኑኤል ገ/ሚካኤል ደካማ ሙከራ በስተቀር ግብ ማስቆጠር ተስኗቸው ጨዋታው በአዳማ ከተማ 1-0 አሸናፊነት ተጠናቋል።

ኢትዮጵያ መድን ከ ነጌሌ አርሲ

12፡00 ሲል በዋና ዳኛ በሪሶ በላንጎ መሪነት በሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ በተካሄደው ጨዋታ በመጀመሪያው አጋማሽ ኢትዮጵያ መድኖች በኳስ ቁጥጥሩ ብልጫ በመውሰድ ለመጫወት ቢሞክሩም በማጥቃት እንቅስቃሴው በኩል ግን ነጌሌዎች ከፍተኛ ብልጫ መውሰድ ችለዋል። ሆኖም ግን ሰጎኖቹ  በርካታ ሙከራዎችን ቢያደርጉም ዒላማውን የጠበቀ ሙከራ ለማድረግ ግን ሲቸገሩ ተስተውሏል።

ከዕረፍት መልስ ጨዋታው ሳቢ በሆነ ፉክክር በተመሳሳይ ሂደት ቀጥሎ ነጌሌዎች 61ኛው ደቂቃ ላይ ጨዋታውን መምራት ጀምረዋል። ግብ ጠባቂው ኢድሪሱ አብዱላሂ ከራሱ ሳጥን በረጅሙ ያሻማውን ኳስ በመድን ተከላካይ እንዲሁም በቡድን አጋሮቹ ተጨራርፎ ያገኘው ተቀይሮ የገባው ምስጋናው መላኩ ኳሱን መረቡ ላይ አሳርፎታል። ግብ ከተቆጠረባቸው በኋላ መልስ ለመስጠት ጥረት ያደረጉት መድኖች ንጹህ የግብ ዕድል ለመፍጠር ሲቸገሩ ሰጎኖቹ ግን 83ኛው ደቂቃ ላይ ተጨማሪ ግብ ለማስቆጠር እጅግ ተቃርበው ነበር። ከቤ ብዙነህ ወደ ግራ ካደላ ቦታ ላይ ከሳጥን ውጪ ያደረገውን ድንቅ ሙከራ ግብ ጠባቂው ፋሲል ገብረሚካኤል በድንቅ ቅልጥፍና አስወጥቶበታል። መድኖች ከጨዋታው አንድ ነጥብ ሊያገኙ የሚችሉበትን አጋጣሚ 90+5ኛው ደቂቃ ላይ አግኝተው ብሩክ ሙሉጌታ ከቀኝ መስመር የተሻገረለትን ኳስ በግንባሩ ገጭቶት የግቡ አግዳሚ መልሶበታል። ጨዋታውም የውጤት ለውጥ ሳይደረግበት በነጌሌ አርሲ 1ለ0 አሸናፊነት ተጠናቋል።