ሪፖርት | ምድረገነት ሽረ እና ሲዳማ ቡና ድል አደረጉ

ሪፖርት | ምድረገነት ሽረ እና ሲዳማ ቡና ድል አደረጉ

መስመሩን ያለፈ ግብ የተሻረበት እንዲሁም ሁለት ጊዜ የጨዋታ መጠናቀቂያ ፊሽካ በተነፋበት አወዛገቢ የሲቢኢ ፕሪምየር ሊግ ምድብ አንድ ጨዋታዎች ምድረ ገነት ሽረ እና ሲዳማ ቡና ሁለተኛ ተከታታይ ድላቸውን አስመዘገቡ።

ምድረገነት ሽረ ከ ሀዋሳ ከተማ

ጥሩ ፉክክር እንዲሁም ተመጣጣኝ የኳስ ቁጥጥር ድርሻ በታየበት የመጀመርያው አጋማሽ ወደ ተጋጣሚ የግብ ክልል በመድረስም ሆነ ሙከራዎች በማድረግ የምድረ ገነት ሽረ ብልጫ የታየበት ነበር።

በአጋማሹ በሐይቆቹ በኩል ያሬድ ብሩክ ከግራ መስመር ተሻምታ ጌታነህ ከበደ ያመቻቻትን ኳስ ተጠቅሞ ያደረጋት ሙከራ እንዲሁም አብነት ደምሴ ከመዓዝን የተሻማችውን ኳስ ተጠቅሞ በግንባር ያደረጋት ዒላማዋን ያልጠበቀች ሙከራ ሲጠቀሱ ተካልኝ ደጀኔ ከግራ መስመር አሻምቷት ሳጥን ውስጥ የነበረው ሽመክት ጉግሳ ያደረጋት ለግብ የቀረበች ሙከራ እና ዳንኤል ዳርጌ ከሽመክት ጉግሳ የተቀበለውን ኳስ ወደ ሳጥኑ የቀኝ ክፍል ገፍቶ በመምታት የግቡን አግዳሚ የመለሰበት እጅግ ለግብ የቀረበ ሙከራ ደግሞ ምድረ ገነት ሽረ በኩል የተደረጉ ሙከራዎች ናቸው። በ34 ኛው ደቂቃም የተሻለ ብልጫ የነበራቸው ምድረ ገነት ሽረዎች በአቤል ማሙሽ አማካኝነት ባስቆጠሯት ግብ ጨዋታውን መምራት ጀምረዋል፤ ተካልኝ ደጀኔ ከግራ መስመር ካሻማት በኋላ ከሰይድ ሀብታሙ እጅ የሾለከችውን ኳስ ተጠቅሞ አጥቂው ያስቆጠራት ግብም ቡድኑን መሪ ማድረች ችላለች።

በሁሉም መለኪያዎች ቀዝቃዛ የነበረው ሁለተኛው አጋማሽ ሽረ ምድረ ገነቶች ወደ ግብ ክልላቸው ተጠግተው ለመከላከል፤ ሐይቆቹ ደግሞ በተሻለ የኳስ ቁጥጥር ለማጥቃት ጥረት ያደረጉበት ቢሆንም ፈቃደ ስላሴ ደሳለኝ ከርቀት ካደረጋት ሙከራ ውጭ ይህ ነው የሚባል ሙከራ አልተደረገበትም። መደበኛ ክፍለ ጊዜ አልቆ በተጨመሩ ደቂቃዎችም ትልቅ ትኩረት የሳበ ኩነት ተፈጥሯል፤ ዋና ዳኛው አሸብር ሰቦቃ የተጨመሩ አራት ደቂቃዎች ሳይጠናቀቁ ጨዋታው መጠናቀቁን በፊሽካቸው ከገለጹ በኋላ በረዳቶቻቸው ጥቆማ ጨዋታው ዳግም የጀመረበት ኩነትም የብዙዎች ትኩረት የሳበ ነበር።

ሲዳማ ቡና ከ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ

በፈጣን ሽግግሮች ታጅቦ በተካሄደው የዕለቱ ሁለተኛ ጨዋታ በመጀመርያው አጋማሽ የሲዳማ ቡናዎች ብልጫ የታየበት ሲሆን ቡድኑ ቀዳሚ ለመሆን የፈጀበት ደቂቃም 4 ብቻ ነበር፤ ሬድዋን ናስር ከመስመር አሻምቷት ብርሀኑ በቀለ በግንባር ያስቆጠራት ግብም ሲዳማ ቡናዎችን መሪ ያደረገች ግብ ነበረች። ከግቧ መቆጠር በኋላም ጫና ፈጥረው መጫወት የቻሉት ሲዳማ ቡናዎች በርከት ያሉ ሙከራዎች ማድረግ ሲችሉ ብሌስ ናጎ በግምባር ያደረጋት ሙከራ እንዲሁም ፍቅረየሱስ ተወልደብርሀን ከቆመ ኳስ ተሻግራ የንግድ ባንክ ተጫዋቾች በአግባቡ ያላራቋትን ኳስ ተጠቅሞ ያደረጋት እጅግ ለግብ የቀረበች ሙከራ ይጠቀሳሉ። ሀምራዊ ለባሾቹ በአጋማሹ ምንም ዓይነት የግብ ሙከራ ማድረግ አልቻሉም።

ከመጀመርያው አጋማሽ የተለየ የፉክክር ደረጃ የታየበት ሁለተኛው የጨዋታ ምዕራፍ ሁለት ተጫዋቾች ቀይረው በማስገባት አጋማሹን የጀመሩት ንግድ ባንኮች ጫና የፈጠሩበት ነበር። አዲስ ግደይ ተቀይሮ ከገባው ናትናኤል ዳንኤል የተሻገረችለትን ኳስ ወደ ሳጥን ይዞ በመግባት መቷት አግዳሚውን ገጭታ የተመለሰች ኳስ እንዲሁም ናትናኤል ዳንኤል ከቆመ ኳስ የተሻገረችውን ኳስ ተጠቅሞ በግንባር ያደረጋት ሙከራም ቡድኑን አቻ ለማድረግ የተቃረቡ ሙከራዎች ናቸው።

በአጋማሹ መጠነኛ መቀዛቀዝ በታየባቸው ሲዳማ ቡናዎች በኩልም መስፍን ታፈሰ እና ብለስ ናጎ ከርቀት ያደረጓቸው ሙከራዎች ይጠቀሳሉ። ብዙ ክስተቶች በተስተናገዱባቸው መገባደኛ ደቂቃዎች ሀምራዊ ለባሾቹ በናትናኤል ዳንኤል አማካኝነት አስቆጪ ሙከራ ካደረጉ በኋላ ግብ ማስቆጠር ቢችሉም አዲስ ግደይ አሻምቷት ሳይመን ፒተር በግንባሩ ያስቆጠራት መስመሩን ያለፈች ግብ በመሃል ዳኛው ዳንኤል ይታገሱ ተሽራለች። ጨዋታውም በሲዳማ ቡና አሸናፊነት ተጠናቋል።