ቅድመ ጨዋታ መረጃዎች | የ9ኛ ሳምንት የመጀመሪያ ቀን ጨዋታዎች

ቅድመ ጨዋታ መረጃዎች | የ9ኛ ሳምንት የመጀመሪያ ቀን ጨዋታዎች

በ9ኛ ሳምንት የሲቢኢ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የመጀመሪያ ቀን በሁለቱም ስታዲየሞች የሚደረጉ ሁለት ጨዋታዎችን የተመለከቱ መረጃዎች እነሆ !

ወላይታ ድቻ ከ ምድረገነት ሽረ

በጥሩ ወቅታዊ ብቃት ላይ የሚገኙ ቡድኖች የሚያደርጉት ጨዋታ በአዲስ አበባ ስታዲየም የሚካሄድ የዕለቱ ብቸኛ ጨዋታ ነው።

አሰልጣኝ መሳይ ተፈሪን ከሾሙ በኋላ ባደረጓቸው ሁለት ጨዋታዎች ወልዋሎን አሸንፈው ከ ፋሲል ከነማ ጋር አቻ የተለያዩት ድቻዎች ባሳዩት ትልቅ መነሳሳት ድል ተቀዳጅተው ከወራጅ ቀጠናው ራቅ ለማለት እያለሙ ወደሜዳ ይገባሉ። ምንም እንኳ ባሳለፍነው ሳምንት የገጠሙት ቡድን ገና በመጀመሪያዎቹ ደቂቃዎች ተጫዋች በቀይ ካርድ ቢያጣም የነበረው ፈታኝ አቀራረብ ከአንድ ነጥብ በላይ እንዳያገኙ ቢያደርግም በሁሉም የዘንድሮ የሊግ ጨዋታዎች ጎል ያስተናገደው የመከላከል አደረጃጀት ላይ ማስተካከያ ማድረግ የአሰልጣኝ መሳይ ተፈሪ ዋነኛ ሥራ እንደሚሆን ይጠበቃል።

እጅግ ማራኪ በሆነ እንቅስቃሴ ተከታታይ ሁለት ጨዋታዎችን ማሸነፍ የቻለው ምድረገነት ሽረ ወደ አዲስ አበባ ከመጣ በኋለ ከመቻል ጋር አቻ ሲለያይ ድሬዳዋ እና ሀዋሳ ከተማን በአሳማኝ ብቃት አሸንፏል። በተለይም ከባለ ልምዱ አማካይ ሽመክት ጉግሳ በሚነሱ ኳሶች በየጨዋታው በርካታ የግብ ዕድሎችን የሚፈጥረው ቡድን በአሸነፈባቸው ጨዋታዎች ጎል አለማስተናገዱ ጠንካራ ጎኑ ሲሆን አጨራረስ ላይ ግን እንደሚፈጠሩ የግብ ዕድሎች ከዚህም በላይ ጎል ማስቆጠር ይጠበቅበታል።

ምድረገነት ሽረ በዛሬው ጨዋታ አዲሱ ተስፋዬን በቅጣት ፀጋአብ ዮሐንስ እና ብሩክ ሓድሽ ደግሞ በጉዳት ምክንያት አያሰልፍም፤ ዋና አሰልጣኙ ዳንኤል ፀሐዬ ግን የሦስት ጨዋታዎች ቅጣታቸውን ጨርሰው በዛሬው ጨዋታ ቡድናቸውን ይመራሉ።

የተሰረዘውን እና በስሑል ሽረ የሁለት ለባዶ አሸናፊነት የተጠናቀቀውን የ2012 ጨዋታ ሳይጨምር 4 ጊዜ የተገናኙት ቡድኖቹ በሦስቱ ጨዋታዎች አቻ ሲለያዩ ወላይታ ድቻ 1 ጊዜ አሸንፏል።  በጨዋታዎች ወላይታ ድቻ 3 ስሑል ሽረ ደግሞ 2 ግብ አስቆጥረዋል።

ኢትዮጵያ መድን ከ ኢትዮ ኤሌክትሪክ

ከሽንፈት እና አቻ የተመልሱ ቡድኖች የሚያደርጉት ጨዋታ በሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ስታዲየም የሚካሄድ የዕለቱ ብቸኛ ጨዋታ ነው።

ከሁለት ዓመታት በኋላ በተከታታይ ሁለት ጨዋታዎች ሽንፈት ያስተናገዱት ኢትዮጵያ መድኖች ዘንድሮ በካፍ ቻምፒዮንስ ሊግ የነበራቸው ጥንካሬ በፕሪሚየር ሊጉ ፈጽሞ አብሮቸው ሊቀጥል አልቻለም። ቡድኑ ከኢንተርናሽናል ውድድሩ መልስ ሀዲያን ማሸነፍ ቢችልም ከዛ በኋላ በተደረጉ አምስት ጨዋታዎች ግን አንድ ብቻ አሸንፎ በአንዱ አቻ ተለያይቶ በሦስቱ ተሸንፏል። ከአምስቱ በአራቱ ጨዋታዎች ጎል ያላስቆጠረውን የማጥቃት ኃይል ማስተካከል ደግሞ የአሰልጣኝ ገብረመድኅን ኃይሌ ትልቁ የቤት ሥራ ነው።

በመጨረሻው ሳምንት ከአዳማ ከተማ ጋር ያለ ጎል የተለያዩት ኢትዮ ኤሌክትሪኮች ወደ ሀዋሳ ካመሩ በኋላ በሦስት ጨዋታዎች አራት ነጥቦችን ብቻ ቢሰበስቡም አዲስ አበባ ላይ የነበራቸው ጥንካሬ እና አብሯቸው የዘለቀው ማራኪ እንቅስቃሴ አሁንም ተስፋ ሰጪ ነው። ከስምንት ጨዋታዎች 15 ነጥቦች ሰብስቦ 5ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጠው ቡድኑ የዛሬውን ጨዋታ የሚያሸንፍ ከሆነ በጊዜያዊነትም ቢሆን ሁለተኛ ደረጃ ላይ መቀመጥ ይችላል።

ሁለቱ ቡድኖች 28 ጊዜ ተገናኝተው ኤሌክትሪክ 16 ጨዋታ በማሸነፍ ቀዳሚ ሲሆን ኢትዮጵያ መድን 8 ጨዋታዎችን አሸንፏል። በቀሪዎቹ 4 ጨዋታዎች ደግሞ አቻ ተለያይተዋል። ለወትሮውም በጎል የታጀበ የእርስ በርስ ግንኙነት ታሪክ ያላቸው ሁለቱ ቡድኖች ባደረጓቸው ጨዋታዎች 2 ጊዜ ብቻ ያለ ጎል ሲያጠናቅቁ ኤሌክትሪክ 42 ፣ መድን 27 ጎሎችን አስቆጥረዋል።

በኢትዮ ኤሌክትሪክ በኩል ጉዳት ላይ ከሚገኘው አብዱላሂ አላዩ ውጪ ሁሉም የቡድኑ አባላት ለጨዋታው ዝግጁ ናቸው።