የሲቢኢ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የዘጠነኛ ሳምንት ጨዋታዎች ዛሬ ሲጀመሩ በምድብ አንድ ወላይታ ድቻ እና ምድረገነት ሽረ 1-1 በሆነ አቻ ውጤት ተለያይተዋል።
የዘጠነኛ ሳምንት መክፈቻ በነበረው ጨዋታ ወላይታ ድቻዎች በይበልጥ ጫናን ፈጥረው ወደ ተጋጣሚ የግብ ክልል በተደጋጋሚ መድረስ የቻሉ ቢሆንም በአጋማሹ ግብጠባቂውን ሪችሞንድ አይ የሚፈትን የግብ ሙከራ ማድረግ ተቸግረዋል። መከላከልን ምርጫቸው ያደረጉት ምድረ ገነት ሽረዎችም በተመሳሳይ ይህ ነው የሚባል ለግብ የቀረበ የግብ ሙከራን ሳያስመለክቱን የመጀመሪያው አጋማሽ ተጠናቋል።

ከዕረፍት መልስ ራሳቸውን አሻሽለው የቀሩቡት ምድረገነት ሽረዎች 54ኛው ደቂቃ ላይ የወላይታ ተጫዋች በራሱ ሳጥን ውስጥ ኳስ በእጅ መንካቱን ተከትሎ ያገኙትን ፍፁም ቅጣት ምት በሽመክት ጉግሳ አማካኝነት ወደ ግብነት ቀይረው ጨዋታውን መምራት ጀምረዋል። አማካዩ ኳሷን ከመታ በኋላ ግብ ጠባቂው እና ቋሚውን ለትማ የተመለሰች ኳስ በድጋሜ በመምታት ነበር ያስቆጠረው።

ከግቡ መቆጠር በኋላ ወደ ጨዋታ ለመመለስ ወደ ተጋጣሚ የግብ ክልል ተጠግተው መጫወት የቻሉት የጦና ንቦች በቅዱስ ቂርቆስ የሳጥን ውጭ ሙከራ ያደረጉ ቢሆንም በግብጠባቂው ሪችሞንድ አይ አማካኝነት ተመልሶባቸዋል ሙሉ ለሙሉ በሚባል ደረጃ ጨዋታውን የተቆጣጠሩት እና በቴዎድሮስ ታፈሰ አማካኝነት ከቆመ ኳስ ጥሩ ሙከራ ያደረጉት የጦና ንቦቹ ከተደጋጋሚ ሙከራዎች በኋላ በ 87ኛው ደቂቃ ላይ ከመዓዝን ምት ተሻምታ ተቀይሮ የገባው አዛርያስ አቤል በግንባሩ ገጭቶ ባስቆጠራት ግብ አቻ መሆን ችለዋል። ወላይታ ድቻዎች በተሰጡት ጭማሪ ደቂቃዎች በቅዱስ ቂርቆስ እና ዮናታን ኤልያስ አማካኝነት ያለቀላቸው ሙከራዎች ማድረግ ቢችሉም ጨዋታው ተጨማሪ ግብ ሳይቆጠርበት በአቻ ውጤት ተጠናቋል።


