ሪፖርት | ወልዋሎዎች ጣፋጭ ድልን ሲያሳኩ ድሬዳዋ ከተማ እና ሲዳማ ቡና ነጥብ ተጋርተዋል

ሪፖርት | ወልዋሎዎች ጣፋጭ ድልን ሲያሳኩ ድሬዳዋ ከተማ እና ሲዳማ ቡና ነጥብ ተጋርተዋል

የሲቢኢ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የ9ኛ ሳምንት የምድብ አንድ ጨዋታዎች ዛሬም ሲቀጥሉ ወልዋሎ ተከታታይ ድሉን ሲያሳካ የድሬዳዋ ከተማ እና ሲዳማ ቡና ጨዋታ ባዶ ለባዶ ተጠናቋል።

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከ ወልዋሎ

ወደ ድል ለመመለስ እና ድላቸውን ለማስቀጠል የሚያልሙ ቡድኖችን  ያገናኘው የዕለቱ ቀዳሚ ጨዋታ በመጀመርያው አጋማሽ ቀዝቃዛ እና በሙከራዎች ያልታጀበ ነበር። ሆኖም ጨዋታው በተጀመረ በ3ኛው ደቂቃ ላይ ጥሩ አጀማመር የነበራቸው የኢትዮጵያ ንግድ ባንኮች በወልዋሎ ሳጥን የተሰራውን ጥፋት ተከትሎ ያገኙት ፍፁም ቅጣት ምት በአዲስ ግደይ አማካኝነት አስቆጥረው ጨዋታውን መምራት ጀምረዋል። ከግቡ መቆጠር በኋላ ወልዋሎዎች የተሻለ ብልጫ  ወስደው ጥቂት የማይባሉ የግብ ዕድሎች ቢፈጥሩት በሙከራ ደረጃ ፍሬው ሰለሞን ከቆመ ኳስ ከሞከሯት ውጭ ለግብነት የቀረበ ሙከራ ማድረግ አልቻሉም።
አጋማሹ ሊገባደድ ደቂቃዎች ሲቀሩትም የኢትዮጵያ ንግድ ባንኩ ካሌብ አማንክዋህ በሁለት ቢጫ ካርዶች በቀይ ካርድ ከሜዳ ወጥቷል።

ወልዋሎዎች ብልጫቸውን ያስቀጠሉበት ሁለተኛው አጋማሽ ቢጫዎቹ በሁሉም ረገድ የተሻለ እንቅስቃሴ ያደረጉበት ሲሆን ኪሩቤል ወንድሙ ከቆመ ኳስ እንዲሁም ኮንኮኒ ሐፊዝ ከሳጥኑ ጠርዝ ካደረጓቸው ሙከራዎች በኋላም በ65 ኛው ደቂቃ ላይ በኢትዮጵያ ንግድ ባንኮች ሳጥን የተሰራውን ጥፋት ተከትሎ ያገኙት ፍፁም ቅጣት ምት በጌትነት ተስፋዬ አማካኝነት አስቆጥረው አቻ መሆን ችለዋል።

ከግቧ መቆጠር በኋላም ጫና መፍጥራቸውን ቀጥለው ፍቃዱ መኮንን ከሳጥኑ የቀኝ ክፍል አሻግሮት ሰመረ ሀፍታይ ከመታው በኋላ ፓላክ ቾል በጥሩ መንገድ በመለለው ኳስ ግብ ለማስቆጠር ተቃርበው የነበሩት ወልዋሎዎች ጨዋታው ሊጠናቀቅ ሽርፍራፊ ደቂቃዎች ሲቀሩት ተቀይሮ በገባው ስምዖን ማሩ አማካኝነት ግብ ማስቆጠር ችለዋል፤ ስምዖን ማሩ ሌላው ተቀይሮ የገባው ምክኤለ ኪዳነ ከቀኝ መስመር አክርሮ  ከመታው በኋላ ፓላክ ቾል ያዳነውን ኳስ ተጠቅሞ በማስቆጠር ነበር ቡድኑን የማታ ማታ አሸናፊ ያደረገው።

ድሬዳዋ ከተማ ከ ሲዳማ ቡና

ጥሩ ፉክክር የተደረገበት የመጀመርያው አጋማሽ በርከት ያሉ ዕድሎች የተፈጠሩበት ቢሆንም ወደ ጥራት ያላቸው ሙከራዎች የተቀየሩት ግን ጥቂት ናቸው። በአመዛኙ ደቂቃዎች ብልጫ ወስደው የተንቀሳቀሱት ሲዳማ ቡናዎች በጅማሮ ላይ በፌደሬክ ኑሱ ካደረጋት ሙከራ በኋላ ሀብታሙ ታደሰ ከመዓዝን ተሻምታ በግንባር ባደረጋት እንዲሁም አጥቂው ከቆመ ኳስ ተሻግራ ያሬድ ባየህ በግምባር ከመለሳት በኋላ ተከላካዮች ያላራቋትን ኳስ አግኝቶ መቷት ተጫዋቾች ተደርበው በመለሷት ኳስ ግብ ለማግኘት ጥረት አድርገዋል። በአጋማሹ አመርቂ የፊት መስመር እንቅስቃሴ ባልነበራቸው ድሬዳዋ ከተማዎች በኩልም  ዓብዱሰላም የሱፍ አመቻችቷት አብዲሳ ጀማል አክርሮ በሞከራት ኳስ ሙከራ አድርገዋል።

ሁለተኛው አጋማሽ ተመጣጣኝ እንዲሁም ጥሩ ፉክክር የተደረገበት ቢሆንም ጥራት ባላቸው ሙከራዎች ያልታጀበ ነበር። በመጀመርዎቹ ሰላሣ ደቂቃዎች የነበራቸውን ብልጫ ማስቀጠል ባልቻሉት ሲዳማ ቡናዎች በኩል መስፍን ታፈሰ ሳጥን ውስጥ ከሀብታሙ ታደሰ የተቀበላትን ኳስ ተጠቅሞ መቷት አብዩ ካሳሁን በድንቅ ብቃት ያዳናት እንዲሁም ተቀይሮ የገባው ተመስገን መንገሻ ከቆመ ኳስ የተሻገረችውን ኳስ ተጠቅሞ በግምባር ያደረጋት ሙከራ፤  በሁለተኛው አጋማሽ ተሻሽለው በቀረቡት ድሬዳዋ ከተማዎች በኩል ደግሞ ጀሚል ያዕቆብ ከቀኝ መስመር አሻግሯት መሐመድኑር ናስር በግንባር ገጭቷት አማኑኤል ካል በጥሩ መንገድ የመለሳት ኳስ በሁለቱም ቡድኖች የታዩ ለግብ የቀረቡ ሙከራዎች ናቸው። አዝናኝ ግን በሙከራዎች ያልታጀበው ጨዋታም ግብ ሳይቆጠርበት በአቻ ውጤት ተጠናቋል።