የ10ኛው ሳምንት የሲቢኢ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ዛሬ በሚደረጉ ጨዋታዎች ፍፃሜውን ያገኛል።

ድሬዳዋ ከ አዳማ ከተማ
ባከናወኗቸው ዘጠኝ መርሐ-ግብሮች ሦስት ሦስት ጊዜ ሦስቱም የውጤት ዓይነቶች አስመዝግበው አስራ ሁለት ነጥቦች የሰበሰቡት ድሬዳዋ ከተማዎች በአምስተኛው ሳምንት ወልዋሎን ሁለት ለአንድ ካሸነፉ ወዲህ ባለፉት አራት ጨዋታዎች ድል ማድረግ አልቻሉም፤ በዛሬው ጨዋታ ድል ማድረግም ከሰንጠረዡ አካፋይ ከፍ የማለት ዕድል ይሰጣቸዋል። በመጨረሻዎቹ ሳምንታት የሊጉ መሪ ሲዳማ ቡናና ተከታዩ ፋሲል ከነማ እንዲሁም መቻል እና ምድረ ገነት ሽረን የገጠሙት ብርቱካናማዎቹ ከገጠሟቸው ቡድኖች ጥንካሬ አንፃር ሲታት ያሳዩት እንቅስቃሴ መጥፎ የሚባል ባይሆንም የማጥቃት አጨዋወታቸው ግን ለውጦችን ይሻል። በአራት መርሐ-ግብሮች አንድ ግብ ብቻ ያስቆጠረው እንዲሁም በጨዋታዎቹ ጥቂት የግብ ዕድሎች የፈጠረው ቡድኑ በዛሬው ጨምሮ በቀጣይ ጨዋታዎች የተጠቀሰውን ድክመት መቅረፍ ይጠበቅባቸዋል።
አራት አራት ጊዜ የድል እና የአቻ ውጤቶች በእኩሌታ እንዲሁም አንድ ሽንፈት አስመዝግበው 16 ነጥቦች የሰበሰቡት አዳማ ከተማዎች ይበልጥ ወደ ሊጉ አናት እንዲጠጉ የሚያስችላቸውን ድል ለማግኘት ብርቱካናማዎቹን ይገጥማሉ። በ9ኛው ሳምንት ጨዋታ በሙጂብ ቃሲም ብቸኛ ግብ ቅዱስ ጊዮርጊስ ማሸነፍ የቻሉት አዳማ ከተማዎች ከመጨረሻዎቹ ስድስት ጨዋታዎች ማግኘት ከሚገባቸው አስራ ስምንት ነጥቦች አምስቱን ጥለው አስራ ሦስቱን በማሳካት ጥሩ ጉዞ በማድረግ ላይ ቢገኙም በግብ ማስቆጠሩ ረገድ ያላቸው ድክመት ግን መቀረፍ የሚገባው ነው። በዘጠኝ ሳምንታት ጉዞ በጨዋታ ከአንድ ግብ በላይ ማስቆጠር ያልቻለውን የማጥቃት አጨዋወት ማሻሻልም የአሰልጣኝ ስዩም ከበደ ቀዳሚ ስራ ይሆናል ተብሎ ይጠበቃል።
በድሬዳዋ ከተማ በኩል አቤል አሰበ እና አስቻለው ታመነ በጉዳት አቡበከር ሻሚል ደግሞ በቅጣት ምክንያት የማይኖሩ ሲሆን በአዳማ ከተማ በኩል አህመድ ሁሴን ፣ አብዱልከሪም መሐመድ እና ጋዲሳ ዋዶ በሕመም ከጨዋታው ውጪ ሲሆኑ ቢኒያም ዐይተን ጤንነቱ መሻሻል ስላለው ዛሬ ቡድኑን ተቀላቅሏል።
ሁለቱ ቡድኖች በአጠቃላይ በሊጉ 26 ጊዜ ሲገናኙ አዳማ ከተማዎች 12 ጊዜ ባለድል በመሆን የበላይ ሲሆኑ ድሬዳዋ ከተማዎች ደግሞ በ7 ይከተላሉ የተቀሩት 7 ጨዋታዎች ደግሞ በአቻ ውጤት የተቋጩ ነበሩ። በጨዋታዎቹ አዳማዎች 30 ሲያስቆጥሩ ድሬዎች በአንጻሩ 24 ግቦችን ማስቆጠር ችለዋል።
ሲዳማ ቡና ከ ቅዱስ ጊዮርጊስ
በሀያ ነጥቦች በሊጉ አናት ላይ የተቀመጡት ሲዳማ ቡናዎች ትላንት ድል አድርጎ በነጥብ ከተስተካከላቸው ፋሲል ከነማ ጋር ያላቸውን የነጥብ ልዩነት በማስፋት መሪነታቸውን ለማጠናከር ዛሬ ወሳኝ ጨዋታ ያከናውናሉ። በመጨረሻው የሊጉ መርሐ-ግብር ከድሬዳዋ ከተማ ጋር ነጥብ የተጋራው ቡድኑ በ3ኛው ሳምንት በፋሲል ከነማ ከገጠመው ሽንፈት በኋላ ባደረጋቸው ስድስት ጨዋታዎች በአራቱ ድል አድርጎ በሁለቱ ደግሞ የአቻ ውጤት ማስመዝገብ ጥሩ ጉዞ በማድረግ ላይ ይገኛል። ቡድኑ በውጤትም ይሁን በእንቅስቃሴ ደረጃ በመልካም ሁኔታ እየተጓዘ ቢገኝም ዓመቱን በድንቅ ሁኔታ በጀመረው የፊት መስመር ላይ የሚስተዋለው ህፀፅ እና የውሳኔ አሰጣጥ ድክመት መቅረፍ ይኖርበታል።
አምስት ድሎች እና አራት ሽንፈቶች አስመዝግበው አስራ አምስት ነጥቦች መሰብሰብ የቻሉት ቅዱስ ጊዮርጊሶች ደረጃቸውን ለማሻሻል በአምስት ነጥቦች ከሚበልጣቸው ሲዳማ ቡና ጋር ይፋለማሉ። ከመጀመርያዎች አምስት ጨዋታዎች በአራቱ ድል አድርገው ዓመቱን በጥሩ ሁኔታ የጀመሩት ፈረሰኞቹ በቅርብ ሳምንታት መጠነኛ መንገራገጮች ገጥሟቸዋል። በመጨረሻዎቹ አራት የሊጉ ጨዋታዎች ሦስት ሽንፈቶች ያስተናገደው ቡድኑ ካለው የነጥብ መቀራረብ አንፃር በተከታታይ ጨዋታ ነጥብ መጣል የደረጃ ማሽቆልቆል ሊያስከትልበት ስለሚችል በብዙ ረገድ ተሻሽሎ መቅረብ ይኖርበታል። በተለይም በመጨረሻዎቹ አራት መርሐ-ግብሮች አንድ ግብ ብቻ ያስቆጠረው የማጥቃት ጥምረት ለውጦችን ይሻል።
ሲዳማ ቡናዎች በቅጣትም ሆነ በጉዳት የሚያጡት ተጫዋች የለም፤ በቅዱስ ጊዮርጊስ በኩል ደግሞ አዲሱ አቱላ እና አሚን ነስሩ ከጉዳት ሲመለሱ አቤል ያለው እና ሻሂዱ ሙስጠፋ ከዛሬው ጨዋታ ውጭ ናቸው።
ሁለቱ ቡድኖች በሊጉ 30 ጊዜ ተገናኝተው ቅዱስ ጊዮርጊስ 18 ጊዜ በማሸነፍ የበላይነት ሲኖረው በአንፃሩ ሲዳማ ቡና 3 ጊዜ አሸንፏል። 9 ጨዋታዎች ደግሞ አቻ ተጠናቋል። ቅዱስ ጊዮርጊስ 39 ሲዳማ ቡና ደግሞ 13 ጎሎችን አስመዝግበዋል።
መቻል ከ ኢትዮ ኤሌክትሪክ
በአስራ ስድስት ነጥቦች 4ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጡት መቻሎች መሪዎቹን እግር በእግር ለመከታተል የሚያግዛቸውን ነጥብ ለማግኘት ጠንካራውን ኤሌክትሪክ ይገጥማሉ። በመጨረሻዎቹ አምስት ጨዋታዎች ድል ማድረግ ያልቻለው ቡድኑ በፊት መስመር ላይ ያለውን ጥንካሬ ማስቀጠል ቢችልም በመከላከል ክፍሉ ላለው ድክመት ግን መፍትሔ ማበጀት አልቻለም። በመጨረሻዎቹ አራት ጨዋታዎች ስድስት ግቦችን ያስተናገደውን ክፍል ማሻሻልም ከቡድኑ ይጠበቃል።
በዘጠኝ ጨዋታዎች አስራ ስድስት ነጥቦችን ሰብስበው በሰንጠረዡ ወገብ የተቀመጡት ኢትዮ ኤሌክትሪኮች ከሁለት የጨዋታ ሳምንታት በኋላ ድል አድርገው ደረጃቸውን ለመሻሻል ወደ ሜዳ ይገባሉ። በውድድሩ ዓመቱ ከብዙዎች ግምት ውጭ ድንቅ ዓመት በማሳለፍ ላይ ከሚገኙ የሊጉ ክለቦች የሚጠቀሱት ኤሌክትሪኮች በውጤታማነቱ ለመዝለቅ በግብ ማስቆጠሩ ረገድ ያላቸውን ውስን ድክመት መቅረፍ ይኖርባቸዋል።
ሁለቱ ቡድኖች በሊጉ 30 ጊዜ ተገናኝተው ኤሌክትሪክ 11 በማሸነፍ ቀዳሚ ሲሆን መቻል 5 አሸንፎ በ14 ጨዋታዎች ደግሞ ነጥብ ተጋርተዋል። መቻል 32 ሲያስቆጥር ኤሌክትሪክ ደግሞ 44 ግቦች አሉት።


