ሪፖርት | ሰጎኖቹ ድል ሲቀናቸው የጣና ሞገዶቹ እና ዐፄዎቹ ጨዋታ አቻ ተጠናቋል

ሪፖርት | ሰጎኖቹ ድል ሲቀናቸው የጣና ሞገዶቹ እና ዐፄዎቹ ጨዋታ አቻ ተጠናቋል

በአዲስ አበባ በተደረጉ ሁለት ጨዋታዎች ነጌሌ አርሲ በአሸብር ውሮ ብቸኛ ግብ ወልዋሎ ሲያሸንፍ ባህርዳር ከተማ እና ፋሲል ከነማ ነጥብ ተጋርተዋል።

ነጌሌ አርሲ ከ ወልዋሎ ዓ. ዩ

የ11ኛው ሳምንት የመጀመርያ ጨዋታ ነጌሌ አርሲ እና ወልዋሎ ዓ.ዩ አገናኝቷል። በጨዋታው ፈጣን አጀማመር የነበራቸው ነጌሌ አርሲዎችም ገና በአምስተኛው ደቂቃ ነበር በፍፁም ቅጣት ምት ግብ መሪ መሆን የቻሉት። ኪሩቤል ወንድሙ ሳጥን ውስጥ ከቤ ብዙነህ ላይ የሰራውን ጥፋት ተከትሎ የተሰጠውን ፍፁም ቅጣት ምት  አምበሉ አሸብር ውሮ መረብ ላይ አሳርፎ ነበር ሰገኖቹን መሪ ያደረገው። በኳስ ቁጥጥርም ሆነ ዕድሎች በመፍጠር ረገድ ብልጫ የነበራቸው ነጌሌዎች ከጨዋታ ውጪ ተብሎ ከተሻረው የኢብሳ በፍቃዱ አጋጣሚ በኋላ በ22ኛው ደቂቃ ሀቢብ ከማል ከኢብሳ በፍቃዱ የተቀበላትን ኳስ ተጠቅሞ ባደረጋት ጥሩ ሙከራ ተጨማሪ ግብ ለማስቆጠር ጥረት አድርገዋል።

ከቤ ብዙነህ አሻምቶት ሀቢብ ከማል በግንባሩ ሞክሮት ግብ ጠባቂው ያዳነው እንዲሁም ኢብሳ በፍቃዱ የተመለሰውን ኳስ ተጠቅሞ በድጋሜ ሞክሮት ሙታክብዋ ጆኤል የመለሰው ኳስም የሰጎኖቹን መሪነት ከፍ ለማድረግ የተቃረቡ ሙከራዎች ሲሆኑ ወልዋሎዎች በአንፃሩ የጠሩ ዕድሎች ሳይፈጥሩ ከቆዩ በኋላ አጋማሹ ሊጠናቀቅ ሽርፍራፊ ደቂቃዎች ሲቀሩት  አሸብር ውሮ ሳጥን ውስጥ ኳስ በእጁ መንካቱን ተከትሎ ያገኙት ፍፁም ቅጣት ምት ጌትነት ተስፋዬ አምክኖታል።

ሁለተኛው አጋማሽ ጥቂት ሙከራዎች የተደረጉበት ሲሆን ነጌሌ አርሲዎች ውጤቱን አስጠብቀው ለመውጣት የተንቀሳቀሱበት ወልዋሎዎች በተቃራኒው የአቻነት ግብ ፍለጋ በረጃጅም ኳሶች ዕድሎች ለመፍጠር ጥረት ያደረጉበት ነበር። ሆኖም በአጋማሹ ይህ ነው የጠራ ሙከራ ሳይደረግ በአምስተኛው ደቂቃ በተቆጠረች ብቸኛ የፍፁም ቅጣት ምት ግብ ነጌሌ አርሲዎች ሶስት ነጥብ  አግኝተዋል።

ባህርዳር ከተማ ከ ፋሲል ከነማ

በኢንተርናሽናል ዋና ዳኛ ማኑሄ ወልደፃዲቅ መሪነት የተካሄደው የሳምንቱ ተጠባቂ ጨዋታ ብርቱ ፉክክር የተደረገበት ነበር።

ቡድኖቹ በፈጣን ሽግግር እና ወደ ሶስተኛ ሜዳ ክፍል በሚጣሉ ኳሶች ዕድሎች ለመፍጠር ጥረት ያደረጉበት የመጀመርያው አጋማሽ በርካታ የግብ ዕድሎች የተፈጠሩበት። በዐፄዎቹ በኩል በረከት ግዛው እና አቤኔዘር ዩሐንስ ከሳጥን ውጪ ያደረጓቸው ሙከራዎች በጣና ሞገዶቹ በኩል ደግሞ ወንደሰን በለጠ ጨርፎ ያደረገው እንዲሁም አማኑኤል ገብረሚካኤል ሳጥን ውስጥ መረጋጋት ተስኖት ሳይጠቀምባት የቀረው አጋጣሚ ይጠቀሳሉ። በአጋማሹ መገባደጃ ደቂቃዎችም ዐፄዎቹ መሪ ለመሆን ተቃርበው ነበር፤ ከቆመ ኳስ ታሻግራ ያሬድ ብርሃኑ በግንባሩ ከጨረፋት በኋላ ናትናኤል ማስረሻ ብቻውን ሆኖ ያልተጠቀመባት ሙከራ እንዲሁም ዋሳዋ ጂኦፍሪ ከቆመ ኳስ በቀጥታ ወደ ግብ መቷት ፔፔ ሰይዶ ጨርፎ ወደ ውጪ ያወጣት ሙከራም ዐፄዎች መሪ ለማድረግ የተቃረቡ ሙከራዎች ነበሩ።

ሁለተኛው አጋማሽ ዐፄዎቹ ከተጋጣሚያቸው የተሻለ እንቅስቃሴ ያደረጉበት ሲሆን  ከመጀመርያው አጋማሽ አንፃር ግን ጥቂት የግብ ዕድሎች የተፈጠሩበት ነበር። አንፃራዊ ብልጫ የነበራቸው ዐፄዎቹ 70ኛው ደቂቃ ላይ ዳግም አወቀ  ከመስመር  ሞክሯት ፔፔ ሰይዶ የመለሳት ጥሩ አጋጣሚ ተጠቃሽ ስትሆን በረጃጅም ኳሶች ዕድሎች ለመፍጠር ጥረት ያደረጉት የጣና ሞገዶች ግን የፋሲል ከነማ ተከላካዮች አልፈው ሙከራ ማድረግ አልቻሉም። ይህንን ተለትሎ የጣና ደርቢ ግብ ሳይቆጠርበት በአቻ ውጤት ተቋጭቷል።