👉”.. በውስጣቸው እግር ኳሳዊ ሁነት የሚያስተናግዱ ሳይሆን ፅሞና የሚፈልጉ ሰዎች አርምሞ የሚይዙበት የአርምሞ ማዕከልነት ይመስላሉ”
👉”ከእግር ኳሱ ቀንደኛ ተዋናዮች ፍላጎት ጋር የማይጣጣም የመርሐ ግብር አወጣጥ ስርዓት…”
👉”ከሙከራዎች የፀዱ፣ በግቦች ድርቅ ክፉኛ የተመቱ እንዲሁም ጥንቃቄ ላይ ያመዘኑ…”
እግር ኳስ አብዝቶ እንደሚወደድ በሚነገርባት ሀገራችን ስለምን ስታዲየሞቻችን ፀጥታ ነገሰባቸው?
በአንድ ሀገር የእግርኳስ ህልውና ወሳኝ ከሆኑ ነገሮች አንዱ ደጋፊ ነው። ሜዳዎች ላቅ ያለ ክህሎት ባላቸው ተጫዋቾች ቢሞሉ፣ የክለቦች የአጨዋወት መንገድ የፈለገ ማራኪ ቢሆን ካለ ደጋፊ ሁሉም ነገር ከንቱ ነው !
ደጋፊዎች በሜዳዎች ላይ ከሚፈጥሩት ልዩ ድባብ እና በጨዋታዎች ከሚጨምሩት ቀለም በተጨማሪ በስታዲየሞች በመታደም የሚሰጡት ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ በአንድ ክለብ ህልውና ያለው ሚና አይተኬ ነው። ደጋፊዎች የክለባቸውን ባህል እና ማህበራዊ እሴቶች በማስቀጠል ረገድ የደም ስር ያክል ወሳኝ መሆናቸውን ተከትሎም ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በሀገራችን ስታዲየሞች የሚታየው ክፉኛ የደጋፊዎች ድርቅ በተመለከተ ቆም ብለን እንድናስብ ያደርገናል።
ጥቂት ዓመታትን ወደ ኃላ መለስ ስንል በተለይ ከሁለት ሺዎቹ አጋማሽ አንስቶ በተዋረድ ባሉ የሊግ እርከን ውድድሮች በርከት ያሉ ህዝባዊ መሰረት ያላቸው የክልል ከተማ ክለቦች ወደ ሊጎች መቀላቀል መጀመራቸውን ተከትሎ እጅግ ከፍተኛ ቁጥር ያለው ደጋፊ ስታዲየሞችን የፌስቲቫል ድባብ እንዲላበሱ አድርጎ ነበር። በወቅቱ በከፍተኛ የደጋፊ አጀብ የተሞሉ ጨዋታዎችን ማየት ተለማምደን የነበረ ቢሆንም ባለፉት ጥቂት ዓመታት ግን የደጋፊዎች ቁጥር በከፍተኛ ሁኔታ ተመናምኖ ደጋፊ አልባ ጨዋታዎች መመልከት የተለመደ ነገር ሆናል።
ከጥቂት ዓመታት በፊት በሀገሪቱ እግርኳስ ውስጥ ከነበሩ ጥቂት አወንታዊ ነገሮች አንዱ በርከት ያለ ቁጥር ያለው ደጋፊ በስቴድየሞች ታድሞ ለሚወደው ክለብ በየፊናው ደማቅ ድጋፍ መለገስ መቻሉ ነበር። መታረም ከነበረባቸው ክፍተቶች ውጪ ደጋፊዎች በሜዳ ተገኝተው ቡድናቸው የሚያበረታቱበት ባህልም ለደካማው እግር ኳሳችን ብቸኛ ድምቀት ነበር ቢባል ማጋነን አይሆንም።
<img class=”aligncenter size-full wp-image-87035″ src=”https://soccerethiopia.net/wp-content/uploads/2023/04/Gofere-900×110-1.jpg” alt=”” width=”900″ height=”110″ />
ለመሆኑ ደጋፊው ለምን ሸሸ ?
1 የሊጎች የውድድር የቅርፅ ለውጥ !
የወድድር ቅርፅ ለውጥ መደረጉ ሊጎቻችን በደጋፊዎች ድርቅ ክፉኛ እንዲመቱ ካደረጉ ምክንያቶች ዋነኛው እንደሆነ ብዙዎች ይስማሙበታል። ከዚህ ቀደም የስታድየሞች ድምቀት የነበረው ደጋፊ በከተማው በቅርበት የሚወደውን ክለብ መደገፍ አለመቻሉም የቅርፅ ለውጡ ለችግሩ ቀዳሚ ምክንያት እንደሆነ እንደ አንድ ማሳያ መጥቀስ ይቻላል።
ከዘህ ቀደም በነበረው በሜዳ እና ከሜዳ ውጭ ( Home And Away) የውድድር ቅርፅ የጨዋታዎች የተጠባቂነት ስሜት እንዲሁም በደጋፊዎች ዘንድ የነበረውን ስታዲየም ተገኝቶ ይህን ሁነት የመታደም ፍላጎት ከፍተኛ ነበር። በትራንስፖርት ዋጋ እና አማራጭ ውስንነቶች ምክንያት ከቦታ ቦታ ተጓጉዞ ጨዋታዎችን የመመከት ባህል ባልዳበረበት የሀገራችን እግር ኳስ ውድድሮች በአንድ ወይም በሁለት ከተሞች እንዲካሄዱ መደረጉም ደጋፊ ከስታድየሞች እንዲርቅ አድርጎታል።
ዘንድሮ ግን ፕሪምየር ሊጉ ከዓመታት በኃላ ወደ መዲናችን አዲስ አበባ መመለሱን ተከትሎ መጠነኛ ለውጥ ይኖራል የሚል የብዙሃን ግምት ነበር። በአዲስ አበባ ካለው ህብረ ብሔራዊ ስብጥር አንፃር ጨዋታዎች በተሻለ የደጋፊዎች ቁጥር ይደረጋል የሚል ግምትን ቢያሳድርም እስካሁን ባለው ሂደት ግን እየታዘብነው ያለነው የተገላቢጦሽ ይመስላል። በግልፅ ለመነጋገር በአንዳንድ የሊጉ ጨዋታዎች ስታዲየሞቻችንን ለተመለከተ በውስጣቸው እግር ኳሳዊ ሁነት የሚያስተናግዱ ሳይሆን ፅሞና የሚፈልጉ ሰዎች አርምሞ የሚይዙበት የአርምሞ ማዕከልነት ይመስላሉ።
2 የሊጎች መርሐ ግብር አወጣጥ
የብዙሐን ፍላጎት ከግምት ውስጥ ያላስገባው የመርሐ ግብር አወጣጥ ስርዓት ሌላኛው ምክንያት ነው። በሀገራችን የሚካሄዱ ውድድሮች በተወሰኑ የመጫወቻ ሜዳዎች በመደረጋቸው ምክንያት ጨዋታዎች ከሰኞ እስከ ሰኞ መካሄድ ከጀመሩ ዓመታት ተቆጥረዋል። በዚህም አብዛኞቹ ጨዋታዎች በስራ ቀናት እና በስራ ሰዓታት መከናወናቸውን ተከትሎ ደጋፊዎች ወደ ሜዳ ለመሄድ ቢፈልጉ እንኳን ተግዳሮት እንደሚፈጥርባቸው መገመት አያዳግትም።
ከእግር ኳሱ ቀንደኛ ተዋናዮች ፍላጎት ጋር የማይጣጣም የመርሐ ግብር አወጣጥ ስርዓት እየተከተልክ ደጋፊ ወደ ሜዳ እንዲመለስ መሻት የማይቻል ነገር ነው። ከመርሐ ግብር አወጣጥ ጋር የተያያዘው ጉዳይም አወዳዳሪ አካላት መፍትሔ ሊያበጁለት የሚገባ አንገብጋቢ ችግር ነው።
3 የጨዋታዎች ጥራት ጉዳይ ?
በሀገራችን የሚካሄዱ የጥራት ደረጃቸው የወረዱ ጨዋታዎች መብዛታቸው ስታድየሞች በደጋፊ እጦት እንዲመቱ ምክንያት ከሆኑ ጉዳዮች አንዱ ነው። እግር ኳሳችን ስር ነቀል አብዮት እንደሚፈግ ሁሉም የሚስማማበት ነጥብ ነው። ይህ ጉዳይ ሰፊ ጥናት እና የረዥም ዓመታት ስራ የሚጠይቅ ቢሆንም አሰልጣኞች እንዲሁም በክለቦቹ ዙሪያ የሚገኙ አካላት ከውጤት በዘለለ ለጨዋታዎች ጥራት መስራትና መጨነቅ ይኖርባቸዋል። በሊጎቻችን የሚከናወኑ ጨዋታዎች ከሙከራዎች የፀዱ፣ በግቦች ድርቅ ክፉኛ የተመቱ እንዲሁም ጥንቃቄ ላይ ያመዘኑ ስለሆኑም ደጋፊ ከስታድየሞች እንዲሸሽ ሆኗል።
4 የክለቦች እንዲሁም የመገናኛ ብዙሐን ጉዳይ ?
ቡድኖች ከደጋፊያቸው ጋር የሚኖራቸው የስሜት ትስስር (Emotional attachment ) አንድ ደጋፊ ስቴድየሞችን እንዲያዘወትርም ሆነ ከሜዳ እንዲሸሽ ምክንያት ከሚሆኑ ነገሮች አንዱ ነው። በሀገራችን እግር ኳስ በክለቦች እና በደጋፊዎች መካከል ያለው ደካማ የስሜት ትስስር ደግሞ ለተገለፀው ችግር እንደ አንድ ምክንያት የሚጠቀስ ነው።
ክለቦቻችን በማሕበራዊ ትስስር ገፆች ላይ ያላቸው ንቁ ያልሆነና ወጥነት የጎደለው ተሳትፎ፣ በደጋፊዎች መሀል እንዲሁም በደጋፊው እና በክለቡ መካከል የሚኖረውን ትስስር የሚያጉለብቱ ውይይቶችና እንቅስቃሴዎች በማድረግ ረገድ ያላቸው ውስንነትም ክለቡ ከልብ ደጋፊው ጋር እንዲነጣጠል አድርጎታል። የስሜት ትስስር ማዳበር በሁለት አካላት መካከል ለሚኖር ጥልቅና መሰረት ያለው ግንኙነት ወሳኝ ነው። ይህም ደጋፊው በክለቡ የእኔነት ስሜት እንዲሰማው በማድረግ በጥሩም ይሁን በመጥፎው ጊዜ ከክለቡ ዙርያ እንዳይርቅ ያደርገዋል። መሰል ስራዎች በመስራት በአንድ ጀምበር የሚመጣ ውጤት ባይሆንም ክለቦች ከደጋፊዎቻቸው ጋር ያላቸውን ግንኙነት ማጠንከር ላይ አበክረው መስራት ይጠበቅባቸዋል።
መገናኛ ብዙሐንም ስለተመልካቾች ከሜዳ መራቅ ስናስብ ተጠያቂ ከምናደርጋቸው አካላት ውስጥ ናቸው። በርግጥ በቀዳሚነት ከሚነሱ ዋና ዋና ጉዳዮች ውስጥ የሚካተት ባይሆንም በሀገር ውስጥ ለሚከናወኑ ሊጎች እየተሰጠ ያለው በቂ ያልሆነ ትኩረት ለችግሩ የራሱን አስተዋጽዖ አድርጓል።
ሀገሬው ከራሱ እግር ኳስ ይልቅ ስለ አርሰናል እና ማንቸስተር አብዝቶ ማሰብ ከጀመረ ሰነባብቷል። አሁን ላይ የሀገር ውስጥ ጨዋታዎችን ለመታደም ወደ ስታዲየም ማምራት በአብዛኛው ሰዎች አዕምሮ ውስጥ የሚመጣ ቀዳሚ ጉዳይ አይደለም ብንልም ለስህተት የሚዳርግ አይመስልም። ታድያ ይህንን አካሄድ የመቀየር ኃላፊነት ካላቸው አካላት ውስጥ የሆኑት መገናኛ ብዙሐን በሀገር ውስጥ እግር ኳስ ዙርያ ያላቸው ተሳትፎ በብዙ ረገድ ማሻሻል ይጠበቅባቸዋል።
በስታድየሞች መታደም ከሚያዘወትረው ደጋፊ ውጭ እግር ጥሎት ለመጣ ሰውም ያላቸው መስህብ እጅግ ደካማ በመሆኑ ሊጎቹ በተለያዩ አማራጮች በሚከወኑ የመገናኛ ብዙሐን ስራዎች ብቻ የብዙሐን የትኩረት ማዕከል ማድረግ እንደማይቻል እሙን ነው። ሆኖም የሀገር ውስጥ እግር ኳስ በተመለከተ በሀገሪቱ መገናኛ ብዙሃን ሆነ አሁን ላይ ዋነኛ የመረጃ ልውውጥ አማራጭ በሆኑት ማህበራዊ ትስስር ገፆች ላይ የሚሰጠው ትኩረት በየጊዜው እያሽቆለቆለ መምጣቱ ሰዎች ጨዋታዎችን መከታተል ይቅር እና የጨዋታ መርሃግብሮችን የማወቅ ዕድላቸው የመነመነ እንዲሆን የራሱን አስተዋጽዖ አድርጓል።
እጅግ ደካማ የሆነው እግር ኳሳችን እንዳይሞት እስካሁን እስትንፋሱን ያስቀጠሉት ደጋፊዎች ናቸው ቢባል ማጋነን አይሆንም። በመሆኑም አሁን ላይ እግር ኳሳችን ካሉበት ዓብይት ችግሮች ሁሉ ጊዜ የማይሰጠውን የደጋፊዎች ቁጥር መመናመን ስለሆነ ከላይ የተዘረዘሩት ዋና ዋና ችግሮችን ለመቅረፍ በአበክሮ መስራት ይኖርብናል።

