ሪፖርት | ኢትዮጵያ መድን እና ወልዋሎ ዓ/ዩ ነጥብ ተጋርተዋል

ሪፖርት | ኢትዮጵያ መድን እና ወልዋሎ ዓ/ዩ ነጥብ ተጋርተዋል

በ15ኛ ሳምንት የመጀመሪያ ቀን በአ/አ ስታዲየም በተደረገ ብቸኛ ጨዋታ ኢትዮጵያ መድን እና ወልዋሎ ዓዲግራት ዩኒቨርሲቲ ያለ ግብ ተለያይተዋል።

በአዲስ አበባ ስታዲየም በ15ኛ ሳምንት የመጀመሪያ ቀን ጨዋታ ኢትዮጵያ መድንን ከወልዋሎ ዓዲግራት ዩኒቨርሲቲ አገናኝቷል። የመድኖቹን ጥንካሬ የተመለከትንበትን እና የተሻለ የግብ ማግባት አጋጣሚዎችን ሲፈጥሩ ያስተዋልንበት የመጀመሪያ አጋማሽ 3 ዒላማቸውን የጠበቁ ሙከራዎች የተደረጉበት ሲሆን ሁሉንም ሙከራዎችን ያደረጉት ኢትዮጵያ መድኖች ነበሩ። የጨዋታ ብልጫ የተወሰደባቸው ቢጫ ለባሾቹ በአጋማሹ ምንም አይነት ሙከራ ያላስመለከቱን ቢሆንም ኮንኮኒ ሃፊዝን ኢላማ ባደረጉ ረጃጅም ኳሶች የመልሶ ማጥቃት እንቅስቃሴ እያደረጉ የመሃል ሜዳ ብልጫ ለመውሰድ ጥሩ ፉክክር ማድረግ ችለዋል።

በ12ኛው ደቂቃ ረመዳን የሱፍ ከሳጥን ውጪ ሆኖ ካደረገው ኢላማውን ከጠበቀው ሙከራ በደቂቃዎች ልዩነት አለን ካይዋ በቢጫ ለባሾች ተከላካዮች መነሻ ሳጥን ውስጥ የተገኘውን ኳስ ብቻውን ሆኖ አግኝቶ ወደላይ ሰቅሎታል። በተደጋጋሚ ቀዳሚ ለመሆን እድሎችን ሲፈጥሩ የነበሩት መድኖች ዘለግ ካለ ደቂቃ ቆይታ በኋላ የመጀመሪያ ግብ ለማስቆጠር ጫፍ ደርሰው የነበረ ቢሆንም ወገኔ ገዛኸኝ ከረመዳን የሱፍ የተሻገረለትን ያለቀ ኳስ አግኝቶ ወደ ግብ መትቶ ግብ ጠባቂው እንዴትም ጨርፎ ያወጣባቸው እጅግ አስቆጪው አጋጣሚ ይጠቀሳል። እንዲሁም 40ኛው ደቂቃ ላይ ዳዊት አውላቸው ሳጥን ውስጥ ኳስ አግኝቶ በጠባብ መስመር መትቶ ለጥቂት ከቋሚ ብረት ርቆ ያለፈባቸው ሙከራ አይዘነጋም።

በአጠቃላይ የቢጫ ለባሾቹ ግብ ጠባቂ በተደጋጋሚ የተፈተነበት እና የመድኖቹ ግብ ጠባቂ በተቃራኒው ብዙም ያልተፈተነበት የመድን ብልጫ የታየበት የመጀመሪያ አጋማሽ ግብ የሚቆጠርበት እየመሰለ ያለግብ ተጠናቆ ለእረፍት ገብተዋል።

ጨዋታው በሁለተኛ አጋማሽ ተመልሶ ወልዋሎዎች በሽግግሮች ወደፊት በመሄድ ረገድ ተሻሽለው ቀርበው በመጀመሪያዎቹ አምስት ደቂቃዎች ብቻ ተደጋጋሚ አጋጣሚዎችን የፈጠሩ ሲሆን በተለይም 52ኛው ደቂቃ ላይ ፍሬው ሰለሞን እና በየነ ባንጃ ባደረጉት ጥሩ ቅብብል በየነ ባንጃ ከሳጥኑ ጠርዝ ላይ ኳሷን አግኝቶ አክርሮ መትቷት ግብ ጠባቂው ፋሲል ገብረሚካኤል በግሩም ሁኔታ ያገደባቸው አደገኛው ሙከራ ኢላማውን የጠበቀ ሙከራ ነበር። ከመጀመሪያው አጋማሽ አንፃር ፍፁም በተሻለ አቀራረብ የገቡት ቢጫ ለባሾቹ መሪ ለመሆን እጅጉን የቀረቡበትን ሌላኛውን ሙከራ 64ኛው ደቂቃ ላይ አድርገዋል። የተሻማውን ኳስ ሀፊዝ ኮንኮኑ በግንባሩ ገጭቶ ያደረገውን ሙከራ ግብ ጠባቂው እንዴትም ጨርፎ ካወጣባቸው በኋላ ያገኙትን ሌላኛውን አጋጣሚ ሀፍዝ ኮንኮኒ ግብ ጠባቂው መውጣቱን ተከትሎ ወደ ግብ መምታት የሚችለውን ኳስ ዘግይቶ ያመለጣቸው አስቆጪው አጋጣሚ ነበር።

በሁለተኛው አጋማሽ ጨዋታ ሲመለስ በኳስ ቁጥጥር አንፃራዊ ብልጫ እንዲሁ ወደፊት በመሄድ አኳያ በተቀዛቀዘ ጨዋታ እንቅስቃሴ የተመለሱት መድኖች ሙሉ ለሙሉ በግብ ማግባት ሙከራ በማድረግ ረገድ ደካማ እንቅስቃሴ ሲያደርጉ አስተውለናል። በዚህም በመስመር በኩል ኳሶችን ይዘው ለመግባት ጥረት ያድርጉ እንጂ የጠራ የግብ ማግባት እድል መፍጠር አልቻሉም። ቢጫ ለባሾቹ እስከመጨረሻው ደቂቃ በፈጣን ሽግግር ግቦችን ለማስቆጠር ጥረት ያደረጉበት እና መድኖች ግብ የማግባት ሙከራዎችን ማድረግ ያልቻሉበት  ሁለተኛው አጋማሽ ግብ ሳይቆጠርበት ጨዋታው ያለ ግብ ለመጠናቀቅ ተገዷል።