አነጋጋሪ ክስተት በተፈጠረበት ጨዋታ ሸገር ከተማ እና ፋሲል ከነማ ያለግብ አቻ ሲለያዩ ሀዲያ ሆሳዕና ከመመራት ተነስቶ ሽረ ምድረ ገነትን 3ለ1 አሸንፏል።
ሸገር ከተማ ከ ፋሲል ከነማ
በደረጃ ሰንጠረዡ ተቃራኒ ቦታ ላይ የተቀመጡ ቡድኖች ያገናኘው የአዲስ አበባ ስታዲየሙ የእለቱ ቀዳሚ ጨዋታ በመጀመሪያ አጋማሽ ቡድኖቹ እየተፈራረቁ የኳስ ቁጥጥር ብልጫ የወሰዱበት እና ተመጣጣኝ የጨዋታ እንቅስቃሴ የተመለከትንበት ቢሆንም ሁለቱም በተመሳሳይ ሶስተኛ ሜዳ ክፍል ደርሰው የጠራ ሙከራ ማድረግ ያልቻሉበት አጋማሽ ነበር። እምብዛም ከሙከራ ጋር መታጀብ ባልቻለው አጋማሽም የሸገር ከተማው አቤነዘር ህዝቅኤል ከሳጥን ውጭ ሆኖ የመታት ለግብ ጠባቂው ፈታኝ ያልነበረች ሙከራ ትጠቀሳለ። በመስመሮች በኩል ዕድሎችን ለመፍጠር ጥረት ሲያደርጉ የነበሩት ዐፄዎቹ ግን በአጋማሹ ግልፅ የግብ አጋጣሚ መፍጠር አልቻሉም።

ሁለተኛው አጋማሽ በክስተቶች ታጅቦ የጀመረ ሲሆን
53ኛ ደቂቃ ላይም ሸገር ከተማዎች ኳስ ይዘው ወደ ሳጥን በሚገቡበት ቅፅበት ኳስ ሳጥን ውስጥ በእጅ ተነክቷል በሚል ኢንተርናሽናል ዋና ዳኛ ዳንኤል ይታገሱ ፍፁም ቅጣት ምት ከወሰኑ በኋላ ከረዳት ዳኛው ጋር ተነጋግረው ውሳኔውን ወደ ቅጣት ምት የቀየሩበት አጋጣሚም ትኩረት የሚስብ ክስተት ነበር።
ሸገር ከተማዎች ከውሳኔው መሻር በኋላ በሳጥኑ ጠርዝ ያገኙትን ቅጣት ምት ሄኖክ አዱኛ በቀጥታ መቶ ግብ ጠባቂው ሞይስ ፖዋቲ በድንቅ ብቃት ያወጣው ሙከራም ሸገር ከተማዎችን መሪ ለማድረግ ተቃርቦ ነበር። ከዚህ በተጨማሪ ሄኖክ አዱኛ ከመዓዝን መሬት ለመሬት ወደ ሳጥን አሻግሮት ቢኒያም አብርሃ በድንቅ ሁኔታ ከመታው በኋላ ሞይስ ፓይቴ በግሩም ሁኔታ የመለሰው ኳስም ሌላ ሸገር ከተማን መሪ ለማድረግ የተቃረበ ሙከራ ነበር።

አጋማሹን በጥሩ መነቃቃት ቢጀምሩም የኋላ ኋላ የተቀዛቀዙት ዐፄዎቹም 70ኛው ደቂቃ ላይ አቤኔዘር ዩሐንስን በቀይ ካርድ ካጡ በኋላ የተቀረውን የጨዋታ ክፍለጊዜ ወደ መከላከሉ ለማመዘን ተገደዋል። በጨዋታው መገባደጃ ደቂቃዎች የቁጥር ብልጫ የነበራቸው ሸገሮች ግብ ለማስቆጠር ጥረት ቢያደርጉም ጨዋታው ግብ ሳይቆጠርበት ነጥብ በማጋራት ተቋጭቷል።
ሀዲያ ሆሳዕና ከ ሽረ ምድረገነት
የዕለቱ ሁለተኛው ጨዋታ በመጀመሪያው አጋማሽ ላይ ቡድኖቹ ተቀራራቢ የኳስ ቁጥጥር ድርሻ የወሰዱበት እንዲሁም ጥሩ ፉክክር የተደረገበት ነበር። ፈጣን የማጥቃት እንቅሰቃሴ በማድረግ ጨዋታውን የጀመሩትም ሽረ ምድረ ገነቶች ናቸው። ተካልኝ ደጀኔ ከግራ መስመር አሻግሮት ዳንኤል ዳርጌ የሀድያ ሆሳዕና ተከላካዮች መዘናጋት ተጠቅሞ ብቻውን ሆኖ አግኝቶት ወደ ግብነት ያልቀየረው ዕድልም የጨዋታው ለግብ የቀረበ ቀዳሚ ሙከራ ነበር። ከደቂቃዎች በኋላም ኢዮብ አለማየሁ ከመስመር ይዞት የገባውን ኳስ መቶ ግብ ጠባቂው የመለሰው ሙከራ በነብሮቹ በኩል ይጠቀሳል።
በ12 ኛው ደቂቃ ላይም ሽረ ምድረ ገነቶች ጨዋታውን መምራት የጀመሩ ሲሆን ተካልኝ ደጀኔ ከግራ መስመር ሆኖ ወደ ሳጥን አሻምቷት በቀጥታ መረቡ ላይ ያረፈችው ኳስም ቡድኑን መሪ ማድረግ ችላለች። በሂደቱም የግብ ጠባቂው ትኩረት ማነስ አስተዋፅዖ አድርጓል። ከግቡ መቆጠር በኋላ የተሻለ ጫና የፈጠሩት ሀድያ ሆሳዕናዎችም 45ኛው ደቂቃ ላይ ጥረታቸው ፍሬ አፍርቶ የአቻነት ግብ ማስቆጠር ችለዋል። ፀጋአብ ዩሐንስ ሳጥን ውስጥ ኢዮብ አለማየሁ ላይ የሰራውን ጥፋት ተከትሎ የተሰጠውን ፍፁም ቅጣት ምት ብሩክ በየነ ወደ ግብነት በመቀየር ነበር ቡድኑን አቻ ማድረግ የቻለው።

በሙከራዎች የታጀበ ጥሩ እንቅስቃሴ ያስመለከትው ሁለተኛው አጋማሽ ማራኪ ሳቢ የተደረገበት ነበር። በአጋማሹ የተጫዋች ለውጥ በማድረግ ተጠናክረው የገቡት ሀድያ ሆሳዕናዎች ሲሆኑ አጋማሹ በተጀመረ በአምስት ደቂቃ ውስጥም መሪ መሆን ችለዋል። ተቀይሮ የገባው ተመስገን ብርሃኑ ከግራ መስመር ወደ ሳጥን አሻግሯት ኤልያስ አህመድ ከመረብ ጋር ያዋሀዳት ኳስም ነብሮቹን መሪ ያደረገች ግን ነች።
በቀሩት ደቂቃዎች ከመመራት ተነስተው መሪነቱን የተረከቡት ነብሮቹ ወደ ኋላ አፈግፍገው በመልሶ ማጥቃቶች ዕድሎችን ለመፍጠር ጥረት ሲያደርጉ ሽረዎች በአንፃሩ የአቻነት ግብ ፍለጋ ጫና ፈጥረው ተንቀሳቅሰዋል። 58ኛው ደቂቃ ላይ ዳንኤል ዳርጌ አሻምቷት ሽመክት ጉግሳ በግንባሩ ከገጫት በኋላ ግብ ጠባቂው እንደ ምንም ያወጣት ኳስም እጅግ ሽረዎችን አቻ ለማድረግ የተቃረበች ሙከራ ነበረች።
ጨዋታው ወደ መጠናቀቂያው ሲቃረብ የመልሶ ማጥቃት አጋጣሚ ያገኙት ሀድያ ሆሳዕናዎች በጭማሪ ደቂቃው የግብ ልዩነቱን ያሰፉበት ግብ ማስቆጠር ችለዋል። ግቧ ተቀይረው የገቡት ታዳጊዎቹ በፈጠሩት ጥምረት የተቆጠረች ስትሆን አጥቂው ታሪኩ ፀደቀ አሻግሯት ሱራፌል ተመስገን ከሳጥን ውጭ አክርሮ በማስቆጠር የቡድኑ መሪነት በማስፋት ጨዋታው በሀድያ ሆሳዕና 3 ለ 1 አሸናፊነት ተጠናቋል።

