17ኛው ሳምንት የሲቢኢ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ዛሬ በሚካሄዱ ሦስት ጨዋታዎች ፍፃሜውን ያገኛል፤ ጨዋታዎቹን የተመለከቱ መረጃዎችም እንደሚከተለው አቅርበንላችኋል።

ነገሌ አርሲ ከ ሲዳማ ቡና
አራት ተከታታይ ድሎች ከተቀዳጁ በኋላ ከወላይታ ድቻ ጋር ነጥብ ተጋርተው በሀዋሳ ከተማ ሽንፈት ያስተናገዱት በ26 ነጥብ 6ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጡት ነገሌ አርሲዎች ከሁለት ጨዋታዎች በኋላ ዳግም ወደ ድል መንገድ ለመመለስ ሲዳማ ቡናን ይገጥማሉ። ከአስደናቂው ግስጋሴ በኋላ መጠነኛ መቀዛቀዝ የታየባቸው ሰጎኖቹ ነጥብ በጣሉባቸው ጨዋታዎች ላይ በወትሮው ብቃቱ ያልነበረውን የፊት መስመራቸውን ማሻሻል ይጠበቅባቸዋል። ሰጎኖቹ ምንም እንኳን በመጨረሻው ጨዋታ ሁለተኛው አጋማሽ ላይ የተሻለ ጫና መፍጠር ቢችሉም የዛሬው ተጋጣሚያቸው ከመጨረሻዎቹ አምስት ጨዋታዎች በአራቱ መረቡን አስከብሮ የወጣ ጠንካራ የተከላካይ ክፍል ያለው ቡድን እንደመሆኑ ለሚጠብቃቸው ፈተና በሚገባ መዘጋጀት ይኖርባቸዋል።
በ 33 ነጥቦች ሊጉን በመምራት ላይ የሚገኙት ሲዳማ ቡናዎች ሁለተኛ ተከታታይ ድላቸውን አስመዝግበው መሪነታቸውን ለማደላደል ከሰጎኖቹ ጋር ይፋለማሉ። ከአርባ ምንጭ ከተማ እና አዳማ ከተማ ጋር ባደረጓቸው ሁለት ጨዋታዎች ላይ ተከታታይ የአቻ ውጤቶች ካስመዘገቡ በኋላ ኢትዮጵያ ቡናን ሦስት ለባዶ በማሸነፍ ወደ ድል የተመለሱት ሲዳማ ቡናዎች በተመሳሳይ ሀያ ዘጠኝ ነጥብ ሰብስበው 2ኛ ደረጃ ላይ ከተቀመጡ ሦስት ክለቦች ያላቸውን የነጥብ ልዩነት ወደ ሰባት ከፍ ለመድረግ ዛሬ ወሳኝ ጨዋታ ያደርጋሉ። በቅርብ ሳምንታት በመልሶ ማጥቃት ዕድሎችን ለመፍጠር የሚጥር ውጤታማ የማጥቃት አጨዋወት የገነቡት አሰልጣኝ ያሬድ ገመቹ በዛሬው ዕለት በአምስት መርሐ ግብሮች ዘጠኝ ግቦችን ያስቆጠረው የፊት መስመራቸው ውጤታማ አካሄድ ማስቀጠል ቀዳሚ ስራቸው እንደሚሆን ይታመናል።
ነገሌ አርሲዎች ከአብዱልባሲጥ ከማል ውጭ በጉዳትም ሆነ በቅጣት የሚያጡት ተጫዋች የለም። በሲዳማ ቡና በኩል በመጨረሻው ጨዋታ ተጎድቶ ከሜዳ የወጣው ደግፌ አለሙ እና መጠነኛ ጉዳት አስተናግዶ የነበረው ብርሃኑ በቀለ ለዛሬው ጨዋታ ዝግጁ ሲሆኑ የሬድዋን ናስር የመሰለፍ ጉዳይ ግን አጠራጣሪ ነው።
ሁለቱ ቡድኖች ዛሬ በታሪካቸው የመጀመሪያ የሊግ ጨዋታ ያደርጋሉ።
ሸገር ከተማ ከ ድሬዳዋ ከተማ
በአስራ ስድስት ነጥቦች 17ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጡት ሸገር ከተማዎች ከስምንት የጨዋታ ሳምንታት በኋላ ወደ ድል ለመመለስ ብርቱካናማዎቹን ይገጥማሉ። በዘጠነኛው ሳምንት ባህርዳር ከተማን ሦስት ለአንድ ካሸነፉ ወዲህ
ሦስት ነጥብ ማሳካት ያልቻሉት ሸገር ከተማዎች በመደዳ ከገጠሟቸው አራት ሽንፈቶች በኋላ ባደረጓቸው አራት ጨዋታዎች ተከታታይ የአቻ ውጤቶች በማስመዝገብ ከሽንፈት ቢርቁም አሁንም ከአደጋው ክልል መውጣት አልቻሉም። በዛሬው ጨዋታ ድል አድርጎ የደረጃ መሻሻል ለማግኘትም
በመጨረሻዎቹ አምስት መርሐ ግብሮች ላይ ሁለት ግቦችን ብቻ ያስቆጠረው የፊት መስመራቸውን ማሻሻል ግድ ይላቸዋል።
በአስራ ዘጠኝ ነጥቦች 13ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጡት ድሬዳዋ ከተማዎች ከድል አልባው የአምስት ጨዋታዎች ጉዞ ለመውጣት ወደ ሜዳ ይቀርባሉ። በመጨረሻዎቹ አምስት መርሐ ግብሮች ሁለት ሽንፈቶችና ሦስት የአቻ ውጤቶች ያስመዘገቡት ብርቱካናማዎቹ ዳግም ወደ ድል መንገድ ለመመለስ ዘርፈ ብዙ ለውጦች ማድረግ ይጠበቅባቸዋል። በተለይም በመጨረሻዎቹ አምስት ጨዋታዎች ኳስና መረብ ማገናኘት ያልቻለው የማጥቃት አጨዋወታቸው አንገብጋቢ መፍትሔ ይሻል። ቡድኑ በመጨረሻው ጨዋታ ሁለተኛው አጋማሽ ላይ መጠነኛ መሻሻል ማሳየት ቢችልም የግብ ዕድሎችን በመፍጠር ረገድ ያለበትን ውስንነት መቅረፍ ይኖርበታል።
ሁለቱ ቡድኖች ዛሬ በታሪካቸው የመጀመሪያ የሊግ ጨዋታ ያደርጋሉ።
ኢትዮጵያ ቡና ከ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ
በአስራ ዘጠኝ ነጥቦች 12ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጡት
ኢትዮጵያ ቡናዎች ከሁለት ጨዋታዎች በኋላ ወደ ድል ተመልሰው ደረጃቸውን ለማሻሻል ወደ ጨዋታው ይቀርባሉ። በመጨረሻው መርሐ ግብር በሲዳማ ቡና የሦስት ለባዶ ሽንፈት የደረሰባቸው ቡናማዎቹ በጨዋታው ያሳዩት እንቅስቃሴ ለክፉ የሚሰጥ ባይሆንም በቆመ ኳስ መከላከል ረገድ በነበራቸው ድክመት ሁለት ግቦች አስተናግደው ለሽንፈት ተዳርገዋል። በመጨረሻዎቹ አምስት ጨዋታዎች ሁለት ሁለት ድል እና ሽንፈት በእኩሌታ እንዲሁም አንድ የአቻ ውጤት ያስመዘገበው ቡድኑ ከዚህ ወጥነት የጎደለው አካሄድ ለመውጣት በተጠቀሱት መርሐ ግብሮች ሰባት ግቦችን ያስተናገደው የመከላከል አደረጃጀቱ ማሻሻል ይኖርበታል።
በአስራ ሰባት ነጥቦች 15ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጡት የኢትዮጵያ ንግድ ባንኮች ካሉበት የስጋት ቀጠና ለመውጣት በሁለት ነጥቦች ልቀው 12ኛ ደረጃ ላይ ከተቀመጡት ቡናማዎቹ ይፋለማሉ። ከአምስት ሽንፈት አልባ ጨዋታዎች በኋላ በኢትዮ ኤሌክትሪክ እና አዳማ ከተማ ተከታታይ ሽንፈቶች የገጠማቸው ኢትዮጵያ ንግድ ባንኮች በ12ኛው ሳምንት ኢትዮጵያ መድንን ካሸነፉ ወዲህ ባለፉት አራት ጨዋታዎች ድል ማድረግ አልቻሉም። በመጨረሻዎቹ አራት መርሐ ግብሮች ማግኘት ከሚገባው አስራ ሁለት ነጥብ አስሩን ጥሎ ሁለቱን ብቻ ያሳካው ቡድኑ ከዚህ አካሄዱ ለመውጣት በተጠቀሱት ጨዋታዎች ስድስት ግቦችን ያስተናገደው የመከላከል ውቅራቸው ማሻሻል ግድ ይላቸዋል።
በኢትዮጵያ ቡና በኩል ያለው ዜና ለማግኘት ያደረግነው ጥረት አልተሳካም፤ የኢትዮጵያ ንግድ ባንኮች ጉዳት ላይ የነበሩት ካሌብ አማንክዋህ እና እንዳለ ዮሐንስ ወደ ልምምድ መመለሳቸውን ተከትሎ በዛሬው ጨዋታ ከጉዳትም ሆነ ከቅጣት ነፃ የሆነ ስብስብ ይዘው ይቀርባሉ።
ሁለቱ ቡድኖች በሊጉ 38 ጊዜ ተገናኝተው ቡና 19 ጨዋታ በማሸነፍ የበላይነት ይዟል። ባንክ 9 ሲያሸንፍ በቀሪው 10 ጨዋታ አቻ ተለያይተዋል። ቡና 59 ጎሎች ፣ ባንክ 41 ጎሎችን ማስቆጠርም ችለዋል።

