ግዙፉ አማካይ አዲስ ክለብ ለማግኘት ተቃርቧል

ግዙፉ አማካይ አዲስ ክለብ ለማግኘት ተቃርቧል

ኢትዮጵያዊው አማካይ ወደ ሳውዲ አረብያ ሊግ ሊያመራ ነው

 

በኢትዮጵያ ቡና መለያ ከኢትዮጵያ እግር ኳስ ጋር የተዋወቀው አንድ ሜትር ከዘጠና ሴንቲ ሜትር የሚረዝመው ግዙፍ የተከላካይ አማካይ ስፍራ ተሰላፊ ጋቶች ፓኖም ባለፈው ዓመት ኢትዮጵያ መድንን ለቆ በኢራቅ ስታርስ ሊግ ለሚሳተፈው ኒው ሮዝ ፊርማውን አስቀምጦ በክለቡ ጥቂት ጊዜያት ካሳለፈ በኋላ በሐምሌ ወር ወደ ሌላኛው የሊጉ ክለብ አል ናጃፍ ማምራቱ ይታወሳል።

ከኢራቁ ክለብ ጋር በግሉ ጥሩ ቆይታ ያደረገው ጋቶች ከክፍያ አፈፃፀም ጋር በተያያዘ ከአል ናጃፍ ጋር መለያየቱ እርግጥ ሲሆን ከቀናት በፊት ወደ ሀገር ቤት ተመልሶ ጥቂት ቆይታ ካደረገ በኋለም ወደ ሌላ ክለብ ለማምራት ከትናንት በስትያ ወደ ሳውዲ አረብያ አቅንቷል። ሶከር ኢትዮጵያ ለጉዳዩ ቅርበት ካላቸው ምንጮች እንዳገኘችው መረጃ ከሆነ ተጫዋቹ በሳውዲ አረቢያ ሁለተኛ ዲቪዚዮን ለሚሳተፍ ክለብ ፊርማውን ያኖራል ተብሎ የሚጠበቅ ሲሆን የውል ዘመኑን እና የክለቡን ስም የዝውውሩን ሂደት ተከታትለን የምናሳውቃቹሁ ይሆናል።

ጋቶች ፓኖም ከዚህ ቀደም በኢትዮጵያ ቡና፣ በሩሲያው አንዚ ማካቻካላ ፣ በግብፅ ክለቦች ኤልጎውና እና ሀራስ ኤል ሁዳድ በሳውዲው አል አንዋር በሀገራችን ፕሪሚየር ሊግ ክለቦችን መቐለ 70 እንደርታ ፣ ወላይታ ድቻ ፣ ቅዱስ ጊዮርጊስ፣ ፋሲል ከነማ እና ኢትዮጵያ መድን መጫወቱ ይታወሳል።