ሪፖርት | ቡናማዎቹ ደረጃቸውን ያሻሻሉበትን ወሳኝ ድል ተጎናጽፈዋል

ሪፖርት | ቡናማዎቹ ደረጃቸውን ያሻሻሉበትን ወሳኝ ድል ተጎናጽፈዋል

በመጨረሻ ቀን አዳማ ላይ በተደረገ ብቸኛ ጨዋታ ቡናማዎቹ ወላይታ ድቻን 1ለ0 በማሸነፍ የመጀመሪያውን ዙር አጠናቀዋል።

ኢትዮጵያ ቡና ከ ወላይታ ድቻ

የጨዋታ ሳምንቱ የመጨረሻ ጨዋታ ኢትዮጵያ ቡናን ከወላይታ ድቻ ያገናኘ ሲሆን ቡናማዎቹ የኳስ ቁጥጥር ብልጫ  በመውሰድ ጨዋታውን ሲጀምሩ የጦና ንቦች ግን ቀዳሚ ለመሆን የቀረቡበት ሁለት ጠንካራ ሙከራ በመጀመሪያዎቹ አስር ደቂቃዎች አድርገዋል። ገና በሦስተኛው ደቂቃ ከተከላካይ ጀርባ የጣለውን ኳስ ቴዎድሮስ ኃይለማርያም አግኝቶ እየገፋ የሳጥኑ ጠርዝ ላይ ደርሶ በግቡ አግዳሚ ታኮ ሲያልፍበት 9ኛው ደቂቃ ላይ ብሩክ ኤልያስ ሳጥን ውስጥ የቡናማዎቹን ተከላካዮች አሸንፎ ከሳጥኑ ውጪ ለነበረው ቴዎድሮስ ታፈሰ አሻግሮት መሬት ለመሬት መትቶ ለጥቂት ከቋሚ ብረት ርቆ ባያልፍባቸው መሪ ሊያደርጋቸው የተቃረበ ሌላኛው ሙከራ ነበር።

ቡድኖቹ እየተፈራረቁ የጨዋታ ብልጫ በወሰዱበት በአጋማሹ ቡናማዎቹ መሪ መሆን የቻሉበትን ግብ መረብ ላይ በማሳረፍ ቀዳሚ ሆነዋል። 14ኛው ደቂቃ አቡበከር አዳሙ ያሾለካትን ኳስ ያገኘው ኤርሚያስ ሹምበዛ መሬት ለመሬት ብዙም ጠንካራ ያልሆነችውን ያሻገራት ኳስ ቢኒያም ገነቱ በቀላሉ ተቆጣጠራት ተብላ ስትጠበቅ የኳሷ አቅጣጫ ተቀይሮ መረብ ላይ አርፋ ቡናማዎቹን መሪ ማድረግ ችላለች። ከግቧ መቆጠር በኋላ አንፃራዊ የኳስ ቁጥጥር ብልጫ ወስደው በጫና የአቻነት ግብ ፍለጋቸውን የቀጠሉት የጦና ንቦች ሲሆኑ የተቃራኒ ቡድን ሜዳ ክፍል ላይ ደርሰው የሚያደርጉት ሙከራ አስቆጪ ከመሆን ባሻገር ኢላማውን የጠበቀ ሳይሆን ቀርቶ አጋማሹ ተገባዷል።

በሁለተኛ ጨዋታ ምዕራፍ ጨዋታው ተመልሶ የጦና ንቦች የአቻነት ግብ ፍለጋ በሚሄዱበት ጊዜ ቡናማዎቹ በመልሶ ማጥቃት ኳስ ይዘው በሚገቡበት ቅፅበት የጦና ንቦቹ ተከላካይ መልካሙ ቦጋለ አቡበከር አዳሙ ላይ በሰራው ጥፋት የእለቱ ዋና ዳኛ ለተጫዋቹ ቀጥታ ቀይ ካርድ ካሳዩ በኋላ በአነጋጋሪ ሁኔታ ከረዳቶቻቸው ጋር ተመካክረው ቀዩ ካርዱን የሻሩበት የ49ኛ ደቂቃ ክስተት ሲጠቀስ ቅጣት ምቱን አቡበከር አዳሙ መትቶ ቢኒያም ገነቱ እንዴትም አግዶባቸዋል።

የጦና ንቦች የኳስ የበላይነት እየተመለከትን በቀጠለው በጨዋታው በረከት ያሉ ኳሶችን ይዘው ሳጥን ውስጥ ይዘው ገብተው አደጋ መፈጠር ችለው የነበሩ ሲሆነ በተለይም በፍቃዱ ሕዝቅኤል የቆመ ኳስ አሻምቶ መሳይ ኒኮል በግንባሩ ገጭቶ ያደረገውን ሙከራ ዳንላድ ኢብራሂም እንዴትም የመለሰባቸው አጋጣሚ ይጠቀሳል። ቡናማዎቹ ውጤት አስጠብቀው ለመውጣት ወደኋላ ያፈገፈጉበትን እንቅስቃሴ ያደረጉ ሲሆን ጨዋታው ኃይል በበዛ አጨዋወት እየተቆራረጠ ሊደረግ ተገዶ 82ኛው ደቂቃ ላይ ሲደርስ ሁለት ተጫዋቾች ከሁለቱም ቡድን በቀይ ካርድ ከሜዳ የወጡበት ክስተት ይታወሳል። የጦና ንቦች ጫና የበረታበት ጨዋታም በመጀመሪያ አጋማሽ በተቆጠረች ብቸኛ ግብ ለቡናማዎቹ ሦስት ነጥብ በማጎናፀፍ ተጠናቋል።