ሪፖርት | ወላይታ ድቻ እና ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ድል ቀንቷቸዋል

ሪፖርት | ወላይታ ድቻ እና ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ድል ቀንቷቸዋል

ሰባት ግቦች በተቆጠሩበት ጨዋታ የጦና ንቦች ሁለት ለባዶ ከመመራት ተነስተው መቻልን 4 ለ 3 ሲያሸንፉ ንግድ ባንኮች በበኩላቸው ፋሲል ከነማን 3-1 አሸንፈዋል

ወላይታ ድቻ ከ መቻል

የሲቢኢ ኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የሁለተኛ ዙር ውድድር ከቀናት ዕረፍት በኋላ በዛሬው ዕለት ጅማሮውን አድርጓል። ወላይታ ድቻን እና መቻል ብርቱ ፉክክር ያደረጉበት ጨዋታም በመጀመሪያዎቹ ደቂቃዎች ነበር ግብ ያስመለከተን። ቸርነት ጉግሳ 2ኛው ደቂቃ ላይ በረከት ደስታ ወደ ሳጥን ይዞ ገብቶ የመታውን እና ግብ ጠባቂው የመለሰውን ኳስ ተጠቅሞ ወደ ግብነት የቀየረው ኳስም ቡድኑን በጊዜ መሪ ማድረግ ችሏል።

በአጋማሹ መቻል ከተጋጣሚው አንፃር የተሻለ እንቅስቃሴ ሲያደርግ ከቆየ በኋላም ተጨማሪ ግብ ማስቆጠር ችሏል፤ 39ኛው ደቂቃ ላይ ለመጀመሪያው ግብ መነሻ የሆነው በረከት ደስታ እንደ መጀመሪያው ግብ በተመሳሳይ መንገድ ወደ ሳጥን በመግባት በጥሩ አጨራረስ ግብ አስቆጥሮ መሪነቱም ወደ ሁለት ከፍ ማድረግ ችሏል። ወላይታ ድቻዎች በካርሎስ ዳምጠው የግንባር ሙከራ መቻሎች ደግሞ የዳኛው ፊሽካ በሚጠበቅበት ሰዓት መናፍ ኢሞሮ ከርቀት አክርሮ መቶት የግቡን አግዳሚ ገጭቶ በተመለሰ አጋጣሚ ግብ ለማግኘት ተቃርበው ነበር።

ከዕረፍት መልስ የተጫዋች ቅያሪዎችን በማድረግ ራሳቸውን አጠናክረው የተመለሱት ወላይታ ድቻዎች ውጤታማ ለውጥ ስለ ማድረጋቸው ምስክር የሆነ ግብ ወዲያውኑ አስቆጥረዋል። 47ኛው ደቂቃ ላይ ተቀይሮ የገባው ዮናታን ኤልያስ ከ ቴዎድሮስ ሀ/ማርያም ጋር በጥሩ ቅብብል ያገኘውን ኳስ ሳጥን ውስጥ መቶ በማስቆጠር ቡድኑ ነፍስ እንዲዘራም አድርጓል።

እጅግ ጫናዎችን ፈጥረው መጫወታቸውን የቀጠሉት ወላይታ ድቻዎች 52 ኛው ደቂቃ ላይ ናትናኤል ናሴሮ ከራሱ የግብ ክልል በጥሩ ሁኔታ እየገፋ ይዞ በመግባት በአንድ ሁለት ቅብብል በተጋጣሚ የግብ ክልል ደርሶ ያሻገረውን ኳስ ቴዎድሮስ ሀ/ማርያም ደገፍ አድርጎ በማስቆጠር የጦና ንቦቹን አቻ ማድረግ ችሏል። ከአቻነት ግቡ በኋላ በልዩ የተነሳሽነት መንፈስ የተጫወቱት ወላይታ ድቻዎች 68ኛው ደቂቃ ኪዳኔ አሰፋ ከሜዳው የቀኝ ክፍል አሻምቶት ዮናታን ኤልያስ ባስቆጠረው ግብ ከመመራት ተነስተው መሪ መሆን ችለዋል።

በሁለተኛው አጋማሽ የሁሉም ረገድ ብልጫ የወሰደው ቡድኑ 81ኛው ደቂቃ ላይ በካርሎስ ዳምጠው አማካኝነት መሪነቱን ያሰፋበትን ግብ ማስቆጠር ችሏል፤ ናትናኤል ናሴሮ በመልሶ ማጥቃት የተፈጠረውን ዕድል ተጠቅሞ መቶት የግቡን አግዳሚ ከመለሰው በኋላ ኳሱን በድጋሚ ያገኘው ካርሎስ ዳምጠው ወደ ግብነት የቀየረው ኳስም የግብ ልዩነቱን አስፍቷል። የጨዋታው መጠናቀቂያ ላይ ብልጫ ወስደው ጫናዎችን የፈጠሩት መቻሎች 90+5 ላይ በቸርነት ጉግሳ አማካኝነት ከመሸነፍ ያላዳናቸውን ግብ አስቆጥረው ጨዋታው 4-3 በሆነ ውጤት ተጠናቋል።

 

ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከ ፋሲል ከነማ

 

በዕለቱ ሁለተኛ ጨዋታ በመጀመሪያ አጋማሽ ፋሲል ከነማዎች የተሻለ እንቅስቃሴ ያደረጉበት ሲሆን ኢላማውን የጠበቀ ሙከራ በማድረግ ረገድ ግን ኢትዮጵያ ንግድ ባንኮች ቀዳሚ ነበሩ። 5ኛው ደቂቃ ላይ ዘላለም አበበ ሳጥን ውስጥ ወደ ግብ መቶት የግቡን አግዳሚ ገጭቶ የተመለሰ ኳስም ኢትዮጵያ ንግድ ባንክን መሪ ለማድረግ የተቃረበ አጋጣሚ ነበር። ከዚህ ሙከራ በኋላም 25ኛው ደቂቃ ሳይመን ፒተር ከሳምሶን ቹቹ የተቀበላትን ኳስ ተጠቅሞ በጥሩ የመጀመሪያ ንክኪ ወደ ግብነት ቀይሮ ቡድኑን መሪ ማድረግ ችሏል። ፋሲል ከተማዎች ግን ኢላማውን የጠበቀ ሙከራ ሳያስመለክቱን አጋማሹ ተጠናቋል።

ሁለተኛው አጋማሽ ሀምራዊ ለባሾቹ የተሻለ እንቅስቃሴ ያደረጉበት ነበር። አጋማሹ ናትናኤል ዳንኤል ካደረገው ሙከራ በስተቀር ይሄ ነው የሚባል የግብ አጋጣሚ ሳያስመለክተን ረዘም ያለ ደቂቃን ከዘለቀ በኋላም ሁዘይፋ ሻፊ 73ኛው ደቂቃ ላይ ናትናኤል ዳንኤል ያቀበለውን ኳስ ተጠቅሞ በጥሩ አጨራረስ ወደ ግብነት በመቀየር ልዩነቱን ማስፋት ችሏል።

በቀሩት ደቂቃዎች ሁለቱም ቡድኖች በፈጣን ሽግግሮች ዕድሎች ለመፍጠር ጥረት ያደረጉበት ሲሆን 90ኛው ደቂቃ ላይም የፋሲል ከነማ ተከላካዮች በአግባቡ ማራቅ ያልቻሉት ኳስ ተጠቅሞ ሳምሶን ቹቹ ከሳጥን ውጭ በጥሩ አጨራረስ ግብ አስቆጥሮ በፋሲል ከነማ የማገገም ተስፋ ላይ ውሃ ቸልሶበታል። ጨዋታው ሊጠናቀቅ የዳኛው ፊሽካ በሚጠበቅበት ሰዓትም ኪሩቤል ዳኘ ከቆመ ኳስ ሞክሮት ግብ ጠባቂው ሲመልሰው ያንኑ የተመለሰውን ኳስ ከዋሳዋ ጂኦፍሪ የተቀበለው ታምራት ኢያሱ ከባዶ ከመሸነፍ የዳኑበትን ግብ አስቆጥሮ ጨዋታው 3-1 በሆነ ውጤት ተጠናቋል።