በዘንድሮ የውድድር ዓመት ዳግም ወደ ቀደመ ክለቡ ተመልሶ የነበረው አቤል ያለው ከአስተዳደራዊ ጉዳዮች ጋር በተያያዘ በገባው ቅራኔ ክለቡን በይፋ መልቀቁ ታውቋል።
በሲቢኢ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የ21 ሳምንታት ጉዞ ፈረሰኞቹ አንድ ቀሪ ጨዋታ እያላቸው 24 ነጥቦችን ሰብስበው በደረጃ ሰንጠረዡ 14ኛ ቦታ ላይ መቀመጣቸው ይታወቃል። ከሳምንታት በፊት ከአጥቂው ቢኒያም ፍቅሬ ጋር በስምምነት የተለያየው ክለቡ ከሰሞኑን ከአቤል ያለው ጋርም ሊለያይ ከጫፍ መድረሱ ሲሰማ የነበረ ሲሆን የዝግጅት ክፍላችን አሁን በደረሳት መረጃ ተጫዋቹ በትናትናው ዕለት መልቀቂያውን ከክለቡ መውሰዱን አረጋግጣለች።

የቀድሞ የደደቢ እንዲሁም በግብፁ ዜድ ክለብ ቆይታ የነበረው አቤል ዘንድሮ 15 ጨዋታዎች ላይ ተሳትፎ 8 ጎሎችን ለክለቡ ያስቆጠረ ሲሆን የሊጉን ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪነት ከአዲስ ግዳይ እና ታምራት እያሱ ጋር በጋራ እየመራ ይገኛል። ከደሞዝ እና ተያያዥ ጉዳዮች ጋር በተያያዘ ቅራኔ ውስጥ ገብቶ የነበረው ተጫዋቹ ከክለቡ ለመልቀቅ ከቀናት በፊት ያስገባው ደብዳቤ በትናንትናው ዕለት ምላሽ አግኝቶ በይፋ ቡድኑን መለያየቱ ታውቋል።
አቤልን ለማስፈረም በአሁኑ ሰዓት በይበልጥ ሁለት የሊጉ ክለቦች ጥረት እያደረጉ እንደሚገኙ ሲሰማ በቀጣዮቹ ቀናትም ተጫዋቹ ማረፊያው ይታወቃል ተብሎ ይገመታል።
ከክለቡ ጋር በተያያዘ ዜና ሌሎች የቡድኑ አባላትም መልቀቂያ እንዲሰጣቸው እየጠየቁ መሆኑን ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።

