ሸገር ከተማ ተቀይረው የገቡ ተጫዋቾች ባስቆጠሯቸው ግቦች ሀድያ ሆሳዕናን 2 ለ 0 ሲያሸንፍ ባህርዳር ከተማ በአንተነህ ተፈራ ሁለት ግቦች ቅዱስ ጊዮርጊስን 2 ለ 0 ረቷል።

ሀድያ ሆሳዕና ከ ሸገር ከተማ
ሀድያ ሆሳዕና ከሸገር ከተማ ያፋለመው የዕለቱ የመጀመሪያ ጨዋታ በመጀመሪያው አጋማሽ ጥራት ያላቸው የግብ ዕድሎችም ሆነ ሙከራዎች ያልተደረጉበት ነበር። በአጋማሹም የተሻለ የኳስ ቁጥጥር ድርሻ በመያዝም ሆነ ሙከራዎች በማድረግ የተሻሉ የነበሩት ሸገር ከተማዎች ሲሆኑ ሄኖክ አዱኛ ከቆመ ኳስ በቀጥታ ሞክሮት ኦዉሱ እንድሪውስ ያዳነው፤ ቢንያም ፍቅሩ በጥሩ መንገድ ወደ ሳጥን ገብቶ መቶት ግብ ጠባቂው የመለሰው እንዲሁም ቡልቻ ሹራ ከሳጥን ውጭ ሞክሮት ለጥቂት የወጣው ሙከራም በአጋማሹ የታዩ ለግብ የቀረቡ ሙከራዎች ናቸው።

ሁለተኛው አጋማሽ በሁለቱም ቡድኖች በኩል በተደረጉ ፈጣን እንቅስቃሴዎች ነበር የጀመረው።
ነብሮቹ ብሩክ በየነ ከሳጥን ውጭ በግሩም ሁኔታ መቶት ባህሩ ነጋሽ በድንቅ ብቃት በመለሰው ወርቃማ አጋጣሚ ግብ ለማስቆጠር ከተቃረቡ ከደቂቃዎች በኋላም ሸገር ከተማዎች መሪ የሆኑበትን ግብ ማስቆጠር ችለዋል። 50ኛ ደቂቃ ላይ ተቀይሮ የገባው አሚር አብዶ ከሌላኛው ተቀይሮ የገባው ሚሊዮን ሀይሉ የተሻገረለትን ኳስ በተረጋጋ ሁኔታ በጥሩ አጨራረስ አስቆጥሮም ሸገር ከተማን መሪ ማድረግ ችሏል።

ከግቡ መቆጠር በኋላም ሙከራዎች በማድረግ ረገድ የተሻሉ የነበሩት ሸገሮች ካሌብ በየነ ከግራ መስመር አሻግሮት ሚሊዮን ሀይሉ ባደረገው ዒላማውን የጠበቀ ሙከራ እንዲሁም አሚር አብዶ ከቢንያም ፍቅሩ የተቀበላትን ኳስ ተጠቅሞ ባደረጋት ሙከራ ግብ ለማስቆጠር ሙከራዎች ካደረጉ በኋላ ጥረታቸው ፍሬ አፍርቶ 68ኛው ደቂቃ ላይ መሪነታቸውን ከፍ ያደረጉበት ግብ ማስቆጠር ችለዋል። ሚሊዮን ሀይሉ የሀድያ ተከላካዮች ኳሷን ከሳጥን ለማራቅ በሰሩት ስህተት ያገኛትን ኳስ በጥሩ መንገድ ተቆጣጥሮ ወደ ግብነት በመቀየር የቡድኑን መሪነት ወደ ሁለት ከፍ ማድረግ ችሏል።
ነብሮቹ አቡሽ ደርቤ ከመስመር አሻምቶት ሱራፌል ተመስገን በግንባር ካደረገው ሙከራ ውጭ የግብ ዕድሎች ያልፈጠሩ ሲሆን ጨዋታውም በሸገር ከተማ 2 ለ 0 አሸናፊነት ተጠናቋል።
ቅዱስ ጊዮርጊስ ከ ባህርዳር ከተማ
ከድል ጋር የተራራቁት ፈረሰኞቹ እና የጣና ሞገዶቹ ያደረጉት ጨዋታ በመጀመሪያው አጋማሽ ፈረሰኞቹ ሙከራዎች በማድረግ እና የኳስ ቁጥጥር ድርሻ በመውሰድ ረገድ ብልጫ የወሰዱበት ነበር።
ሻሂዱ ሙስጠፋ ከግራ መስመር አሻግሮት ግብ ጠባቂው በንቃት ባዳነው አጋጣሚ ሙከራ ማድረግ የጀመሩት ቅዱስ ጊዮርጊሶች ቀጥሎም ፍፁም ጥላሁን ከመስመር አሻምቶት ነፃ የነበረው ሀብታሙ ጉልላት በግንባሩ ገጭቶ ባልተጠቀመበት ዕድል ግብ ለማስቆጠር ጥረት አድርገዋል። ፈረሰኞቹ ከተጠቀሱት ሙከራዎች ውጭም በአጋማሹ ጥሩ እንቅስቃሴ ባደረገው ፍፁም ጥላሁን አማካኝነት ሙከራዎች ማድረግ የቻሉ ሲሆን ተጫዋቹ ከግራ መስመር አክርሮ መቶት ወደ ውጭ የወጣው እንዲሁም ከመዓዝን የተሻገረውን ኳስ ተጠቅሞ በግንባሩ ያደረገው ሙከራም የተሻሉ አጋጣሚዎች ነበሩ።

ከመጀመሪያው አጋማሽ የተለየ መልክ የነበረው ሁለተኛው አጋማሽ ባህርዳር ከተማዎች ተሻሽለው የቀረቡበት ነበር። ቅዱስ ጊዮርጊሶች በመጀመሪያዎቹ ደቂቃዎች ጥዑመልሳን ሃይለሚካኤል ከመዓዝን የተሻገረውን ኳስ ተጠቅሞ ባደረገው አስቆጪ ሙከራ ግብ ለማስቆጠር ቢቃረቡም ግብ በማስቆጠር ቀዳሚ የነበሩት ግን ባህርዳር ከተማዎች ናቸው። በ53ኛው ድቂቃ ላይ ወንድወሰን በለጠ በረዥሙ የተሻገረችው ኳስ በአግባቡ ተቆጣጥሮ አመቻችቷት አንተነህ ተፈራ ከሳጥን ውጭ በግሩም ሁኔታ ያስቆጠራት ግብም የጣና ሞገዶቹን መሪ ማድረግ ችላለች።
ከግቡ መቆጠር በኋላም ጫና መፍጠራቸውን የቀጠሉት ባህርዳር ከተማዎች በ60ኛው ደቂቃ ላይ ወንድወሰን በለጠ በግሩም መንገድ ወደ ሳጥን ገብቶ አሻግሯት አንተነህ ተፈራ ከመረቡ ጋር ባዋሀዳት ኳስ መሪነታቸውን ከፍ ማድረግ ችለዋል።

መሪነታቸውን ያጠናከሩበት ግብ ካስቆጠሩ በኋላም
ዕድሎችን መፍጠራቸው የቀጠሉት ባህርዳሮች ብሩክ ሰሙ በሁለት አጋጣሚዎች ባደረጋቸው ሙከራዎች ግብ ለማስቆጠር ተቃርበው ነበር፤ ተጫዋቹ አማኑኤል ገብረሚካኤል ከቀኝ መስመር ያሻገረለትን ኳስ ተጠቅሞ ከግቡ ቅርብ ርቀት ሆኖ ያደረገው እንዲሁም ከሳጥን ውጭ አክርሮ መቶት ሻኪህሎ ፋርክ ወደ ውጭ ያወጣው ሙከራም የቡድኑን መሪነት ወደ ሦስት ከፍ ለማድረግ የተቃረቡ ነበሩ።
በመጨረሻዎቹ ደቂቃዎችም በቅዱስ ጊዮርጊስ በኩል ጥዑመልሳን ሀይለሚካኤል በረዥሙ ለግቷት በፔፔ ሴይዶ የጊዜ አጠባበቅ ድክመት ለጥቂት ወደ ውጭ የወጣችው ሙከራ እና ፋኑኤል አዳሙ በረዥሙ መቷት የግቡን አግዳሚ ለትማ የተመለሰችው ኳስ፤ በባህርዳር ከተማ በኩል ደግሞ አንተነህ ተፈራ በቅዱስ ጊዮርጊስ ተጫዋች የቅብብል ስህተት አግኝቷት ከፍ አድርጎ ያደረጋት ሙከራ ይጠቀሳሉ። በመጀመርያው አጋማሽ ቅዱስ ጊዮርጊስ በሁለተኛው አጋማሽ ደግሞ ባህርዳር ከተማ ብልጫ የወሰዱበት ጨዋታም በጣና ሞገዶቹ 2 ለ 0 አሸናፊነት ተጠናቋል።

