የ24ኛ ሳምንት ጨዋታዎች ዛሬ ጅማሯቸውን ሲያደርጉ ፋሲል ከነማ ከ ከመቻል ያለ ግብ ሲለያዩ ሲዳማ ቡና መሪነቱን በአምስት ነጥብ ከፍ ያደረገበትን ድል አስመዝግቧል።

ፋሲል ከነማ ከ መቻል
በሙከራ ረገድ ይህ ነው ሚባል ሙከራዎችን ባላስመለከተን አጋማሽ በፋሲል ከነማ በኩል 15ኛው ደቂቃ ላይ አቤነዘር ዮሐንስ በግራ እግሩ ሳጥን ውስጥ መቶት ግብጠባቂው ኦሊዮንዚ ናፊያን በመለሰበት ሙከራ እንዲሁም አጋማሹ ሊጠናቀቅ በተጨመሩ ደቂቃዎች 40+1 ላይ የመቻሉ ቻርለስ ሙሴጌ ሞክሮት ግብጠባቂው ሞየስ ፓዋቲ ሲመልስበት የተመለሰውን ኳስ ዓለምብርሃን ይግዛው በግንባሩ ደግሞ ቢሞክርም በሞየስ ፓዋቲ ጥረት ግብ ከመሆን ታድጓቸዋል።

ከዕረፍት መልስ ሁለተኛው አጋማሽ ላይ ፈጣን አጥቂዎቻቸውን ኢላማ ያደረገ የማጥቃት ሙከራዎችን ሲያደርጉ የነበሩት መቻሎች 79ኛው ደቂቃ ላይ ቀይረው ባስገቡት ኮሊንስ ኮፊ አማካኝነት ከሳጥን ውጭ ጥሩ ለግብ የቀረበ ሙከራ ማድረግ ቢችልም በግብ ጠባቂው አማካኝነት ኳሷን ግብ ጎል ከመሆን ታድጓታል። ጨዋታውም ተጨማሪ የግብ ሙከራዎችን እንዲሁም ግቦችን ሳያስመለክተን ጨዋታው 0-0 በሆነ ውጤት ተጠናቋል።
ሲዳማ ቡና ከ ምድረ ገነት ሽረ
በኳስ ቁጥጥሩ ረገድ ሲዳማ ቡናዎች ከፍተኛ ባለድርሻ በነበሩበት በመጀመሪያው አጋማሽ በእንቅስቃሴ ተሽለው ወደ ተጋጣሚ ግብ ክልል በተደጋጋሚ በመድረስ ተጠግተው መጫወት የቻሉ ቢሆንም ነገር ግን በሁለቱም ቡድኖች በኩል ይሄ ነው የሚባል የግብ ሙከራን እንዲሁም በአጋማሹ ምንም ኢላማውን የጠበቀ ሙከራ ሳንመለከት ወደ መልበሻ ክፍል አምርተዋል።

ሁለተኛው አጋማሽ ላይ የሲዳማ ከሲዳማ ቡና ተጫዋቾች ስህተቶችን በመፈለግ በመልሶ ማጥቃት ግቦችን ለማግኘት ጥረት ያደረጉት ምድረ ገነት ሽረዎች 69ኛው ደቂቃ ላይ ተቀይሮ የገባው አቤል ማሙሽ ያቀበለውን ኳስ ዳንኤል ዳርጌ ከሳጥን ውጭ በሃፍ ቮሊ ሞክሮ ግብ ጠባቂው መስፍን ሙዜ መልሶበታል።

ሲዳማ ቡናዎች ከ73 ደቂቃዎች ትዕግስት በኃላ ከግራ መስመር ፍራኦል መንግስቱ ያሻገረውን ኳስ ብርሃኑ በቀለ በግንባሩ በመግጨት ግብ አስቆጥሮ ቡድኑን መሪ ማድረግ ችሏል።
ምድረ ገነት ሸረዎች በቁጥር በዛ ብለው ያቻነት ግብ ለማግኘት በወጡበት ሰዓት ሲዳማ ቡናዎች በመልሶ ማጥቃት እንደ መጀመሪያው ግብ ሁሉ ፍራኦል መንግስቱ ከሜዳው የግራ ክፍል ያሻማውን ኳስ ደስታ ደሙ ወደ ግብ ሞክሮት ግብ ጠባቂው የመለሰበትን ኳስ በድጋሚ ያገኘው አቤል ያለው ወደ ግብነት ቀይሮ ቡድኑን አሸናፊነት ማፅናት ችሏል። ይህንንም ተከትሎ ሲዳማ ቡናዎች 2-0 በማሸነፍ መሪነቱን አጠናክሯል።

