24ኛ ሳምንት ዛሬም በ2ኛ ቀን ጨዋታዎች ይቀጥላል፤ ጨዋታዎቹን የተመለከቱ መረጃዎችም እንደሚከተለው አሰናድተንላችኋል

አርባምንጭ ከተማ ከ ኢትዮጵያ መድን
በ19 ነጥብ በደረጃ ሰንጠረዡ ግርጌ ላይ የሚገኘው አርባምንጭ ከተማ ካለበት የመጨረሻ ደርጃ ለመውጣትና ከወራጅ ቀጠናው ለመራቅ የሚያደርገውን ተስፋ ሰጪ ጉዞ ዛሬም ለመቀጠል ይፋለማል። ቡድኑ ባለፉት አምስት ጨዋታዎች በሁለቱ ድል ቀንቶት በአንዱ ሽንፈት አስተናግዶ በሁለቱ ደግሞ አቻ መውጣት ችሏል። በተለይም በመጨረሻው ጨዋታ አዳማ ከተማን 2 ለ 0 በሆነ ውጤት ማሸነፉ ለዛሬው ጨዋታ የላቀ ስነ-ልቦናዊ ጥንካሬ ይዞ እንዲቀርብ ያደርገዋል። አዞዎቹ ካለባቸው 11 የጎል ዕዳ ተላቀውና የተከላካይ ክፍላቸውን ይበልጥ አጠናክረው ከአደጋው ክልል ለመውጣት ዛሬም የሦስት ነጥብ ግዴታ ይኖርባቸዋል።
በ25 ነጥብ 16ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጠው ኢትዮጵያ መድን ካለፉት አምስት ጨዋታዎች ውስጥ ሦስቱን በአቻ ውጤት ማጠናቀቁ በደረጃ ሰንጠረዡ ላይ ወደ ላይ እንዳይራመድ እንቅፋት ሆኖበታል። በመጨረሻው የሊግ መርሐ-ግብሩ ከሀዲያ ሆሳዕና ጋር 1 ለ 1 ተለያይቶ ነጥብ የተጋራው መድን ካለፉት ስድስት ጨዋታዎች ማግኘት ከሚገባው 18 ነጥብ ውስጥ 7 ነጥብ ብቻ ነው ማሳካት የቻለው። ቡድኑ የፊት መስመሩን ውጤታማነት በማሳደግና ባለፉት ጨዋታዎች የሚታይበትን የጎል ማግባት ችግር በመቅረፍ ዛሬ የሚያገኘው ድል ወደ 11ኛ ደረጃ ከፍ ሊያደርገው ስለሚችል ከሽንፈት በራቀው ጥንካሬው ተጠቅሞ ለሦስት ነጥብ ወደ ሜዳ ይገባል።
በኢትዮጵያ መድን ለረጅም ጊዜ ጉዳት ላይ የነበሩት ዋንጫ ቱት እና ረመዳን ሁሴን ዛሬም ከቡድኑ ጋር የማይኖሩ ተጫዋቾች ናቸው። አርባምንጭ ከተማ አበበ ጥላሁን ከቅጣት መልስ ቢያገኝም ልምምድ ላይ ባጋጠመው ጉዳት ከዛሬው ጨዋታ ውጭ ሆኗል።
ሁለቱ ቡድኖች ከዚህ ቀደም 9 ጊዜ ተገናኝተዋል፤ ስድስት ጨዋታዎች በአቻ ውጤት ሲጠናቀቁ ኢትዮጵያ መድን ሶስት ጊዜ ድል አድርጓል።
ወልዋሎ ዓ/ዩ ከ ድሬዳዋ ከተማ
በ25 ነጥብ 18ኛ ደረጃ ላይ የሚገኘው ወልዋሎ ባለፉት አምስት ጨዋታዎች ሽንፈት ሳያስተናግድ በመጓዝ አስደናቂ ጥንካሬ እያሳየ ይገኛል። ከእነዚህ አምስት መርሃ-ግብሮች ውስጥ በሁለቱ ድል ቀንቶት በሦስቱ ደግሞ ነጥብ ተጋርቶ የወጣው ቡድኑ በተለይም በመጨረሻው ጨዋታ ጠንካራውን መቻልን ያለ ጎል አቻ በመያዝ የተከላካይ ክፍሉን መሻሻል አሳይቷል። በሊጉ ግርጌ ከሚገኙት ቡድኖች መካከል የተሻለ ወቅታዊ አቋም ላይ የሚገኘው ወልዋሎ ዛሬ የሚያገኘው ድል ከወራጅ ቀጠናው ወጥቶ እስከ 12ኛ ደረጃ ድረስ ከፍ እንዲል ዕድል ይሰጠዋል። ቡድኑ ባለፉት አምስት ጨዋታዎች ያስቆጠራቸው አራት ጎሎች ለድል ቢበቁትም ይበልጥ በራስ መተማመን ለመጫወት የማጥቃት መስመሩን ውጤታማነት ማሳደግ ይጠበቅበታል።
በ28 ነጥብ 12ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጠው ድሬዳዋ ከተማ በውድድር ዓመቱ የሚስተዋልበትን የወጥነት ችግር ለመቅረፍ ወደ ሜዳ ይገባል። በመጨረሻው ጨዋታ በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ 2 ለ 1 በሆነ ውጤት ተሸንፎ ነጥብ የጣለው ድሬዳዋ ባለፉት አምስት ጨዋታዎች ማግኘት ከሚገባው 15 ነጥብ ማሳካት የቻለው 5 ነጥብ ብቻ ነው። ቡድኑ የደረጃ ሰንጠረዡን አጋማሽ ተሻግሮ ወደ አናት ለመጠጋት ዛሬ የግድ ማሸነፍ ይኖርበታል። በተለይም በየጨዋታው ጎል የማስተናገድ ችግር ያለበት የተከላካይ ክፍሉ ግስጋሴ ላይ ያለውን የወልዋሎን የማጥቃት መስመር ለመግታት ብርቱ ጥንቃቄ ማድረግ ይኖርበታል።
ወልዋሎዎች ኤፍሬም ሃይለማርያምን በጉዳት ምክንያት አያሰልፉም፤ ጉዳት ላይ የነበረው ያሬድ ከበድ እንዲሁም ቅጣት ላይ የነበረው ኪሩቤል ወንድሙን ጨምሮ በዝውውር መስኮቱ አጋማሽ ቡድኑን የተቀላቀሉ ተጫዋቾች ግን ለዛሬው ጨዋታ ዝግጁ ናቸው። ድሬዳዋ ከተማ ሬድዋን ሸረፋን በጉዳት ድልአዲስ ገብሬን ደግሞ በቅጣት ዛሬ አያገኝም።
ሁለቱ ቡድኖች በሊጉ እስካሁን ባደረጓቸው 7 ጨዋታዎች ድሬዳዋ ከተማ ሦስቱን በማሸነፍ የበላይ ሲሆን በ3 ጨዋታዎች አቻ ተለያይተው ወልዋሎ 1 ጊዜ ብቻ አሸንፏል። በአምስቱ ግንኙነቶች ድሬዳዋ 8 ፣ ወልዋሎ 5 ጎሎች አስቆጥረዋል።
ኢትዮጵያ ቡና ከ አዳማ ከተማ
ኢትዮጵያ ቡና ወደ ሜዳ የሚገባው ካለፉት አምስት ጨዋታዎች በሦስቱ ድል ቀንቶት በመልካም መነሳሳት ቢሆንም በመጨረሻው ሳምንት በኢትዮ ኤሌክትሪክ ከደረሰበት ሽንፈት ለማገገም ብርቱ ፍልሚያ ማድረግ ይጠበቅበታል። በአሁኑ ወቅት በ29 ነጥብ 10ኛ ደረጃ ላይ የሚገኘው ቡድኑ በሊጉ ካደረጋቸው 22 ጨዋታዎች 20 ግቦችን አስቆጥሮ 22 ግቦችን አስተናግዷል፤ የተከላካይ ክፍሉም ዛሬ ከአዳማ ከተማ ፈጣን አጥቂዎች የሚሰነዘርበትን ጫና ተቋቁሞ የኳስ ቁጥጥር ብልጫውን ወደ ግብ መቀየር ከቻለ ደረጃውን ለማሻሻል ትልቅ ዕድል ይኖረዋል።
አዳማ ከተማ በበኩሉ በ33 ነጥብ 7ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጦ ጨዋታውን የሚጀምር ሲሆን ካለፉት አምስት ጨዋታዎች ሦስቱን በአቻ ውጤት ማጠናቀቁና በመጨረሻው መርሃ-ግብር በአርባምንጭ መሸነፉ የነጥብ ረሃብ ውስጥ እንዲቆይ አድርጎታል። በሊጉ 20 ግቦችን አስቆጥሮ በተመሳሳይ 20 ግቦች የተቆጠሩበት አዳማ ከአቻ ውጤት አዙሪት ወጥቶ ወደ መሪዎቹ ለመጠጋት ዛሬ የግድ ማሸነፍ ይኖርበታል። የአዳማው ስብስብ የቡናን የፈጠራ አማካዮች መግታትና በመልሶ ማጥቃት የሚገኙ አጋጣሚዎችን በአግባቡ ከተጠቀመ፣ የደረጃ ሰንጠረዡን አጋማሽ ጥንካሬውን አስከብሮ ለመውጣት ሰፊ አጋጣሚ አለው።
ሁለቱ ቡድኖች ከዚህ ቀደም 47 ጊዜ ተገናኝተው ኢትዮጵያ ቡና 24 ጊዜ በማሸነፍ የበላይነቱን ይዟል። አዳማ ከተማ በበኩሉ 11 ጊዜ ድል ሲቀናው በ12 ጨዋታዎች ደግሞ ቡድኖቹ አቻ ተለያይተዋል። በሁለቱ የእርስ በርስ ግንኙነት ቡና 79 ፤ አዳማ 43 ጎሎችን ማስቆጠር ችለዋል።
ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከ ሀዋሳ ከተማ
የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በደረጃ ሰንጠረዡ የታችኛው ክፍል (13ኛ ደረጃ) ላይ ተቀምጦ ቢገኝም ካለፉት አምስት ጨዋታዎች በሁለቱ ድል ቀንቶት በመጨረሻው ሳምንት በድሬዳዋ ላይ ያስመዘገበው የ 2 ለ 1 ስኬት ለዛሬው ጨዋታ ትልቅ ሞራል ይሆነዋል። ቡድኑ በ23 ጨዋታዎች 28 ግቦችን በማስቆጠር የሚደነቅ የማጥቃት ብቃት ቢኖረውም በአንጻሩ 30 ግቦችን ማስተናገዱ የተከላካይ ክፍሉ ላይ ትልቅ ክፍተት እንዳለ ያሳያል። የባንክ ስብስብ ዛሬ ከሊጉ መሪዎች ተርታ የሚሰለፈውን ጠንካራ ተጋጣሚውን ለመቋቋም ያንን ውጤታማ የማጥቃት መስመሩን ከመከላከል ጥንቃቄ ጋር አቀናጅቶ በመጠቀም ከወራጅ ቀጠናው ስጋት ራሱን ማራቅ ይጠበቅበታል።
ሀዋሳ ከተማ በበኩሉ በ40 ነጥብ 2ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጦ በዋንጫ ፉክክሩ ለመዝለቅ በሚያደርገው ትንቅንቅ ውስጥ የዛሬው ጨዋታ ወሳኝ መወጣጫው ነው። ካለፉት አምስት ጨዋታዎች መካከል ሦስቱን በድል ያጠናቀቀውና በመጨረሻው ጨዋታ መቐለን 1 ለ 0 ያሸነፈው ሀዋሳ በሊጉ እጅግ ጠንካራ ከሚባሉ የተከላካይ ክፍሎች ካሏቸው ቡድኖች አንዱ ሲሆን ከሌላው ጠንካራ የፊት መስመር ያለው ቡድን የሚያደርገው ፍልሚያም ጨዋታው ተጠባቂ ያደርገዋል።
በሊጉ 40 ጨዋታዎች የተገናኙት ሁለቱ ቡድኖች በ14 ጨዋታዎች ነጥብ በመጋራት ሲፈፅሙ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በ15 እንዲሁም ሀዋሳ ከተማዎች ደግሞ በ11 ጨዋታዎች ድል ማድረግ ችለዋል። በጨዋታዎቹ ንግድ ባንኮች 44፤ ሀዋሳ ከተማዎች ደግሞ 40 ግቦችን ማስቆጠር ችለዋል።
ሁለቱም ቡድኖች በዛሬው ጨዋታ በጉዳትም ሆነ በቅጣት የሚያጡት ተጫዋች የለም።

