በጨዋታ ሳምንቱ የመዝጊያ ቀን ጨዋታዎች ቢጫ ለባሾቹ እና ዐፄዎቹ ተጋጣሚዎቻቸውን ድል አድርገዋል

ወልዋሎ ዓ/ዩ ከ ኢትዮ ኤሌክትሪክ
ግብ ለመመልከት ዘጠኝ ደቂቃዎችን ብቻ ባስጠበቀን በዚህ ፍልሚያ ወልዋሎዎች ቀዳሚ መሆን ችለዋል። ከሜዳው የቀኝ መስመር የተሻገረውን ኳስ ሰመረ ሀፍታይ ወደ ግብ ሲሞክረው የኤሌክትሪኩ ግብ ጠባቂ የሱፍ ሞሮ የመለሰውን ኳስ በቅርብ ርቀት ላይ የነበረው ኮንኮኒ ሀፊዝ በጥሩ ንቃት ወደ ግብነት ቀይሮ ቡድኑን መሪ ማድረግ ችሏል።
ነገር ግን የወልዋሎቹ ደስታ ብዙም አልዘለቀም በ22ኛው ደቂቃ ላይ በበርካታ ተከታታይ ንክኪዎች የተገነባውን ማራኪ ማጥቃት ተከትሎ ያሬድ የማነ ከግራ መስመር ያሻገረውን ኳስ አቤል ሀብታሙ በግንባሩ በመግጨት የኤሌክትሪክን የአቻነት ግብ ከመረብ አሳርፏል።

ከዚያም በላይ ሁለቱም ወገኖች በኮንኮኒ ሀፍዝ፣ በአዮብ ገብረማርያም እና በአቤል ሀብታሙ አማካኝነት ተጨማሪ ሙከራዎችን ቢያደርጉም የመጀመሪያው አጋማሽ በ1-1 አቻ ውጤት ተጠናቋል።

ሁለተኛው አጋማሽ ከመጀመሪያው በተለየ ረዘም ላለ ደቂቃ የጠሩ የግብ ዕድሎችን ሳያስመለክተን ቢቆይም ወልዋሎዎች የጨዋታውን መሪነት ለመጨበጥ ያላቸውን ፍላጎት አላቋረጡም። በ70ኛው ደቂቃ ላይ ከቀኝ መስመር በየነ ባንጃ ያሻገረውን ድንቅ ኳስ በጨዋታው ላይ ጥሩ እንቅስቃሴ ሲያሳይ የነበረው እንዳልካቸው ጥበቡ በግንባሩ በመግጨት ግብ አስቆጥሮ ቡድኑን በድጋሚ መሪ ማድረግ ችሏል።
ከግቡ መቆጠር በኋላም ወልዋሎዎች በበየነ ባንጃ አማካኝነት ተጨማሪ የግብ ዕድል ቢፈጥሩም በግብ ጠባቂው ጥረት ሊድን ችሏል። በአንጻሩ የኤሌክትሪክ ተጫዋቾች ወደ ወልዋሎ የግብ ክልል በመጠጋት የአቻነት ግብ ለመፈለግ ተደጋጋሚ ጥረቶችን ቢያደርጉም የወልዋሎን የተደራጀ መከላከል ሰብረው መግባት ሳይችሉ ቀርተዋል። በመጨረሻም ጨዋታው በወልዋሎ ዓ/ዩ 2 ለ 1 አሸናፊነት ተጠናቋል።
ፋሲል ከነማ ከ አዳማ ከተማ
የምሽቱ ተጠባቂ ፍልሚያ በጀመረበት የመጀመሪያ አጋማሽ አዳማ ከተማዎች በግራ ክንፍ በኩል ተደጋጋሚ ጥቃቶችን በመሰንዘር ብልጫ መውሰድ ችለዋል። ዳዋ ሆቴሳ እና ቢኒያም አይተን በግንባር ባደረጓቸው አደገኛ ሙከራዎች ወደ ግብ የቀረቡት አዳማዎች በ12ኛው ደቂቃ ላይ መሪነቱን ጨብጠዋል። ከማዕዘን ምት የተሻማውን ኳስ የፋሲሉ አብዱላዚዝ አማን በራሱ ግብ ላይ ማስቆጠሩ ለአዳማዎች የመሪነት ክብርን አጎናጽፏል።

ግብ ካስተናገዱ በኋላ ቀስ በቀስ ወደ ጨዋታው የተመለሱት ፋሲል ከነማዎች የማጥቃት ጫናቸውን በማበርታት በ35ኛው ደቂቃ ላይ የአቻነት ግባቸውን አግኝተዋል። ከተከላካይ ክፍል የተሻገረውን ኳስ ናትናኤል ገብረጊዮርጊስ በጥሩ ሁኔታ አመቻችቶ ሲያቀብለው ታምራት እያሱ ኳሷን ወደ ግብነት ቀይሮ ቡድኑን ወደ ጨዋታው መለሰ የመጀመሪያው አጋማሽም በ1-1 አቻ ውጤት ተጠናቀቀ።

ሁለተኛው አጋማሽ ሲቀጥል ፋሲል ከነማዎች የተሻለ ጫና ፈጥረው እና ጨዋታውን ተቆጣጥረው መንቀሳቀስ የጀመሩ ሲሆን ይህ ብልጫቸውም በ67ኛው ደቂቃ ላይ ወደ መሪነት አምርቷቸዋል። ከመሀል ሜዳ የተሻገረውን ኳስ ታምራት እያሱ ድንቅ በሆነ ተጋድሎ የአዳማውን ግብ ጠባቂ መውጣት ተመልክቶ በግንባሩ በመግጨት ከመረብ አሳርፎ ለራሱም ለቡድኑም ሁለተኛውን ግብ ማስቆጠር ችሏል።

የጨዋታው መደበኛ ሰዓት አልቆ የዳኛው የመጨረሻ ፊሽካ በሚጠበቅበት ጭማሪ ደቂቃ ላይ ፋሲሎች ፈጣን የመልሶ ማጥቃት የዕለቱ ኮከብ ታምራት እያሱ አመቻችቶ ያቀበለውን ኳስ ቃልኪዳን ዘላለም ከሳጥኑ ጠርዝ ላይ በጥሩ አጨራረስ ከመረብ ጋር በማገናኘት ጨዋታው በፋሲል ከነማ 3 ለ 1 አሸናፊነት ተጠናቋል። ቡድኑም ከተከታታይ ድል አልባ ጉዞዎች በኋላ ወደ ድል ጎዳና ተመልሷል።

