የቶታል ኢነርጂስ አፍሪካ ዋንጫ የምድብ ማጣሪያ ድልድል በነገው ዕለት ይካሄዳል።

በኬንያ ፣ ታንዛኒያ እና ዩጋንዳ አዘጋጅነት ለሚካሄደው የ2027 ቶታል ኢነርጂስ አፍሪካ ዋንጫ የምድብ ማጣሪያ ድልድል በነገው ዕለት 9፡00 ሰዓት በግብፅ መዲና ካይሮ በሚገኘው የግብፅ እግር ኳስ ማህበር ዋና ፅሕፈት ቤት ይካሄዳል።
ሦስቱ የድግሱ አዘጋጆች ጨምሮ 48 ሀገራት የሚሳተፉበት የምድብ ማጣሪያ ውድድሩ እያንዳንዳቸው 4 ቡድኖች ባቀፉ 12 ምድቦች ተከፍሎ የሚካሄድ ሲሆን ምድባቸውን በበላይነት ያጠናቀቁ ሁለት ቡድኖችም በቀጥታ 24 ሀገራት በሚካፈሉበት አፍሪካ ዋንጫ የሚሳተፉ ይሆናል።
በተጨማሪም ቀድመው በውድድሩ መሳተፋቸውን ያረጋገጡ ሦስቱ አዘጋጅ ሀገራት ከሚገኙባቸው ሦስት ምድቦች የተሻለ ነጥብ የሰበሰቡ አንድ አንድ ቡድኖች ብቻ ወደ አፍሪካ ዋንጫው እንደሚያመሩ ታውቋል።
በቀጣይ ዓመት መጀመሪያ ይጀመራል ተብሎ የሚጠበቀው ይህ የምድብ ማጣሪያ ውድድር በሦስት የፊፋ የጨዋታ ካሌንደር ወቅቶች ውስጥ የሚካሄድ ሲሆን የመጀመሪያ ሁለት ጨዋታዎች ከመስከረም 11 እስከ 26 ባሉት ቀናት የሚካሄዱ ይሆናል።

