የሲቢኢ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ 35ኛ ሳምንት ዛሬ በሚደረጉ ሦስት ጨዋታዎች ፍፃሜውን የሚያገኝ ሲሆን ጨዋታዎቹን የተመለከቱ መረጃዎች እንደሚከተለው አቅርበንላችኋለን።

ሸገር ከተማ ከ ወልዋሎ ዓ/ዩ
በሊጉ የደረጃ ሰንጠረዥ በ43 ነጥብ 13ኛ ደረጃ ላይ የሚገኘው ሸገር ከተማ ካለፉት አምስት የሊግ ጨዋታዎች 2 ድል፣ 1 አቻ እና 2 ሽንፈት ያስመዘገበ ሲሆን በቅርብ ጨዋታው ፋሲል ከነማን 1 ለ 0 ማሸነፉ ለዛሬው ፍልሚያ ተጨማሪ ስነ ልቦናዊ ጥንካሬ ይሆነዋል:: ቡድኑ በ34 ጨዋታዎች 30 ጎሎችን አስቆጥሮ 29 ጎሎችን በማስተናገድ የ+1 ንጹህ የግብ ክፍያ ባለቤት ሲሆን ሸገር ከተማ አሁን ላይ ካለበት መካከለኛ የደረጃ ስፍራ ከፍ ለማለትና ወደ ላይኛው ክፍል ለመጠጋት የዛሬውን ጨዋታ በበላይነት ለመጨረስ ከመሃል ሜዳ የሚነሱ ታክቲካዊ እቅዶችን አተኩሮ መተግበር ውጤታማ ሊያደርጉት ይችላሉ።
በበኩሉ በ41 ነጥብ 16ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጠው ወልዋሎ አዲግራት ከታችኛው ክፍል የወራጅ ቀጠና ስጋት ሙሉ በሙሉ ርቆ አስተማማኝ ቦታ ለመያዝ የዛሬውን ጨዋታ እንደ ወሳኝ ማምለጫ ነው የሚቆጥረው። ካለፉት አምስት ጨዋታዎች 1 ድል፣ 3 አቻ እና 1 ሽንፈት ያስመዘገበውና በቀላሉ እጅ የማይሰጥ ስብስብ መሆኑን ያሳየው ወልዋሎ በ34 ጨዋታዎች 30 ጎል አስቆጥሮ 34 ጎል አስተናግዷል። ቡድኑ ከወራጅ ቀጠናው ለመራቅ ያለውን ጽኑ ፍላጎት ለማሳካት የሸገር ከተማን የማጥቃት መስመር በመግታትና የራሱን የኋላ ክፍል ክፍተት አርሞ ውጤት ለመያዝ ዛሬ ጠንካራ ታክቲክ ይዞ እንደሚገባ ይጠበቃል።
ሸገር ከተማዎች ከጉዳትም ሆነ ከቅጣት ነጻ የሆነው ስብስባቸውን ይዘው ለዛሬው ጨዋታ ይቀርባሉ።
ሁለቱ ቡድኖች ለመጀመሪያ ጊዜ በሊጉ መድረክ የተገናኙ ሲሆን ጨዋታውም 1-1 በሆነ አቻ ውጤት ተጠናቋል።
ኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ከ መቐለ 70 እንደርታ
46 ነጥብ በመሰብሰብ በሰንጠረዡ 8ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጠው የኤሌክትሪክ ስብስብ ካለፉት አምስት ጨዋታዎች 1 ድል፣ 1 አቻ እና 3 ሽንፈት ያስመዘገበ ሲሆን ትንሽ በማይባሉ ሳምንታት በውጤት መዋዥቅ ውስጥ ቆይቷል። ቡድኑ በ34 ጨዋታዎች ያስመዘገበውን 28 ጎል እና 24 ጎል ብቻ ያስተናገደውን ጠንካራ የተከላካይ ክፍሉን እንደ ዋና መተማመኛ በመጠቀም ዛሬ ወደ ቀደመው የአሸናፊነት ማንነቱ ለመመለስና ደረጃውን ይበልጥ ከፍ ለማድረግ ይረዳዋል።
በተቃራኒው መስመር በ35 ነጥብ 19ኛ ደረጃ ላይ በመገኘት በወራጅ ቀጠናው ውስጥ ከፍተኛ ውጥረት ላይ የሚገኘው መቐለ በሊጉ የመቆየት ተስፋውን ለማለምለም የዛሬው ጨዋታ ለእነሱ የህልውና ጉዳይ ነው። ካለፉት አምስት ጨዋታዎች 1 ድል፣ 2 አቻና 2 ሽንፈት ያሰናገደውና በ34 ጨዋታዎች 23 ጎሎችን ብቻ ያስቆጠረው መቐለ ያለበትን የማጥቃት ድክመት ቀርፎ ከወራጅ ቀጠናው ለመውጣትና የደጋፊውን ተስፋ ለማደስ ሙሉ አቅሙን አውጥቶ እንደሚጫወት ይገመታል።
ሁለቱ ቡድኖች ከዚህ ቀደም 5 ጊዜ ተገናኝተው መቐለ 4 ኤሌክትሪክ ደግሞ 1 ጊዜ ሲያሸንፉ በጨዋታዎቹ መቐለ 6 በአንጻሩ ኤሌክትሪክ 3 ግቦችን ከመረብ አሳርፈዋል።
ባህር ዳር ከተማ ከ ወላይታ ድቻ
የጣናው ሞገድ ባህር ዳር ከተማ ካለፉት አምስት ጨዋታዎች 2 ድል እና 3 አቻ በመለያየት ምንም ሽንፈት ሳያስተናግድ በመጓዝ በአሁኑ ወቅት በ46 ነጥብ 9ኛ ደረጃ ላይ ይገኛል። በ34 ጨዋታዎች 26 ጎሎችን አስቆጥሮ 23 ጎሎችን ብቻ ያስተናገደውና ጠንካራ የኋላ ክፍል አጥር ያለው ባህር ዳር ከነማ ከዋንጫ ፉክክር ውጪ ቢሆንም ይህንን ያልተሸነፈበትን ግስጋሴ አስጠብቆ በመጓዝ የደረጃ ሰንጠረዡን ይበልጥ ለማሻሻልና እስከ አራተኛ ደረጃ ያለውን ስፍራ ለመሻማት ወደ ሜዳ ይገባል::
በሌላ በኩል በ44 ነጥብ 12ኛ ደረጃ ላይ የሚገኘው ወላይታ ድቻ ካለፉት አምስት ጨዋታዎች 1 ድል እና 4 አቻ በመለያየት በቀላሉ ሊበገር የማይችል ጠንካራ ተፎካካሪ መሆኑን በተግባር አሳይቷል። ድቻዎች 32 ጎሎችን አስቆጥሮ 29 ጎሎችን ያስተናገደውን ስብስባቸውን በመጠቀም የባህር ዳርን ጉዞ ለመግታት፣ በመካከላቸው ያለውን የነጥብ ልዩነት ለማጥበብና ከታችኛው ክፍል ሙሉ በሙሉ ተለይቶ መካከለኛውን የደረጃ ስፍራ በፅኑ ለመያዝ ዛሬ ሳቢ የሆነ ፉክክር ያስመለክቱናል ተብሎ ይጠበቃል::
በውሃ ሰማያዊ ለባሾቹ በኩል አማኑኤል ገብረሚካኤል እና ፍጹም ፍትሕአለው ለዛሬው ጨዋታ ዝግጁ ሲሆኑ ክንዱ ባየልኝ እና ወንድወሰን በለጠ ግን በጉዳት ምክንያት ከጨዋታው ውጭ ናቸው።
ሁለቱ ቡድኖች ከዚህ ቀደም በሊጉ 12 ጊዜ ተገናኝተው ባህርዳር ከተማ 4 ፣ ወላይታ ድቻ 1 ጊዜ አሸንፈው 8 ግንኙነታቸው በአቻ ውጤት ተጠናቋል። የጣና ሞገዶቹ 11 ፣ የጦና ንቦቹ በበኩላቸው 5 ጎሎችን አስቆጥረዋል።

