ሪፖርት | አዞዎቹ እና ዐፄዎቹ ድል ቀንቷቸዋል

ሪፖርት | አዞዎቹ እና ዐፄዎቹ ድል ቀንቷቸዋል

አርባምንጭ ከተማ ተከታታይ ሁለተኛ ጨዋታውን በማሸነፍ ደረጃውን ያሸሻለበትን ወሳኝ ድል ሲያሳካ ፋሲል ከነማ ሀዲያ ሆሳዕናን 1ለ0 ረቷል።

አርባምንጭ ከተማ ከ ምድረገነት ሽረ

በሁለተኛው ቀን አዳማ ላይ ከተደረጉ ጨዋታዎች መካከል ቀዳሚ የነበረው አርባምንጭ ከተማ እና ምድረገነት ሽረ ጨዋታ ጅማሮ ላይ ምድረገነቶች አደገኛ ሙከራ አድርገው ቢጀምሩትም አዞዎቹ በግብ ቀዳሚ የሆኑበት ነበር።

በፈጣን ሽግግር ከግብ ጠባቂያቸው ኳስን የጀመሩት አዞዎቹ በቀኝ መስመር በኩል ኳስ ይዘው ገብተው ጄሮም ፈሊፕ ሳጥን ውስጥ ብቻውን ሆኖ በመጠባብቅ ላይ ለነበረው አብዱራህማን ያሻገረውን ኳስ ተጫዋቹ በቀላል ንክኪ ወደ ግብነት ቀይሮ ቀዳሚ ሊያደርጋቸው ችሏል።

አንፃራዊ የኳስ ቁጥጥር ብልጫ የነበራቸው ምድረገነቶች አልፎ አልፎ ወደፊት ሄደው ጠንካራ ሙከራ ማድረግ የቻሉ ቢሆንም ከተጋጣሚያቸው በላይ በአጨዋወት ረገድ የበላይነት ያሳዩበትን የመጀመሪያ አጋማሽ እየተመሩ መልበሻ ክፍል ለመግባት ተገደዋል።

ጨዋታው በሁለተኛው አጋማሽ ሲመለስ ሙሉ ለሙሉ የጨዋታ ብልጫ ውስደው የተመለሱት ሽረዎች ወደፊት ገብተው በጫና የአቻነት ግብ ለማግኘት ሲጣጣሩ እየተመለከትን ሲሆን በተለይም ለ65ኛው ደቂቃ ላይ የአዞዎቹ የቀዳሚነት ግብ አስቆጣሪው አብዱራህማን በሁለት ቢጫ ካርድ ከሜዳ ከተወገደ በኋላ የበለጠ ተጭነው የነበረ ቢሆንም ፍሬያማ አልነበሩም። በተቃራኒው ግን አዞዎቹ በመልሶ ማጥቃት አደገኛ ሙከራዎችን ሲያደርጉ ነበር።

ጨዋታው ለአዞዎቹ ሦስት ነጥብ በማስገኘት እንዲሁም አንድ ደረጃ ከፍ በማድረግ ለመጠናቀቅ የመጨረሻ ፊሽካ በሚጠበቅበት ሰዓት ተጨማሪ ግብ አስገኝቶላቸዋል። ተቀይሮ ወደ ሜዳ የገባው በፍቅር ግዛው ከመስመር ያሻገረገውን ኳስ ቴዎድሮስ ባንቲ ተጨማሪ ደቂቃ ላይ በማስቆጠር ከደረጃው ግርጌ ሁለት ደረጃዎችን ከረጅም ሳምንታት በኋላ ከፍ እንዲሉ በማድረግ ጨዋታው ተቋጭቷል።

ሀዲያ ሆሳዕና ከ ፋሲል ከነማ

የእለቱ ሁለተኛው ጨዋታ ሀዲያ ሆሳዕናን ከፋሲል ከነማ አገናኝቷል። ነብሮቹ በመከላከል እንዲሁም በመልኮ ማጥቃት ለመጫወት ጥረት ባደረጉበት በመጀመሪያ አጋማሽ ዐፄዎቹ በጥንቃቄ በመጫወት ላይ የነበረውን የነብሮቹን የተከላካይ መስመር ለማስከፈት የተቸገሩበትን አጋማሽ መመለከት ችለናል።

በአጋማሹ አንፃራዊ የጨዋታ ብልጫ የነበራቸው ፋሲል ከነማዎች ሲሆኑ ወደፊት ሄደው ዒላማውን የጠበቀ ሙከራ በማድረግ ረገድ የተሻሉ የነበሩት ግን ነብሮቹ ነበሩ። ዐፄዎቹ በመጀመሪያ ኢላማውን በጠበቀ ሙከራ የአጋማሹ መገባደጃ 43ኛው ደቂቃ ላይ ቀዳሚ የሆኑበትን ግብ ማስቆጠር ችለዋል።

በተጠቀሰው ደቂቃ ዳግም አወቀ ከመስመር ያሻገረውን ኳስ ታምራት እያሱ በቀላል ንክኪ ወደ ግብነት ቀይሮ አጋማሹ በዐፄዎቹ በላይነት እንዲጠነቃቀ ሲያደርግ ከዛ በፊት ዳግም አወቀ አስቆጥሮ ከጨዋታ ውጪ ተብሎ የተሻረባቸው እንዲሁም ሀብታሙ ተከስተ በሁለት ቢጫ ካርድ ከሜዳ የወጣበት ክስተት በአጋማሹ የሚጠቀሱ ክስተት ነበሩ።

ነብሮቹ ጠንከር ብለው በተመለሱበት በሁለተኛው አጋማሽ አስቆጪ አጋጣሚዎችን እየፈጠሩ ወደ ጨዋታ ለመመለስ ጥረት ሲያደርጉ የጨዋታውን የበላይነት የወሰዱበትን ሂደትም በግብ እጅግ ለአቻነት የተቃረቡ ሙከራዎችን ማድረግ ችለዋል። አንፃራዊ የጨዋታ ብልጫ የተወሰደባቸው ዐፄዎቹ በመልሶ ማጥቃት እየገቡ ተጨማሪ ግብ ለማስቆጠር ጥረት ያደረጉ ቢሆንም የተገኘውን ውጤት ለማስጠበቅ ጠንከር ያለ መከላከል በሙሉ ሀይላቸው ሲያደርጉ እያስተዋልን ሁለተኛው አጋማሽ ግብ የሚቆጠርበት እየመሰለ በመጀመሪያው አጋማሽ መጠናቀቂያ ላይ በተቆጠረች ብቸኛ ግብ ለዐፄዎቹ ሦስት ነጥብ በማስገኘት መቋጫውን አግኝቷል።