የ2019 ሲቢኢ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ጨዋታን በባሕር ዳር ከተማ ማካሄድ በሚቻልበት ሁኔታ ዙርያ ውይይት ተደረገ።

የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ በአዲስ መልክ መካሄድ ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ የሊጉን ውድድር በጥሩ ሁኔታ በማዘጋጀት የምትታወቀው ባህር ዳር ከተማ ከቅርብ ጊዚያት ወዲህ ስታዲየሙ በFIFA የወጣውን መስፈርት የሚያሟላ ዓለም አቀፍ ስታዲየም ለማድረግ በሚካሄደው ግንባታ ምክንያት ያለፉትን ሦስት ዓመታት የሊጉ ውድድሮች ሳይካሄድበት ቀርቷል።
አሁን ግንባታው ወደ መጨረሻው ምዕራፍ እየደረሰ እንደሆነ በሚገለፀው የባህርዳር ዓለም አቀፍ ስታዲየም የ2019 የሲቢኢ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የውድድር ዘመን ዳግም ወደ ማስተናገድ በምትመለስበት ዙርያ በዛሬው ዕለት የመስክ ጉብኝት እና የሁለትዮሽ ውይይት መደረጉን አውቀናል።
በቦታውም የባሕር ዳር ከንቲባ አቶ ጎሹ እንዳላማው የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ አክሲዮን ማህበር የቦርድ ሰብሳቢው መቶ አለቃ ፈቃደ ማሞ እና ሥራ አስኪያጅ አቶ ክፍሌ ሰይፈን ጨምሮ ሌሎች የሚመለከታቸው አካላት በተገኙበት ዓለም አቀፍ ስታዲየሙን ጨምሮ በባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ 3 ካምፓሶች ያሉትን የልምምድና የውድድር ሜዳዎችን ተዟዙረው ጎብኝተዋል።
የባሕር ዳር ከንቲባ አቶ ጎሹ እንዳላማው “ባሕር ዳር የ2019 የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ጨዋታን ማካሄድ የሚያስችል ብቁ ቁመና ላይ እንደምትገኝ” ገልፀው ውድድሩ ወደ ባህር ዳር በሚመጣበት ሁኔታ ዙርያ ከአክስዮን ማህበሩ ከፍተኛ አመራሮች ጋር ውይይት ማድረጋቸውን ከባህር ዳር ከተማ ኮሚዩኒኬሽን ቢሮ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።

