ፕሪሚየር ሊግ ትኩረት 11 | No Sponsor No Problem

ፕሪሚየር ሊግ ትኩረት 11 | No Sponsor No Problem

ሌላኛው የዚህኛው ሳምንት ትኩረታችን ደግሞ ብልሃት የተሞላበት የሸገር ከተማ ውሳኔን ይመለከታል።


እግር ኳሳችን በሜዳ ሆነ ከሜዳ ውጭ ባሉ ጉዳዮች ከፍ ያለ የሀሳብ እጥረት እንዳለበት ተደጋግሞ ይነገራል። ታዲያ በዚህ ውስጥ ግን ከዚህ ከተለመደው የታጠረ አስተሰሳብ ወጣ ያሉ ሙከራዎችን አልፎ አልፎ የሚያደርጉ አካላት ሲመጡም እግር ኳሳችን በሚገባው ልክ እውቅና ሲሰጣቸው አንመለከትም ፤ ይህም አለመሆኑ ሀሳቡ ገዢ ሀሳብ እንዳይሆንና ሌሎችም ወደዚሁ መንገድ እንዳይገቡ ሲያደርግ ይስተዋላል።

የዚህ እሳቤ ሰለባ የሆኑት አብዛኛቹ የሀገራችን ክለቦች ከድክመቶቻቸው አንዱ ክለቦች ከስያሜ እና መለያ ቀለሞች ባለፈ የመጡበትን ማህበረሰብን ሆነ ከተማ እምብዛም አይመስሉም። የዚህም አንደኛው መገለጫ ክለቦች ማህበረሰባቸውን ሲወክሉና ሲያስተዋውቁ አይስተዋልም ፤ ለዚህ ብዙ ማሳያዎችን ማቅረብ ቢቻልም የዘንድሮው ሸገር ከተማ አካሄድ ግን በዚህ ረገድ የሚበረታት አውንታዊ እርምጃ ተደርጎ ሊወሰድ ይችላል።

እንዳለመታል ሆኖ አብዛኞቹ የሊጉ ክለቦች ከመንግስት ቋት ከሚገኝ ሀብት በዘለለ ሌሎች የገቢ ምንጮች እምብዛም እንደሌላቸው ይታወቃል ከእነዚህ የገቢ ማግኛ መንገዶች አንዱ የመለያ ላይ ስፓንሰሮች ሲሆኑ አሁን ላይ በጣት ከሚቆጠሩ ክለቦች ውጭ አብዛኞቹ መለያቸው በፊትና ኋላው “ወና” እንደሆነ ይታወቃል። በዚህም ምክንያት ከሚኖረው ፋይናንሺያል እጦት ባሻገር ግን ክለቦች በመላው ዓለም በቀጥታ ስርጭት በሚታለፈው ውድድር የሚገኘው ትልቅ ዕይታ (Visibility) ለበጎ ዓላማ (Positive Cause) ከመጠቀም አንፃር በክለቦች ዘንድ ያለው አረዳድ ፍፁም ደካማ መሆኑም እንዲሁ የሚስተዋል ሀቅ ነው።

ነገር ዘንድሮ ሸገር ከተማ በዚህ ረገድ አንድ እርምጃ ወደ ፊት የተራመደ ይመስላል ፤ በዚህም በመለያው ላይ ያሉ ቁልፍ የማስታወቂያ ቦታዎችን ግን ለላቀ ዓለማ መጠቀም ጀምሯል።በሸገር ከተማ መለያ ደረት ላይ “Shaggar The Future City” የሚል እንዲሁም በመለያው እጀታ ላይ ደግሞ “Discover Shaggar” የሚሉ ከተማዋን ለዓለም ህዝብ የሚያስተዋውቁ ግዙፍ ሀሳብን ያነገቡ መልዕክቶችን አስፍረው እየተመለከትን እንገኛለን።

ይህ ጉዳይ ከምንም በላይ ከሳጥን ውጭ የማሰብ ውጤት ነው ፤ ጉዳዩ የአዲስ ዕይታም እንዲሁ መገለጫ ነው።ስፓርት በተለይ እግር ኳስ ካለው ዓለም አቀፍ ቅቡልነትና ተደራሽነት መነሻነት ሸገር ከተማ ኢትዮጵያ ውስጥ ከምትገኝ ከተማነት ባሻገር ከተማዋ በእነዚህ መልዕክቶች ሰዎች ይበል ስለከተማዋ እንዲጠይቁና እንዲያውቁ በትልቁ ማስተዋወቅ የሚችል እርምጃን ተራምደዋል።

በሀገራችንም በ2014 የውድድር ዘመን ወልቂጤ ከተማ በመለያው እጀታ ላይ “Visit Ethiopia” የሚል መልዕክት አስፍሮ እንደነበር የሚታወስ ሲሆን ከዛ በኃላ በነበሩ ዓመታት ግን በተለይ ስፓንሰር አልባ ክለቦች ይህ ነው የሚባል ሙከራን አልተመለከትንም።

እ.ኢ.አ በ2006 ባርሴሎና በታሪኩ ለመጀመሪያ ጊዜ ባደረገው የመለያ የደረት ስፓንሰር ስምምነት በተባበሩት መንግስታት የህፃናት መብት አጠባበቅ ላይ ትኩረት አድርጎ ከሚሰራው “UNICEF” ጋር በመፈራረም እስከ 2011 ድረስ ክለቡ ከተቋሙ ገቢ ሳያገኝ በአንፃሩ ለተቋሙ ድጋፍ እያደረገ ተቋሙን ሲያስተዋውቅ መቆየቱ ይታወቃል።

ታድያ የእኛ ሀገር ክለቦችም ቢያንስ ስፓንሰር ባይኖራቸው እንኳን እንደ ሸገር ከተማ ከተማቸውን ለዓለም ማስተዋወቅ አልያም እንደ ባርሴሎና የ2006 አካሄድ ሌሎች ማህበራዊ ኃላፊነቶችን መወጣት የሚያስችሉ ምግባረ ሰናይ ተቋማትን በማስተዋወቅን ለከተማቸው አልያም ለማህበረሰባቸው አንዳች በጎ ተፅዕኖን ማሳደር የሚችሉበት ዕድል ስለሚኖር ክለቦች ይህን ጉዳይ ሊያጤኑበት ይገባል እንላለን።