በርበሬዎቹ እና ነብሮቹ ቅጣት ተላለፈባቸው

በርበሬዎቹ እና ነብሮቹ ቅጣት ተላለፈባቸው

ሀላባ ከተማ እና ሀድያ ሆሳዕና ቅጣት ተጣለባቸው

የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ አክስዮን ማሕበር በአምስተኛ ሳምንት በተካሄዱ ጨዋታዎች ተፈጠሩ ላላቸው የስነ ምግባር ግድፈቶች የቅጣት ውሳኔዎች አስተላፏል። በዚህ መሰረት ጥቅምት 20 በሀላባ ከተማ እና በሀድያ ሆሳዕና መካከል በሃላባ ስታድየም በተካሄደው ጨዋታ ላይ የሁለቱም ክለብ ደጋፊዎች የስነ ምግባር ግድፈት ማሳየታቸውን በመጥቀስ የቅጣት ውሳኔ አስተላልፏል።

ሊግ ካምፓኒው ባለሜዳ የነበሩት ሀላባ ከተማዎች ደጋፊዎቻቸው በዕረፍት ሰዓት የተጋጣሚ ደጋፊዎች ላይ የውሀ ኮዳዎች በመወርወራቸው እንዲሁም በ55ኛው ደቂቃ ላይ የብሎኬት ስብርባሪዎች በመወርወር ደጋፊ ላይ ጉዳት ማድረሳቸውን ጠቅሶ ሀላባ ከተማን 75,000 ብር መቅጣቱን ይፋ ሲያደርግ የሀድያ ሆሳዕና ደጋፊዎችም የተጋጣሚ ደጋፊዎች ላይ የውሀ ኮዳዎች እና ቁሳቁስ በመወርወር ምላሽ መስጠታቸውንና የፀጥታ አካላትን ትዕዛዝ ባለማክበር ሁከት መፍጠራቸውን ተከትሎ ሀድያ ሆሳዕናን 50,000 ብር መቅጣቱ አስታውቋል።

በተያያዘ ዜና ነጌሌ አርሲ ከሸገር ከተማ ጋር ባደረገው ጨዋታ የተጋጣሚ ተጫዋችን በክርን ተማተሃል ተብሎ በቀይ ካርድ ከሜዳ የወጣውን ያሬድ ብሩክ የአራት ጨዋታ ቅጣት ሲተላለፍበት በተጨማሪም 3,000 ብር እንዲከፍል ተወስኖበታል።