በትናንትናው ዕለት በኢትዮጵያ ሽንፈት ያስተናገዱት የሞዛምቢኩ አሠልጣኝ ቺኪንሆ ኮንዴ እና ጋዜጠኛ አልፍሬዶ ጁኒየር መካከል ምን እንደተፈጠረ ጋዜጠኛው ማብራሪያ ሰጥቷል።
በአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ የምድብ 3ኛ ጨዋታ ሞዛምቢክ በሜዳዋ በኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን 1ለ0 ከተሸነፈች በኋላ የድህረ-ጨዋታ ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ በማምባዎቹ ዋና አሰልጣኝ ቺኪንሆ ኮንዴ እና በታዋቂው የላንስ ኤምዜድ ጋዜጠኛ አልፍሬዶ ጁኒየር መካከል የከረረ አለመግባባት እና ለአካላዊ ፀብ የተዳረገ ሁነት መፈጠሩት በትናንትናው ዕለት መረጃ ሰጥተናችው ነበር።
ጋዜጠኛ አልፍሬዶ ጁኒየር ከመግለጫው በኋላ በማኅበራዊ ትስስር ገጹ ባወጣው ዝርዝር ማብራሪያ ውዝግቡ ሊቀሰቀስ የቻለበትን ዋና ምክንያት እና በመግለጫው አዳራሽ የተፈጠረውን ሁኔታ በግልጽ አቅርቧል። እንደ ጋዜጠኛው ገለጻ ጉዳዩ የጀመረው ባለፈው ረቡዕ ሲሆን በግል ጉዳዮች ምክንያት በብሔራዊ ቡድኑ ልምምድ ላይ ባልተገኘበት ወቅት አሰልጣኝ ቺኪንሆ ኮንዴ ለሌሎች ጋዜጠኞች ስሙን በመጥቀስ የሽሙጥ ንግግር ሰንዝረው ነበር። ሐሙስ በተደረገው የቅድመ-ጨዋታ መግለጫ ላይ ደግሞ ሌሎች ጋዜጠኞች እሱ ሊጠይቃቸው ያሰባቸውን ጉዳዮች ቀድመው በማንሳታቸውና በተሰጠው ምላሽ በመርካቱ ጥያቄ ሳያነሳ መውጣቱን ገልጿል።

ዓርብ ምሽት ሞዛምቢክ በኢትዮጵያ ከተሸነፈች በኋላ በተሰጠው መግለጫ ላይ ጋዜጠኛው ሁለት ዋና ዋና ጥያቄዎችን ለአሰልጣኙ አቅርቧል። የመጀመሪያው የሞዛምቢክ እግር ኳስ “ፈርጥ” የሆነውን ጄኒ ካታሞን ከሜዳ የማስወጣት ውሳኔ ምን ዓይነት የእግር ኳስ አመክንዮ እንዳለው ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ ማክሰኞ በኢትዮጵያ ስለሚደረገው የመልስ ጨዋታ ዕቅድ የሚመለከት ነበር። ይሁን እንጂ አሰልጣኝ ቺኪንሆ ኮንዴ በጥያቄዎቹ በመበሳጨት ከጨዋታው በፊት በነበረው መግለጫ ላይ ጥያቄ ያላነሱ ጋዜጠኞች ዛሬ ስንሸነፍ ብቻ “ለምን ተሸነፍን?” ብለው ለመጠየቅ እንደሚመጡ በመግለጽ ወቀሳ ሰንዝረዋል። መግለጫው ከተጠናቀቀ በኋላ ጋዜጠኛ አልፍሬዶ ከባልደረባው ኤሊሴው ፓቲፌ ጋር ተቀምጦ የቡድኑን አምበል ኤድሚልሰን ዶቭን ለማነጋገር እየተጠባበቀ ባለበት ወቅት ሁኔታው ተባብሷል። አሰልጣኝ ቺኪንሆ ኮንዴ ወደ እርሱ ጣታቸውን በመቀሰርና በማመልከት ተገቢ ያልሆኑ ንግግሮችን እንደተናገሩት አስታውቋል።
አልፍሬዶ ጁኒየር በፅሑፉ ማጠቃለያ ላይ ድርጊቱን አጥብቆ በመተቸት አሰልጣኙን ጄኒ ካታሞን ለምን እንደቀየረ ወይም የማክሰኞው ጨዋታ ዕቅድ ምን እንደሆነ መጠየቅ ትንኮሳም ሆነ ጥቃት እንዳልሆነ አፅንኦት ሰጥቷል። አሰልጣኙ ለጥያቄዎች መልስ የመስጠት ግዴታ እንደሌለበት ቀደም ሲል ብሩኖ ዊልሰንን ለምን እንዳልጠራ ሲጠየቅ እንዳደረገው ሁሉ ዝም ማለት ይችል እንደነበር ጠቁሟል። ነገር ግን ጋዜጠኞች መቼ እና ምን ዓይነት ጥያቄ መጠየቅ እንዳለባቸው የሚወስነው አሰልጣኙ አለመሆኑን የጋዜጠኝነት ሚና በድል ቀን ብቻ ሳይሆን በተለይም በሽንፈት ጊዜ መጠየቅ፣ ማብራሪያ መፈለግና ሕዝብን ማሳወቅ እንደሆነ በመግለጽ ምቾት የማይሰጡ ጥያቄዎችን ከግላዊ ጥቃት ጋር መቀላቀል እንደማይገባ አሳስቧል።
በመግለጫው ላይ የተነሳውን ሁከት አስመልክቶ እስካሁን ብሔራዊ ፌዴሬሽኑ የሰጠው መረጃ ስለሌለ በአሠልጣኙ ወይም በፌዴሬሽኑ በኩል ያለውን ሀሳብ ማቅረብ አልቻልንም።

