ፕሪሚየር ሊግ ፡ ኢትዮጵያ ቡና በግብ ሲንበሸበሽ ሲዳማ ቡና ነጥብ ጣለ

ዛሬ በተካሄዱ 2 የ13ኛው ሳምንት የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ጨዋታዎች ኢትዮጵያ በሰፊ ግብ ሲያሸንፍ መሪው ሲዳማ ቡና አቻ ተለያይቷል፡፡

አበበ ቢቂላ ላይ በ8 ሰአት ወልድያን ያስተናገደው ኢትዮጵያ ቡና 5-2 በሆነ ሰፊ ውጤት አሸንፎ ከመሪው ጋርe ያለውን የነጥብ ልዩነት አጥብቧል፡፡ ኢትዮጵያ ቡና በ17ኛው ደቂቃ ቢንያም አሰፋ እንዲሁም ሀብታሙ ረጋሳ በ23ኛው ደቂቃ ባስቆጠሩት ግብ 2-0 ሲመራ ቆይቶ በ34ኛው ደቂቃ ብርሃን በላይ ለእንግዳዎቹ ግብ አስቆጥሮ ወልድያ ወደ ጨዋታው የተመለሰ መስሎ ነበር፡፡ ነገር ግን ኢትዮጵያ ቡናዎች ተደጋጋሚ ግቦች ለማስቆጠር ብዙም አልጠበቁም፡፡ በ40ኛው ደቂቃ ቢንያም አሰፋ እና በ42ኛው ደቂቃ አስቻለው ግርማ ባስቆጠሩት ተጨማሪ ግብ የመጀመርያውን አጋማሽ 4-1 በሆነ ውጤት አጠናቀዋል፡፡

ከእረፍት መልስ አብይ በየነ ለወልድያ ግብ ቢያስቆጥርም ጨዋታው ሊጠናቀቅ በተቃረበበት ደቂቃ ቢንያም አሰፋ የኢትዮጵየያ ቡናን 5 ኛ ግብ ከመረብ አሳርፎ ጨዋታው በቡና 5-2 አሸናፊነት ተጠናቋል፡፡ ቢንያም የ2007 የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ከተጀመረ ወዲህ ሐት – ትሪክ የሰራ የመጀመርያ ተጫዋች ለመሆን ሲበቃ የከፍተኛ ግብ አግቢነቱንም በ11 ግቦች መምራት ጀምሯል፡፡

ቀጥሎ የተደረገው የንግድ ባንክ እና ሲዳማ ቡና ጨዋታ 1-1 በሆነ አቻ ውጤት ተጠናቋል፡፡ የሊጉ መሪ ሲዳማ ቡና በአንዱአለም ንጉሴ የ65ኛ ደቂቃ ግብ 1-0 ሲመራ ቢቆይም ናይጄርያዊው አጥቂ ፊሊፕ ዳውዚ በ73ኛው ደቂቃ ላይ ግብ አስቆጥሮ ንገድ ባንክን ከሽንፈት ታድጓል፡፡

ሲዳማ ቡና ነጥብ ሲጥል ከ5 ተከታታይ ድሎች በኋላ ለመጀመርያ ጊዜ ሲሆን ግብ ጠባቂው ለአለም ብርሃኑም ከ5 ተከታታይ ጨዋታ በኋላ ግብ አስተናግዷል፡፡

ሊጉ ነገ በአበበ ቢቂላ እና የክልል ስታዲየሞች ሲቀጥል አበበ ቢቂላ ላይ ኤሌክትሪክ ከወላይታ ድቻ በ8 አሰት ፤ ቅዱስ ጊዮርጊስ ከ ደደቢት በ10 ሰአት ፤ አርባምንጭ ላይ አርባምንጭ ከነማ ከ አዳማ ከነማ ፤ አሰላ ላይ ሙገር ሲሚንቶ ከ መከላከያ ፤ ጎንደር ላይ ዳሽን ቢራ ከ ሀዋሳ ከነማ በተመሳሳይ 9 ሰአት ላይ ይጫወታሉ፡፡

ሊጉን 13 ጨዋታ ያደረገው ሲዳማ ቡና በ27 ነጥቦች ሲመራ 11 ጨዋታ ያደረገው ቅዱስ ጊዮርጊስ እና 12 ጨዋታ ያደረገው ኢትዮጵያ ቡና ኢትዮጵያ ቡና በእኩል 21 ነጥቦች ይከተላሉ፡፡

 

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *