የጨዋታ ሪፖርት | ጅማ አባ ቡና ከ ደደቢት ነጥብ ተጋርተዋል

በ5ኛው ሳምንት የኢትዮዽያ ፕሪሚየር ሊግ ጅማ ላይ ጅማ አባ ቡና ደደቢትን አስተናግዶ ነጥብ ተጋርቷል፡፡

የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ ከመጀመሩ አስቀድሞ ባሳለፍነው ሐሙስ ባልተጠበቀ ሁኔታ ሕይወቱ ላለፈው ለቀድሞ የኤሌክትሪክ እና የኢትዮዽያ ብሔራዊ ቡድን ተጫዋች ዘላለም ተሾመ የአንድ ደቂቃ የህሊና ፀሎት ተደርጓል፡፡

ከወትሮው በተለየ ሁኔታ ቁጥሩ ከፍተኛ የሆነ ተመልካች የታደመበት ጨዋታ ፈጠን ባለ እንቅስቃሴ የተጀመረ ሲሆን በመጀመርያው አጋማሽ ባለሜዳዎቹ ጅማ አባቡናዎች ተሽለው ታይተዋል፡፡ ደደቢት በመልሶ ማጥቃትና የፕሪሚየር ሊግ ልምዳቸውን በመጠቀም ጫናውን ተቆጣጥረው የወጡበት ፉክክር ተስተውሏል፡፡

ጨዋታው ከተጀመረበት ደቂቃ አንስቶ ባለ ሜዳዎቹ ጅማ አባቡናዎች አብዛኛውን የመጀመርያ አጋማሽ ክፍለ ጊዜ በኳስ ቁጥጥርም ሆነ በተደጋጋሚ ወደ ጎል በመድረስ የተሻለ ቢሆንም የሜዳው 3ኛ ክፍል ላይ ሲደርሱ ይቸገሩ ነበር፡፡

በ26ኛው ደቂቃ ማህመድ ናስር የግብ ጠባቂውን መውጣት ተመልክቶ በቀኝ መስመር የመታውና ግብ ጠባቂው ክሌመንት እንደምንም ያወጣበት ከጅማ አባ ቡና በኩል የምታስቆጭ የግብ አጋጣሚ ነበረች፡፡

በአንፃሩ ደደቢቶች በጌታነህ ከበደና በዳዊት ፍቃዱ አማካኝነት ያስቆጠሩት ጎል የእለቱ ዳኛ ከጨዋታ ውጭ ብለው በመሻራቸው ተጨዋቾቹ ተቃውሟቸውን ያሰሙ ሲሆን 24ኛው ደቂቃ ላይ ከአስራት መገርሳ ያሻገረለት ጌታነህ ከበደ ሳይጠቀምበት ከቀረው እድል ውጭ ይህ ነው የሚባል ሙከራ አላደረጉም፡፡

picsart_1481480529989

በሁለተኛው አጋማሽ ጅማ አባ ቡናዎች እንደመጀመርያው ሁሉ በኳስ ቁጥጥሩ የተሻሉ ቢሆኑም ከ40 ሜትር ርቀት ከቀኝ መስመር ዳዊት ተፈራ በቀጥታ ወደ ግብ ሞክሮት የደደቢት ግብ ጠባቂ ካወጣበት ኳስ በስተቀር በሁለቱም በኩል ይህ ነው የሚባል የጎል ሙከራ ሳይደርጉ ጨዋታው ያለ ምንም ግብ ተጠናቋል፡፡

የአሰልጣኞች አስተያየት

picsart_1481480446150

አሰልጣኝ ደረጄ በላይ – ጅማ አባ ቡና

” ጨዋታውን ማሸነፍ ይገባን ነበር፡፡ እድለኞች ባለመሆናችን ሳናሸንፍ ቀርተናል፡፡ የልጆቼ እንቅስቃሴ ማራኪ ነበር ፤ አድርጉ ያልኳቸውን አድርገዋል፡፡ የገጠምነው በፋይናንስ  ፣ በተጨዋች ስብስብ ፣ በሁሉም ረገድ ከእኛ የተሻለ ቡድን ነው፡፡ ሆኖም በሜዳ ላይ እንቅስቃሴ በልጠናቸዋል፡፡ አለማሸነፋችን ግን በጣም አበሳጭቶኛል፡፡

picsart_1481480490618

አሰልጣኝ አስራት ኃይሌ – ደደቢት

” ክለቡን የተረከብኩት በአጭር ጊዜ ውስጥ ነው፡፡ እንግዲህ በሂደት ቡድኑ እየተስተካከለ ይሄዳል፡፡ በዛሬው ጨዋታ ከሜዳ ውጭ እንደመጫወታችን ነጥብ መጋራታችን ጥሩ ነው፡፡ የመኪና ላይ ጉዞ ትንሽ አድክሞናል ፤ ተጫዋቾቼም በሙሉ ጤንነት ላይ ሳይገኙ መጫወታቸው ጎድቶናል፡፡ የተጫዋች ቅያሪው የሚያሳየንም ይሄን ነው፡፡ ልጆቼ በሙሉ ጤንነት ቢሆኑ የተሻለ ውጤት እናስመዘግብ ነበር፡፡ ያስቆጠርናቸው ግቦች መሻራቸው አልገባኝም፡፡ በተለይ አንደኛው ጎል መሻሩ አስገርሞኛል፡፡ በአጠቃላይ እንዲህ ባለ ደጋፊ መሀል ተጫውቶ ነጥብ ማግኘት አያስከፋም”

picsart_1481480408980

በመጨረሻም . . .

የጅማ ስታድየም ቡድኑ በሚያደርጋቸው ጨዋታዎች መያዝ ከሚገባው የተመልካች ቁጥር በላይ ለመያዝ በመገደዱ ተመልካቹን ለከፍተኛ ትርምስና አካል ጉዳት እየዳረገ ይገኛል፡፡ የሚመለከተው አካል ከዚህ የባሰ አደጋ ሳይከሰት ለችግሩ መፍትሔ እንዲያበጅ ከወዲሁ መልክታችንን ለማስተላለፍ እንወዳለን፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *