ሀዋሳ ስታድየም ላይ በተካሄደ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ 5ኛ ሳምንት ሀዋሳ ከተማ ከ መከላከያ 2-2 በሆነ አቻ ውጤት ተጠናቋል፡፡ በጥሩ የኳስ ፍሰት የጀመረው ጨዋታ 4 ግቦች ፣ 8 ቢጫ እና 4 ቀይ ካርዶች አስተናግዶ በውዝግብ ተጠናቋል፡፡
መከላከያ ከ2 ሳምንታት በፊት በእሳት አደጋ ህይወቱን ያጣው ክብረአብ ዳዊትን ምስሉ ያለበት ቲሸርት በመልበስ ወደ ሜዳ የገቡ ሲሆን በዚህ ሳምንት ከዚህ አለም በሞት ለተለየው የቀድሞ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ተጫዋች ዘላለም እሸቱ የ1 ደቂቃ የህሊና ጸሎት በማድረግ ጨዋታው ተጀምሯል፡፡
በሁለቱም በኩል ማራኪ የኳስ ፍሰት በታየበት በመጀመሪያው አጋማሽ የጨዋታ ክፍለ ጊዜ ሀዋሳ ከተማ በኤፍሬም ዘካሪያስ ፣ ጋዲሳ መብራቴ እና ፍርዳወቅ ሲሳይ አማካኝነት ተደጋጋሚ ሙከራዎችን ቢያደርግም የመከላከያው ግብ ጠባቂ አቤል ማሞ አክሽፏቸዋል ፡፡
የመጀመሪያው አጋማሽ መደበኛ ክፍለ ጊዜ ተጠናቆ በተጨማሪው 5 ደቂቃ ላይ አወል አብደላ ያሻገረለትን ኳስ ተጠቅሞ ምንይሉ ወንድሙ መከላከያን መሪ በማድረግ ወደ መልበሻ አቅንተዋል፡፡
ሁለተኛው አጋማሽ የጨዋታ ክፍለ ጊዜ ከመጀመርያው የተለየ መልክ ነበረው፡፡ አጅግ አስነዋሪ ስፖርታዊ ጨዋነት ግድፈት የታየበት ሲሆን በቁጥር በርካታ የነበሩ ጥፋቶች እንዲሁም ካርዶች ታይተዋል፡፡
ፍርዳወቅ ሲሳይን ተክቶ ወደ ሜዳ የገባው ቶጓዊው ጃኮ አራፋት በ58ኛው ደቂቃ ሀዋሳ ከተማን አቻ ያደረገች ግብ አስቆጥሯል፡፡
በግቧ የተነቃቁት ሀዋሳዎች በፍሬው ሰለሞን ፣ ጃኮ አራፋት እና ታፈሰ ሰለሞን አማካኝነት ጎል ሊሆኑ የሚችሉ እድሎችን መፍጠር ችለዋል፡፡ መከላከያዎችም በመልሶ ማጥቃት እንቅስቃሴ በምንይሉ ፣ ሳሙኤል ታዬ እና ማራኪ ወርቁ አማካኝነት የግብ ሙከራ ማድረግ ቢችሉም በ68ኛው ደቂቃ ጋዲሳ መብራቴ በ68ኛ ደቂቃ ከ25 ሜትር ርቀት አክርሮ በመምታት ሀዋሳን መሪ አድርጓል፡፡ ጋዲሳ ከግቡ መቆጠር በኋላ ደስታውን ለመግለፅ መለያው በማውለቁ በሁለት ቢጫ ከሜዳ ተሰናብቷል፡፡
በ71ኛው ደቂቃ የመሀል ዳኛው ይርጋለም ወ/ጊዮርጊስ በሀዋሳ ከተማ የሜዳ አጋማሽ የግራ ጠርዝ የቅጣት ምት የሰጡበት ውሳኔ የጨዋታውን መልክ የቀየረ ሆኗል፡፡ የሀዋሳ ከተማ ተጫዋቾች ውሳኔው ያልተገባ ነው በሚል ከዳኛው ጋር ክርክሮችን በመፍጠራቸው ዳንኤል ደርቤ በቀጥታ ቀይ ከሜዳ ተወግዷል ፡፡ ይህ ከሆነ 8 ደቂቃዎች በኃላ የመከላከያ እና የሀዋሳ ከተማ ተጫዋቾች እርስ በእርስ የፈጠሩት ያለመግባት ወደ ፀብ አምርቶ የመከላከያ እና ሀዋሳ ተጫዋቾች ለቡጢ ተጋብዘዋል፡፡ ይህ ፀብም በታፈሰ ሰለምን ተቀይሮ ከሜዳ የወጣው አዲስ አለም ተስፋዬ ከሀዋሳ ከተማ ታፈሰ ሰርካ ከመከላከያ በቀጥታ ቀይ ከተጠባባቂ ወንበሮቻቸው ላይ እንዲወገዱ ምክንያት ሆኗል፡፡
ጨዋታው በተፈጠረው ውዝግብ ለ15 ደቂቃዎች ከተቋረጠ በኃላ ቀጥሎ ሀዋሳ በ8 ተጫዋቾች ቀሪውን የጨዋታ ክፍለ ጊዜ ለመጫወት ተገዷል፡፡
መደበኛው 90 ደቂቃ ተጠናቆ በተጨመረው 10 ደቂቃ በምንይሉ ወንድሙ ተቀይሮ ወደ ሜዳ የገባው ካርሎስ ዳምጠው 90+3ኛው ደቂቃ ላይ ግብ አስቆጥሮ መከላከያን አቻ በማድረግ ጨዋታው 2-2 በሆነ አቻ ውጤት ተጠናቋል፡፡
በጨዋታው በአጠቃላይ 8 የቢጫ ካርድ እና 4 የቀይ ካርዶች የተመዘዙ ሲሆን የተጫዋቾች ያልተገባ ባህሪያት እንዲሁም የዳኝነት ክፍተት ተስተናግዶበት አልፏል፡፡
አስተያየቶች
አሰልጣኝ ውበቱ አባተ – ሀዋሳ ከተማ
” ጨዋታው በጥሩ መንፈስ ነበር የተጀመረው፡፡ ዳኛው ግን ስተቶችን ሰርቷል፡፡ ከማወራው በላይ ተበድለናል ፤ ምንእንደምል አላውቅም፡፡ 3 ተጫዋቾች በቀይ ካርድ ተሰናብተውብን ማሸነፍ የምንችለውን ጨዋታ አቻ ወጥተናል፡፡ ”
“ይህ ክስተት ለቀጣይ ጨዋታ ጫና አይፈጥርብንም ፤ ወደ አሸናፊነት እንመለላለን፡፡”
አሰልጣኝ በለጠ ገብረኪዳን – መከላከያ
” ከሜዳችን ውጭ እንደመጫወታችን ማግኝት ያለብንን አንድ ነጥብ አሳክተናል፡፡ ከዛ ባለፈ የዳኝነት ስተቶች ነበሩ ፤ ሰአት ሳያልቅ ነው ጨዋታው እንዲጠናቀቅ የተደረገው፡፡ ”
” ሀዋሳን ሳውቀው ጨዋ ህዝብ እና ተጫዋች እንደነበረው ነው፡፡ ነገር ግን ዛሬ የታየው ሌላ ነው፡፡ ስለ ስፖርታዊ ጨዋነት ብናስተምር መልዕክቴ ነው ”
* አርቢቴር ይርጋለም በሁለተኛው አጋማሽ የእጅ ሰአት ረስቶ በመግባቱ ጨዋታው ለጥቂት ደቂቃዎች ተቋርጦ ቆይቷል፡፡