የጨዋታ ሪፖርት | አርባምንጭ ከተማ መሪው ደደቢትን ነጥብ አስጥሏል

በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ 9ኛው ሳምንት ዛሬ አርባምንጭ ላይ በተደረገ ጨዋታ  አርባምንጭ ከተማ ከደደቢት 1-1 በሆነ አቻ ውጤት ተጠናቋል

ሁለት መልክ የነበረው የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ ማራኪ የኳስ ፍሰት ፣ ሁለት ድንቅ ጎሎች፣ ሽኩቻ እና ፍትጊያ የበዛበት እንዲሁም የደጋፊ የአደጋገፍ ድባብ አሳይቶን ተጠናቋል፡፡

በመጀመርያው አጋማሽ እንግዶቹ ደደቢቶች በኳስ ቁጥጥር ብልጫ ወስደው የተጫወቱ  ቢሆንም ባለሜዳዎቹ አርባምንጮች የግብ ዕድል በመፍጠር ቀዳሚ ነበሩ፡፡ በ20ኛው ደቂቃ ገ/ሚካኤል ያዕቆብ ከሳጥን ውጭ አክርሮ የመታው ፤ 24ኛው ደቂቃ ላይ አማኑኤል ጎበና ከወድሜነህ ዘሪሁን የተሻገረለትን በግራ እግሩ  በቮሊ መትቶ በግቡ አናት ላይ የወጣው ኳስ በአርባምንጭ በኩል አስደንጋጭ የጎል ሙከራዎቸች ነበሩ፡፡

በ26ኛው ደቂቃ ላይ ከሳጥን ውጭ በግምት ከ18ሜትር ርቀት ላይ የሊጉ ኮከብ ጎል አስቆጣሪነት እየመራ የሚገኘው ጌታነህ ከበደ ያገኘውን አጋጣሚ ወደ ጎልነት የመቀየር አቅሙን ያሳየበትን ግሩም ጎል አስቆጥሮ እንግዶቹ ደደቢቶችን ቀዳሚ አድርጓል። ግቧንም ተከትሎ በስቴዲዮሙ የተገኘው ተመልካች ለጌታነህ ከበደ ቆሞ በማጨብጨብ አድናቆቱን ገልፅውለታል።

ከግቡ መቆጠር በኋላ በቀሩት 19 ደቂቃ ባለሜዳዎቹ አርባምንጮች የአቻነት ጎል ፍለጋ ተጭነው ቢጫወቱም በጨዋታው መሀል በሚፈጠር ጉሽሚያና ውዝግብ ምክንያት ጨዋታው በመቆራረጡ ውበት ያለው ሳቢ ጨዋታ ሳይታይ የመጀመርያው አጋማሽ በደደቢት 1-0 መሪነት ተጠናቋል፡፡

በሁለተኛው አጋማሽ ሙሉ ሙሉ በሚያስብል ሁኔታ አርባምንጭ ከተማዎች በኳስ ቁጥጥሩም ሆነ ለጎል የቀረቡ ግልፅ የማግባት አጋጣሚዎችን በመፍጠር ረገድ ተሽለው የቀረቡ ሲሆን በአንፃሩ ደደቢት ተዳክሞ ታይቷል፡፡

በ48ኛው ደቂቃ ወድሜነህ ዘሪሁን ከርቀት መቶ በአግዳሚው ጠርዝ የወጣበት ፣ 54ኛው ደቂቃ ታደለ መንገሻ በአንድ ሁለት ቅብብል ገብቶ በግራ እግሩ መትቶ ግብ ጠባቂው ክሌመንት ያዳነበት አርባምንጭ ጫና ለመፍጠሩ ማሳያ የነበሩ ሙከራዎች ናቸው ።

በ56ኛው ደቂቃ ላይ በሳጥኑ ጠርዝ ላይ የመሃል ተከላካይ ሆኖ እየተጫወተ የሚገኘው ደስታ ደሙ ኳስ በእጁ በመንካቱ የተሰጠውን ቅጣት ምት በዕለቱ ድንቅ እንቅስቃሴ ሲያደርግ የዋለው ወድሜነህ ዘሪሁን በግሩም ሆኔታ አስቆጥሯል። ግብ ጠባቂው ክሌመንት ግቧ ስትቆጠር ቆሞ ከመመልከት በቀር ምነም ጥረት ማድረግ አልቻለም፡፡

ጎሉ መቆጠር በኋላ የተነቃቁት አርባምንጮች ተጨማሪ ጎል ለማስቆጠር የሚያስችሉ የግብ ሙከራዎች ማድረግ ችለው ነበር፡፡ በ60ኛው ደቂቃ አመለ ሚልኪያስ ያመከነው ግልፅ የጎል አጋጣሚ እንዲሁም 69ኛው ፣ 74ኛው እና 78ኛው ደቂቃ ላይ ተቀይሮ የገባው ጸጋዬ አበራ ያመከናቸው የግብ አጋጣሚዎች እጅግ የሚያስቆጩ ነበሩ፡፡

በአንፃሩ ደደቢቶች 80ኛው ደቂቃ ላይ የግብ ጠባቂው አንተነህ መሳን መውጣት ተከትሎ ከ30 ሜትር ርቀት ጌታነህ ከበደ ሞክሮ የግቡን አግዳሚ ታኮ የወጣው ሙከራ አስደንጋጭ የነበረ ሲሆን በስታዲዮሙ ነበረውን ተመልካችም በድንጋጤ ጸጥ ያሰኘች አጋጣሚ ነበረች ።

በቀሩት 10 ደቂቃዎች ደደቢቶች ከሜዳ ውጭ እንደመጫወታቸው የአቻ ውጤቱን ለማስጠበቅ በመከላከልና ሰአት የማባከን ታክቲክ ውስጥ በመግባት በሚፈልጉት መልኩ ጨዋታውን ተቆጣጥረው በአቻ ውጤት ማጠናቀቅ ችለዋል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *