ጋቦን የ2017 የቶታል አፍሪካ ዋንጫ አዘጋጅነትን ያገኘችው ሊቢያ ውድድሩን ለማዘጋጀት ባለመቻሏ ነበር፡፡
ከአምስት ዓመት በፊት ውድድሩን ከጎረቤቷ ኤኳቴሪያል ጊኒ ጋር በጣምራ ያዘጋጀችው ጋቦን አሁን ላይ የተሻሉ ተጫዋቾችን በስብስብ ደረጃ ይዛለች፡፡ የብሄራዊ ቡድን አሰልጣኟን ከወራት በፊት መቆየሯ ግን ብሄራዊ ቡድኑ ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ አለው፡፡ እንደአዘጋጅነቷ ብዙ ርቀት እንድትጓዝ ቢጠበቅባትም ከጋቦን እንደሚወጡ ዘገባዎች ከሆኑ ደጋፊው እምብዛም ትኩረቱን ልክ እንደ2012ቱ ውድድር ወደ ብሄራዊ ቡድኑ አላዞረም፡፡ ልጆቻቸውን ለአፍሪካ ዋንጫ ወደ ስታዲየም የሚወስዱ የወላጆች ቁጥርም ይቀንሳል ተብሏል፡፡ የሃገሪቱ ፕሬዝደንት አሊ ቦንጎ ኦንዲምባ ጥያቄ በሚያስነሳ ሁኔታ ዳግም መመረጣቸው በተነሳው ተቋውሞ እና የአፍሪካ ዋንጫው ለመተው በሚፈልጉ ወገኖች መሃከል ጥቋቁር ግስላዎቹ ከ2012 የተሻለ ውጤትን ለማምጣት ተስፋ ሰንቃለች፡፡
የአፍሪካ ዋንጫ ተሳትፎ ብዛት – 7
ውጤት፡ ሩብ ፍፃሜ (1996 እና 2012)
አሰልጣኝ፡ ሆዜ አንቶኒዮ ካማቾ
ጋቦን በምድብ አንድ ከካሜሮን፣ ቡርኪናፋሶ እና ጊኒ ቢሳው ጋር ተመድባለች፡፡ በአቋም መለኪያ ጨዋታ የሃገሪቱን ክለብ ሲኤፍ ሞናናን የገጠመው የካማቾ ስብስብ በጫና ውስጥ ሆኖ ወደ ውድድር እንደሚገባ የታወቀ ነው፡፡ ስፔናዊው ካማቾ ከቡድኑ ጋር በነበራቸው አጭር ቆይታም ከሜዳ ውጪ ከፌድሬሽኑ ጋር እየተጋጩ የአፍሪካ ዋንጫ ደርሷል፡፡ ከካማቾ በፊት የነበሩት ሆርጌ ኮስታ ከፌድሬሽኑ ጋር በነበራቸው ቅራኔ ተሰናብተዋል፡፡ ፌድሬሽኑ ፈረንሳዊው የቀድሞ የማሊ እና ማዜምቤ አሰልጣኝ ፓትሪስ ካርትሮንን ቢፈልግም ሳይሳካለት ለሶስት ዓመታ ከእግርኳስ አሰልጣኝነት እርቀው የነበሩትን የቀድሞ የሪያል ማድሪድ አሰልጣኝ ካማቾን ቀጥሯል፡፡
ተስፋ
አዘጋጅ እንደመሆኗ በርካታ ቁጥር ያለው ደጋፊ በሜዳ ተገኝቶ ቡድኑን ስለሚያበረታታ ይህ ለተጫዋቾች ትልቅ እገዛ ይሆናል፡፡ በአፍሪካ የወቅቱ ምርጥ አጥቂ ፒየር ኤምሪክ ኦባሚያንግን መያዙ ወደፊት ለመጓዝ የተሻለ እድል አለው፡፡ ወጥነት ያለው ስብስብ የጋቦን ሌላው ጥንካሬ ነው፡፡ ተጫዋቾች እምብዛም አለመለወጣቸው ቡድኑ በጎ ጎን ነው፡፡ ከኦባሚያንግ ባሻገር በዋይዳድ ካዛብላንካ እና አል አሃሊ የተሳካ ቆይታ የነበረው ማሊክ ኢቮና ኦባሚያንግን ግብ በማስቆጠሩ ረገድ ማገዝ መቻሉ ሌላው ለአሰልጣኝ ካማቾ ጥሩ ጎን ነው፡፡ የመክፈቻ ጨዋታዋን ልምድ ከሌላት ጊኒ ቢሳው ጋር ማድረጓ ደግሞ ሲታከልበት ለጥሩ ጅማሮ እንደመነሻሻ ይሆናል፡፡
ስጋት
የጋቦን ብሄራዊ ቡድን ችግሮች ብዙ ናቸው፡፡ የአሰልጣኝ ለውጥ በታህሳስ ወር ማድረጎ አሰልጣኝ ካማቾ የሚከተሉት የጨዋታ ፍልስፍና ተጫዋቾቻቸው ላይ ለማስረፅ ከብዷቸዋል፡፡ ያለው የፓለቲካ ሁኔታ ከጫናው ጋር ተደምሮ ውጤቷ ላይ ተፅዕኖ ሊያሳድር ይችላል፡፡ በኮስታ የአሰልጣኝነት ዘመን የኦባሚያንግ እና ኢቮና ጥምረት የዳበረ አለመሆን ሌላው የጋቦን ትልቅ ስጋት ነው፡፡ ቡድኑ ጫና የመቋቋም አቅሙ እስከየት ድረስ እንደሆነ ባይታወቅም ከ2012 የተሻለ ሆኖ ግን መቅረብ አለበት፡፡ ከ2015 የአፍሪካ ዋንጫ መጠናቀቅ በኃላ ቡድኑ የነጥብ ጨዋታ ያደረገው ሁለት ጊዜ ብቻ ነው፡፡ በሌሊቹ ጨዋታዎች የወዳጅነት ስለነበሩ ትክክለኛውን የቡድኑ ጥንካሬን ለማወቅ ለአሰልጣኞች ከብዷል፡፡ የአሁን አሰልጣኝ ካማቾ ኮስታ ይጠቀሙበት የነበረውን የ4-4-2 አሰላለፍ የሚጠቀሙ ከሆነ የቡድኑ ተገማችነት በይበልጥ ይጨምራል፡፡
የሚጠበቁ ተጫዋቾች
ጋቦን ልክ እንደከዚህ ቀደሙ ሁሉ ግብ የማስቆጠር ኃላፊነቱን ለኦባሚያንግ ጥላለች፡፡ የዶርትሙንድ አጥቂ ከአለማችን ምርጥ አጥቂዎች አንዱ ሲሆን የብሄራዊ ቡድን የምንግዜም ኮከብ ግብ አስቆጣሪ መሆኑ ካለው ወቅታዊ አቁሙ ጋር ተደምሮ ለተከላካዮች ፈተና ይሆናል፡፡ አሁን በቻይና እየተጫወተ የሚገኘው ኢቮናም እንደኦባሚያንግ ባይሆንም ለግብ ያለው ዓይን በጣም ጥሩ የሚባል ነው፡፡ በጣሊያን የሚጫወተው አማካዩ ማሪዮ ለሚና ከሳጥን ሳጥን የሜዳውን ክፍሎ አካሎ ለረጅም ደቂቃ መጫወት መቻሉ በጋቦን በኩል እንዲጠበቅ አድርጎታል፡፡ አዲስ መጪው ዴኒስ ቦአንጋም እድል ከተሰጠው ለሃገሩ ከፍተኛ ግልጋሎት መስጠት ይችላል፡፡ ዲዲዬ ንዶንግም ለአዘጋጇ ሃገር የአማካይ ስፍራ ይበልጥ ጥንካሬን ያላብሳል፡፡
የማጣሪያ ጉዞ
ጋቦን አዘጋጅ ስለሆነች በቀጥታ ለአፍሪካ ዋንጫው አልፋለች፡፡ ቢሆንም እንደወዳጅነት ጨዋታ ለመጠቀም በማሰብ ካፍ ጋቦንን በምድብ ከኮትዲቯር፣ ሱዳን እና ሴራሊዮን ጋር በምድብ 9 መድቧት ነበር፡፡
ሙሉ ስብስብ
ግብ ጠባቂዎች
ዲዲዬ ኦቮኖ (ኬቪ ኦስተንድ/ቤልጂየም)፣ የቪስ ቢትስኪ (ሲኤፍ ሞናና)፣ አንቶኒ ማፋ ሚዝዊ (ኔንት/ጋቦን)
ተከላካዮች
አሮን አፒንዳንጎይ (ስታደ ላቫሎስ/ፈረንሳይ)፣ ፍራንክ ኦማምቦ (አሶሴሽን ስፖርቲቭ ስታደ ማንጂ/ጋቦን)፣ ብሩኖ ኢቹል (ካርዲፍ ሲቲ/እንግሊዝ)፣ ዩሃን ኦቢያንግ (ሮይስ/ፈረንሳይ)፣ ሎይድ ፓልን (ሬድ ስታር/ፈረንሳይ)፣ ቤንጃሚን ዚ ኦንዶ (ሞስታ/ማልታ)፣ ዩሃን ዋቸር (ሰዳን/ፈረንሳይ)
አማካዮች
ኮምባ ታንጂጎራ (ሚዣን ሃካ/ቻይና)፣ ማሪዮ ለሚና (ጁቬንቱስ/ጣሊያን)፣ ሌቪ ማዲንዳ (ናስቲክ ታራጎና/ስፔን)፣ ጉሎር ካንጋ (ኤቷል ሮግ ደ ቤልግሬድ/ሰርቢያ)፣ ሳሞን ማቢንጉዊ (ራጃ ክለብ አትሌቲክ/ሞሮኮ)፣ ሰርጌ ንጎአሊ (ብሮማፖካርና/ስዊድን)፣ ዲዲዬ ንዶንግ (ሰንደርላንድ/እንግሊዝ)
አጥቂዎች
ፒየር ኤምሪክ ኦባሚያንግ (ቦሩሲያ ዶርቱሙንድ/ጀርመን)፣ ማሊክ ኢቮና (ቲያጂን ቴዳ/ቻይና)፣ አቡ አንጉኤ (ሊሪያ/ፖርቹጋል)፣ ሴድሪክ ኦንዶ ቢዮሂ (ሲኤፍ ሞናና/ጋቦን)፣ ዴኒስ ቡአንጋ (ቱርስ/ፈረንሳይ)
ጋቦን የምድብ የመክፈቻ ጨዋታዋን ጊኒ ቢሳውን ቅዳሜ በመግጠም ትጀምራለች፡፡