የቶታል 2017 የአፍሪካ ዋንጫ የምድብ አራት ጨዋታዎች በፖርት ጀንትል ተደርገዋል፡፡ ጋና ሙሉ ሶስት ነጥብ ይዛ የወጣችበትን ድል ዩጋንዳ ላይ ስታስመዘግብ ማሊ እና ግብፅ ነጥብ ተጋርተዋል፡፡
የምስራቅ አፍሪካዋ ብቸኛ ተወካይ ዩጋንዳ ከ39 ዓመታት በኃላ ለመጀመሪያ ግዜ በተሳተፈችበት የአፍሪካ ዋንጫ በጋና የ1-0 ሽንፈትን አስተናግዳለች፡፡ በመጀመሪያው አጋማሽ የጋና የበላይነት የታየ ሲሆን በተለይ የመስመር አማካዩ ክሪስቲያን አትሱ የክሬንሶቹን የተከላካይ ክፍል ወደ አደጋው ክልል በሚልካቸው ኳሶች ሲረብሽ ተስተውሏል፡፡ የቀድሞ የቅዱስ ጊዮርጊስ ተከላካይ አይዛክ ኢዜንዴ በጅያን አሰሞሃ ላይ በ31ኛው ደቂቃ በሰራው ጥፋት የተገኘውን የፍፁም ቅጣት ምትን አንድሬ አዩ አስቆጥሮ ብላክ ስታርሶቹን ለድል አብቅቷል፡፡
በሁለተኛው አጋማሽ አሰልጣኝ ሚቾ በመሃል ክፍሉ ላይ ጥሩ ያልነበረውን ማይክ አዚራን በሞሰስ ኦሎያ ከቀየሩ በኃላ ቡድኑ በተሻለ የአቻነት ግብ ለማግኘት ተጭኖ ተጫውቷል፡፡ በፋሩክ ሚያ፣ ቶኒ ማዌጄ እና ጅኦፍሪ ማሳ አማካኝነት ያልተሳኩ ሙከራዎች ማድረግም ችለዋል፡፡
ከጨዋታው ፍፃሜ በኋላ የጋናው አትሱ የጨዋታው ኮከብ ተጫዋች ተብሎ መርጧል፡፡
ማሊ እና ግብፅን ያገናኘው የምድቡ ሁለተኛ ጨዋታ ግብ ሳይቆጠርበት በአቻ ውጤት ተጠናቅቋል፡፡ ተመጣጣኝ ፉክክር በታየበት ጨዋታ ፈርኦኖቹ በጨዋታው መጀመሪያ የሙከራ የበላይነት ሲይዙ ንስሮቹም ለግብ የቀረቡ ሙከራዎች ሲያደርጉ ተስተውሏል፡፡ ማርዋን ሞሂሰን እና መሃመድ ኤልኒኒ በግብፅ በኩል ላሳና ኩሊባሊ እና ሙሳ ማሪጋ በማሊ በኩል ለግብ የቀረቡ ሙከራዎች ማደረግ ችለዋል፡፡
የግብፁ ግብ ጠባቂ አህመድ ኤል-ሸናዊ በ23ኛው ደቂቃ ኩሊባሊ በግንባሩ በመግጨት የሞከረውን ኳስ ለማዳን በመሞከር ሂደት ላይ በመጎዳቱ በኤሳል ኤል-ሃዳሪ ተቀይሮ ወጥቷል፡፡ የአራት ግዜ የአፍሪካ ዋንጫ አሸናፊዊው ኤል-ሃድሪ በ44 ዓመቱ ጨዋታው ማድረግ የቻለ ሲሆን በእድሜ አንጋፋው አፍሪካ ዋንጫው ላይ ለመጫወት የቻለ ተጫዋችም መሆን ችሏል፡፡
በሁለተኛው አጋማሽ የመጀመሪ ደቂቀቃዎች ሰባት ግዜ የአፍሪካ ዋንጫ አሸናፊዎቹ ተጭነው ቢጫወቱም ግብ ማስቆጠር ሳይችሉ ቀርተዋል፡፡
ካፍ የማሊው ሙሳ ማሪጋንየጨዋታው ኮከብ አድርጎ መርጦታል፡፡
የአፍሪካ ዋንጫው ዛሬም ሲቀጥል የምድብ አንድ 2ኛ ጨዋታዎች ዛሬ ይደረጋሉ፡፡ አዘጋጇ ጋቦን ቡርኪናፋሶን ምሽት 1፡00 ላይ እንዲሁም ካሜሮን ጊኒ ቢሳውን ምሽት 4፡00 ላይ ይገጥማሉ፡፡ ጨዋታዎች በጋቦን ርዕሰ መዲና ሊበርቪል በሚገኘው ስታደ አሚቴ ይደረጋሉ፡፡