ጋቦን 2017፡ ካሜሮን ምድብ አንድን መምራት ጀምራለች

ጋቦን በማስተናገድ ላይ ባለችው የቶታል 2017 የአፍሪካ ዋንጫ የምድብ አንድ ሁለተኛ ጨዋታዎች በሊበርቪል ስታደ አሚቴ ተደርገዋል፡፡ አዘጋጅዋ ጋቦን ከቡርኪናፋሶ ጋር አቻ ስትለያይ ካሜሮን ከኋላ ተነስታ ጊኒ ቢሳውን 2-1 ረታለች፡፡

ጋቦን የመጀመሪያ ሶስት ነጥብ ማሳካት ባቃታት ጨዋታ ከቡርኪናሶ ጋር 1-1 ተለያይታቸለች፡፡ ጨዋታውን በአራተኛ ዳኝነት የመራው ኢትዮጵያዊው ኢንተርናሽናል ባምላክ ተሰማ ነው፡፡ ሁለቱም ሃገራት በ2015 የኤኳቶሪያል ጊኒው የአፍሪካ ዋንጫ ከምድብ የተሰናበቱ ሲሆን ጥቋቁር አነሮቹ በፈረሰኞቹ ላይ በባለፉት ጥቂት ጨዋታዎች የበላይነትን መውሰድ ችለው ነበር፡፡ ተፅዕኖው ፈጣሪው የቡርኪናፋሶ ተጫዋች ጆናታን ፔትሮፒያ በጉዳት ከሜዳ መውጣቱን ተከትሎ ቀይሮት የገባው ፕሪጁስ ናኮልማ በመልሶ ማጥቃት የመጣውን ኳስ ተጠቅሞ ፈረሰኞቹን ቀዳሚ አድርጓል፡፡ ለግቡ መቆጠር የጋቦን ተከላካዮች ድክመት ከፍተኛ አስተዋፅኦ ነበረው፡፡

ጥቋቁር ነብሮቹ በመጀመሪያው አጋማሽ አቻ መሆን የሚችሉበትን አጋጣሚ በፍፁም ቅጣት ምት አግኝተው ፒየር ኤምሪክ ኦባሚያንግ ተጠቅሞበታል፡፡ ፍፁም ቅጣት ምቱ የተሰጠው የቡርኪናፋሶው ግብ ጠባቂ ካዎኮ ኮፊ ኦባሚያንግን በመጥለፉ ነበር፡፡

በሁለተኛው አጋማሽ በተጫዋቾች ቅያሪ እና ጉዳቶች እንደመጀመሪያው አጋማሽ ማራኪ እንቅስቃሴ ባይደረግም የተሻለ ፉክክር ታይቶበታል፡፡ የጋቦኑ ዴኒስ ቦአንጋ በ80ኛው ደቂቃ ከቅርብ ርቀት አግኝቶ የሞከረውን አስደንጋጭ ሙከራ ኮፊ በድንቅ ሁኔታ ያመከነበት በሁለተኛው አጋማሽ ከተደረጉ ሙከራዎች ተጠቃሽ ነው፡፡ ጨዋታው በአቻ ውጤት መጠናቀቁን ተከትሎ ሃገራቱ ወደ ቀጣይ ዙር የማለፍ እድላቸውን ማጥበብ ጀምረዋል፡፡ የጨዋታው ኮከብ ሆኖ በካፍ የተመረጠው የጋቦኑ ዴኒስ ቦአንጋ ነው፡፡

ካሜሮን የጨዋታ ብልጫ በወሰደችበት የምድቡ ሁለተኛ ግጥሚያ ጊኒ ቢሳውን 2-1 በማሸነፍ የምድቡ መሪነትን መጨበጥ ችላለች፡፡ የማይበገሩት አናብስቶቹ ከ2010 ወዲህ በአፍሪካ ዋንጫው ማሸነፍ ሲችሉ ይህ የመጀመሪያቸው ነው፡፡ ሶስት ግሩም ግቦች በተስተናገዱበት ጨዋታ የግብ ማግባት ቅድሚያውን የያዙት ተኩላዎቹ ነበሩ በፒኩዊቲ አማካኝነት፡፡ ፒኩዊቲ ከመሃል ሜዳ ኳስን ይዞ በመምጣት ሶስት የካሜሮን ተጫዋቾችን ካለፈ በኃላ ኳስን እና መረብ አገናኝቷል፡፡ ካሜሮች አቻ ለመሆን ሲጥሩ ጊኒ ቢሳዎች ያስቆጠሯትን ግብ በማስጠበቅ እና በመልሶ ማጥቃት ሲጫወቱ ተስተውሏል፡፡

በሁለተኛው አጋማሽ የካሜሮን አሰልጣኝ ሁጎ ብሮስ ክሊንተን ንጂን በቶኮ ኢካምቢ ያደረጉት ለውጥ ውጤት አምጥቶላቸዋል፡፡ ሰባስቲያን ሲያኒ ከቤንጃሚን ሙካንጆ የተቀበለውን ኳስ በግሩም ሁኔታ አክርሮ በመምታት ኳሜሮንን አቻ ሲያደርግ ተከላካዩ ሚካኤል ንጋዱ የማሸነፊያዋን ግብ አስቆጥሯል፡፡ የጨዋታው ኮከብ ተብሎ በካፍ የተመረጠው ለሁለተኛው የካሜሮን ግብ መቆጠር ቁልፍ የነበረው ክሪስቲያን ባሶጎግ ነው፡፡ ምድቡን ካሜሮን ስትመራ ጋቦን እና ቡርኪናፋሶ በሁለት ነጥብ ተከታዮቹን ደረጃዎች ይዘዋል፡፡

የምድብ ጨዋታዎች ሐሙስም ሲቀጥሉ የሰሜን አፍሪካዎቹ ተቀናቃኞች አልጄሪያ እና ቱኒዚያ ምሽት 1፡00 ላይ ሲገናኙ ዚምባቡዌ ከሴኔጋል ምሽት 4፡00 ላይ ይጫወታሉ፡፡ ጨዋታዎቹ በፍራንስቪል የሚደረጉ ይሆናሉ፡፡

ፎቶ – AFP

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *