ጋቦን 2017፡ ሞሮኮ ድል ሲቀናት ዲ.ሪ. ኮንጎ እና ኮትዲቯር ነጥብ ተጋርተዋል

የ2017 ቶታል የአፍሪካ ዋንጫ በኦየም ከተማ በተደረጉ ሁለት የምድብ ሶስት ጨዋታቸው ሲቀጥል የወቅቱ አሸናፊ ኮትዲቯር ከዲ.ሪ. ኮንጎ ጋር 2 አቻ ስትለያይ ሞሮኮ ቶጎን 3-1 ረታለች፡፡

ዲ.ሪ. ኮንጎ ከኮትዲቮር በተፋለሙበት ጨዋታ 2-2 ተለያይተዋል፡፡ በ28 ደቂቃዎች ውስጥ በዘንድሮው አፍሪካ ዋንጫ ባልተለመደ መልኩ ሶስት ግቦችን ባስተናገደው ጨዋታ የተደራቢ አጥቂነት ሚናን በአሰልጣኝ ፍሎረንት ኢቤንጌ የተሰጠው ኒስከንስ ኬባኖ ነብሮቹን ቀዳሚ ያደረገች ግብ በዝሆኖቹ ግብ በስተቀኝ በኩል አስቆጥሯል፡፡ ዌልፍሬድ ቦኒ ከማዕዘን ማክስ ግራድል ያሻገረለትን ኳስ ተጠቅሞ በግንባሩ በመግጨት ሃገሩን አቻ ቢያደርግም ሞሮኮ ላይ ኮንጎ ድል እንድትቀዳጅ ያስቻለው አመካዩ ጁኒየር ካባናጋ በግንባሩ መግጨት ዳግም መሪነቱን ለነብሮቹ መልሷል፡፡ ቡድኖቹ ወደ መልበሻ ክፍል ለዕረፍት እስኪያመሩ ድረስ የተሻለ መንቀሳቀስ የቻለችው ኮንጎ ነበረች፡፡

በሁለተኛው አጋማሽ የአቻነት ግብ ለማግኘት ተጭነው የተጫወቱት ኮትዲቯሮች ኳስን ቢቆጣጠሩም ወደ ግብ በመሞከር ረገድ ግን እምብዛም አልነበሩም፡፡ አማካዩ ሴሬ ዴይ ከሳጥኑ ውጪ ወደ ግብ የላከው ኳስ በኮንጎ ተከላከይ ተጨርፋ ዝሆኖቹን አቻ አድርጋለች፡፡ ተቀይሮ ወደ ሜዳ የገባው ሰለሞን ካሉ በመጨረሻዎቹ ደቂቃዎች ግብ ቢያስቆጥርም ከጨዋታ ውጪ አቋቋም ላይ በመገኘቱ ግቡ ሳይቀፀድቅ ቀርቷል፡፡ ኮንጎ ፈረመን ሙቤሌ እንዲሁም ኮትዲቯር በሰርጅ ኦሪየር ግብ ማስቆጠር የሚችሉበትን እድሎች በሁለተኛው አጋማሽ አግኝተው አምክነዋል፡፡ የኮትዲቯሩ ሰሬ ዴይ በካፍ የጨዋታው ኮከብ ሆኖ ተመርጧል፡፡

በምድቡ ሁለተኛ ጨዋታ ሞሮኮ ቶጎን 3-1 በማሸነፍ ሙሉ ሶስት ነጥብ ማሳካት ችላለች፡፡ ሞሮኮ በዘንድሮው የአፍሪካ ዋንጫ ሶስት ግቦች በእንድ ጨዋታ ማስቆጠር የቻለች የመጀመሪያዋ ሃገር ሁናለች፡፡ ግብ በማስቆጠር ቅድሚያውን የያዙት ቶጎዎች ነበሩ፡፡ በ5ተኛው ደቂቃ ማቲዩ ዶሲቪ በጥሩ የመልሶ ማጥቃት የመጣውን ኳስ ወደ ግብነት ቀይሮ ቶጎን ቀዳሚ አድርጓል፡፡ የአትላስ አናብስቶቹ በ14ኛው ደቂቃ አዚዝ ባሃዶዝ በግንባር በመግጨት ኳስ እና መረብን ሲያገናኝ ሮሜን ሳኢስ ሁለተኛዋ ግብ ከሳባት ደቂቃ በኃላ አክሏል፡፡ ቶጎ በሁለተኛው አጋማሽ በኤማኑኤል አዲባዮር ለግብ የቀረበ ሙከራ ማድረግ ስትችል በ71ኛው ደቂቃ የሞሮኮው የፊት መሰመር ተሰላፊ የሱፍ ኤ-ነስሪ ከሳጥኑ ውጪ የመታው ኳስ ልምድ ያለው የቶጎው ግብ ጠባቂ አጋሳ ድክመት ታክሎበት መርቡ ውስጥ አርፎ ለአትላስ አናብስቶቹ ሶስተኛ ግብ ሆኖ ተመዝግቧል፡፡ ነስሪ ከየሱፍ ኤል አረቢ ቀድሞ በቋሚ አሰላለፉ ውስጥ መግባቱ ብዙዎችን እያነጋገረ ነው፡፡ የቶጎው ፍሎይድ አይቴ ውጤቱን የሚያጠብበት እድል እግኝቶ ሳይጠቀምበት ኳሷን ወደ ውጪ ሰድዷታል፡፡ ፋይሰል ፋጃር ሁለት ግብ የሆኑ ኳሶችን አመቻችቶ በማቀበል ወሳኝ ሚናን በጨዋታው ተወጥቷል፡፡ በካፍ የጨዋታው ኮከብ ተብሎም ፈይሰል  ተመርጧል፡፡

ሁለቱን ጨዋታዎች ተከትሎ ዲ.ሪ. ኮንጎ ምድቡን በአራት ነጥብ ስትመራ ሞሮኮ በሶስት ትከተላለች፡፡ኮትዲቯር እና ቶጎ በሁለት አና አንድ ነጥብ ተከታዮቹን ደረጃዎች ይዘዋል፡፡ በምድብ አራት ቅዳሜ ጋና ማሊን ምሽት 1፡00 ላይ እንዲሁም ዩጋንዳ ግብፅን ምሽት 4፡00 ላይ ትገጥማለች፡፡ ጨዋታዎች በፓርት ጀንትል ይደረጋሉ፡፡

የፎቶ ምንጭ – AFP, Gallo

 

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *