የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 13ኛ ሳምንት ዛሬ በተደረጉ ጨዋታዎች ሲጀምር አበበ ቢቂላ ስታዲየም ላይ አዲስ አበባ ከተማን የገጠመው ኢትዮጵያ ቡና 1-0 በማሸነፍ ደረጃውን ማሻሻል ችሏል።
ጨዋታው ከ8 ተከታታይ ጨዋታዎች ሽንፈት በኋላ ባሳለፍነው ሳምንት ወላይታ ድቻን ከሜዳው ውጪ ማሸነፍ የቻለው አዲስ አበባ ከተማ እና አሠልጣኝ ኒቦሳ ቩሴቪችን ካሰናበተ በኋላ ከሶስት ጨዋታዎች 7 ነጥብ ይዞ ወደ መሪዎቹ መጠጋት የቻለው ኢትዮጵያ ቡና መሀል የተደረገ ነበር።
ኢትዮጵያ ቡና ጨዋታው ከመጀመሩ አንስቶ ግብ ለማስቆጠር ጫና አድርጎ የተጫወተ ሲሆን አዲስ አበባ ከተማዎች በአንፃሩ በመልሶ ማጥቃት የግብ ዕድሎችን መፍጠር ችለዋል። በጨዋታው 3ኛ ደቂቃ አብዱልከሪም ሀሰን ከግቡ በቀኝ በኩል ያገኘውን ኳስ አየር ላይ እንዳለ በቮሊ መትቶ ግብ ጠባቂው ደረጄ አለሙ የያዘበት ሙከራ የጨዋታው የመጀመሪያ ዒላማውን የጠበቀ ሙከራ ነበር።
በ10ኛው ደቂቃ የአዲስ በአበባ ከተማው አማካይ ዮናታን ብርሃነ በጉዳት ጨዋታውን መቀጠል ባለመቻሉ አሠልጣኝ ስዩም ከበደ ዘሪሁን ብርሃኑን ቀይረው ለማስገባት ተገደዋል። ኢትዮጵያ ቡናዎች ከርቀት ወደግብ በመምታት ግብ ለማስቆጠር የሞከሩ ሲሆን አስቻለው ግርማ በ15ኛው ደቂቃ፣ እንዲሁም ኤፍሬም ወንድወሰን በ35ኛው ደቂቃ ያደረጓቸው ሙከራዎችም ለግብ የቀረቡ ነበሩ። ኃይሌ እሸቱ ከቡናው ግብ ጠባቂ ጋር ፊት ለፊት ተገናኝቶ ሃሪስተን የመለሰበት ኳስ በአዲስ አበባ ከተማ በኩል የሚጠቀስ ሙከራ ነበር።
በ25ኛው ደቂቃ ፀጋ አለማየሁ በሃሪስተን ተጠልፏል በሚል የአዲስ አበባ ከተማ ተጫዋቾች ፍፁም ቅጣት ምት እንዲሰጣቸው ቢጠይቁም የመሃል ዳኛው ለሁለቱ ተጫዋቾች የህክምና ዕርዳታ ከተደረገ በኃላ ጨዋታው አስቀጥለዋል።
ኢትዮጵያ ቡናዎች በሁለተኛው አጋማስ ላለፉት 3 ጨዋታዎች በጉዳት ያልተሰለፈው አህመድ ረሺድን ቀይረው ያስገቡ ሲሆን ከመጀመሪያው አጋማሽ በተሻለ ኳስን ተቆጣጥረው እና በቁጥር በርከት ብለው ወደግብ በመድረስ መጫወት ችለዋል። አስቻለው ግርማ እና ሳሙኤል ሳኑሚ በሁለተኛው የጨዋታ ክፍለጊዜ የመጀመሪያ ደቂቃዎች ሙከራዎችን ቢያደርጉም ደረጄ አለሙን አልፎ በአዲስ አበባ ከተማ መረብ ላይ ያረፈ ኳስ አልነበረም።
አዲስ አበባ ከተማዎች በመልሶ ማጥቃት የግብ ዕድሎችን የፈጠሩ ሲሆን በ61ኛው ደቂቃ እንየው ካሳሁን ከሳጥኑ ውጪ የመታው ኳስ የግቡን ቋሚ ለትሞ ሲመለስ ኤፍሬም ቀሬ አግኝቶት በማይታመን ሁኔታ ሳይጠቀምበት የቀረው የሚያስቆጭ አጋጣሚ ነበር። ጫና ፈጥረው መጫወት የቀጠሉት ኢትዮጵያ ቡናዎች በጋቶች ፓኖም እና ኤልያስ ማሞ አማካኝነት ከርቀት ተጨማሪ ሙከራዎችን ማድረግ ችለዋል።
በጨዋታው 67ኛ ደቂቃ አህመድ ረሺድ ከቀኝ መስመር ያሻማውን ኳስ ዘንድሮ ክለቡን የተቀላቀለው እና በውድድር ዘመኑ አጋማሽ በውሰት ወደ ሀዋሳ ከተማ ሊያመራ እንደሚችል ሲነገር የቆየው ሳሙኤል ሳኑሚ በግንባሩ ገጭቶ በማስቆጠር ኢትዮጵያ ቡናን መሪ አድርጓል።
በጨዋታው ቀሪ ደቂቃዎች በሁለቱም በኩል ከርቀት የተደረጉ ሙከራዎች ውጤታማ ያልነበሩ ሲሆን በ86ኛው ደቂቃ እያሱ ታምሩ አማኑኤል ያሻገረለትን ኳስ ከግብ ጠባቂው ጋር ተገናኝቶ ደረጄ ያወጣበት አጋጣሚ የጨዋታው የመጨረሻ ግልፅ የግብ ዕድል ነበር።
ኢትዮጵያ ቡና ጨዋታውን ማሸነፉን ተከትሎ በ13 ጨዋታ 20 ነጥብ በመሰብሰብ ከመሪው አዳማ በ4 ነጥብ ብቻ አንሶ ደረጃውን ወደ 6ኛ ያሻሻለ ሲሆን አዲስ አበባ ከተማ በአንፃሩ በ8 ነጥብ እና 8 የግብ ዕዳ 15ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል።