የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 13ኛ ሳምንት ላይ ሲደርስ በመጀመሪያ ቀን ውሎው ባስተናገደው ሶስተኛ ጨዋታ መከላከያ እና ፋሲል ከተማ ነጥብ ተጋርተዋል።
እንደተለመደው ቡድናቸውን እየተዘዋወሩ የሚደግፉት የፋሲል ከተማ ደጋፊዎች በካታንጋ በብዛት እንዲሁም በሌሎቹም የስታድየሙ የተለያዩ ክፍሎች ተገኝተው ገና ጨዋታው ከመጀመሩ በፊት ጀምሮ በሚያሰሙት ድጋፍ ታጅቦ ነበር ጨዋታው የተጀመረው።
ምንም እንኳን በጨዋታው የመጀመሪያ ደቂቃዎች ላይ ፋሲል ከተማዎች የኳስ ቁጥጥር ብልጫውን ቢወስዱም በሙከራ ግን ቅድሚያውን የወሰዱት መከላከያዎች ነበሩ። ሙከራውም 6ኛው ደቂቃ ከሽመልስ ተገኝ የርቀት ቅጣት ምት የተነሳ ሲሆን ምንተስኖት አደጎ እና የግቡ አግዳሚ በአንድ ላይ ጎል ከመሆን ታድገውታል ።
በ12ኛው ደቂቃ ላይ ምንተስኖት አደጎ ሳሙኤል ታዬን በእግሩ ለማለፍ ሲሞክር የተነጠቀውን ኳስ ሳሙኤል ታዬ ሳታት እንጂ ሌላ ጎል መሆን የምትችልበት አጋጣሚ ነበረች ። ይህ ከመሆኑ አንድ ደቂቃ ቀደም ብሎም ኄኖክ ገምቴሳ ከኤርሚያስ ኃይሉ ጥሩ ኳስ ደርሶት ግብ ለማስቆጠር ቢቃረብም በአቤል ማሞ ጥረት ሳይሳካ ቀርቶ ነበር ።
ፋሲሎች በኳስ ቁጥጥሩ ብልጫ ወስደው የጎል እድሎችን ለመፍጠር እየሞከሩ መከላከያዎችም በፈጣን እንቅስቃሴ እና በረጃጅም ኳሶች ወደግብ ለመድረስ እየጣሩ ፣ በጉሽሚያዎች የታጀበ ጥሩ የጨዋታ ፍሰት እየታየ ነበር በ28ኛው ደቅቃ ፋሲሎች በአብዱርሀማን ሙባረክ ጎል ቀዳሚ የሆኑት። አብዱርሀማን ከመከላከያ ፍፁም ቅጣት ምት ክልል ውጪ ላስቆጠራት ጎል የሶስቱ የፋሲል የፊት አጥቂዎች ፈጣን ቅብብል ወሳኝ ሚና ነበረው።
በጥሩ የመሸናነፍ ፉክክር የቀጠለው የመጀመሪያ ግማሽ ሊጠናቀቅ 10 ደቂቃዎች ሲቀሩት የጦሩ የፊት አጥቂ ማራኪ ወርቁ ከአማካዩ ሳሙኤል ታዬ የተሻገረለትን ኳስ ከፋሲሎች የተከላካይ መስመር ጀርባ ይዞ በመግባት የአቻነቷን ጎል አስመዝግቧል።
በተቀሩት ደቂቃዎች ሁለቱ ቡድኖች ፈጠን ባለ አጨዋወት አንዳቸው አንዳቸውን እየፈተኑ ለተመልካች የሚያዝናና መልካም ጨዋታ አሳይተዋል ። ሆኖም ግን ተደጋጋሚ ቅጣት ምቶች እና የቢጫ ካርዶችን እንጂ ሁለተኛ ግብ በሁለቱም በኩል ሳንመለከት ተጨዋቾቹ ለእረፍት ወደ መልበሻ ክፍል አምርተዋል ።
ሁለተኛው አጋማሽ ሲጀመር ከመጀመሪያው በተለየ ጨዋታው ቀዝቀዝ ያለ ይመስል ነበር። በ 50ኛው ደቂቃ ላይ በመጀመሪያው ግማሽ አላስፈላጊ ግርግር ፈጥሮ ቢጫ ካርድ ተመልክቶ የነበረው የመከላከያው አጥቂ ምንይሉ ወንድሙ በፍፁም ቅጣት ምት ክልል ውስጥ ተጠለፍኩ ብሎ ሲወድቅ ፌደራል አልቢትር አሸብር ሰቦቃ ሆን ብለህ ነው በማለት ቅጣት ምቱን በተቃራኒው ለፋሲሎች አድርገውታል። በዚህም የተነሳ ምንይሉ በፈጠረው ሰጣ ገባ በሁለተኛ ቢጫ ካርድ ከሜዳ ተወግዷል ። ዘግየት ብሎም መከላከያዎች ውሳኔውን በመቃወም ክስ አስይዘዋል።
በሂደት መጀመሪያ ወደነበረው ፉክክር የተመለሰው ጨዋታም ሰለሞን ገ/መድህን በኤፍሬም አለሙ እንዲሁም ፍቅረሚካኤል ዓለሙን በይስሀቅ መኩሪያ በመተካት የመሀል ክፍላቸውን ባጠናከሩት ፋሲሎች የመስመር አጥቂ አብዱርሀማን ሙባረክ አማካይነት ሁለተኛ ጎል አስተናግዷል ። ኄኖክ ገምቴሳ በአስገራሚ ሁኔታ ከመሀል ሜዳ በአየር ላይ ያሳለፈውን ኳስ ነበር የአምናው የከፍተኛ ሊግ ኮከብ ተጨዋች በአግባቡ የተጠቀመባት።
ከጎሏ በኃላ የፋሲል ከተማዎች መሀል ክፍል ሶስት ማዕዘናዊ ቅርፅ ተገልብጦ ፍቅረሚካኤል አለሙ እና ሔኖክ ጋምቴሳ ከተከላካይ መስመሩ ፊት መታየት መጀመራቸው ቡድኑ ውጤት ለማስጠበቅ ያሰበ ቢያስመስለውም የመስመር ተከላካዮቹ የማጥቃት እንቅስቃሴ እና በድንገት የሚጀምረው መልሶ ማጥቃታቸው ሶስተኛ ጎል እየፈለጉ እንደሆነ የሚናገር ነበር። በዚሁ የፋሲሎች የማጥቃት ፍላጎት መነሻነት መሀል ሜዳ ላይ መከላከያዎች ያቋረጡት ኳስ በሳሙኤል ሳሊሶ አማካይነት ከቀኝ መስመር ተሻምቶ በየመጀመሪያውን ጎል አመቻችቶ ለማራኪ ወርቁ ባቀበለው ሳሙኤል ታዬ ብቃት ወደጎልነት ተቀይሯል።
የጨዋታው 2-2 መሆን እና የሰዐቱን መግፋት ተከትሎም በጎዶሎ ተጨዋች እየተጫወተ የነበረው መከላከያ በመጠኑ ወደኋላ በማፈግፈግ አልፎ አልፎ የመልሶ ማጥቃት እድሎችን ለመጠቀም ሲሞክር አፄዎቹም በበኩላቸው ሁለቱን መስመሮቻቸውን እንዲሁም የመሀል ሜዳ ቀጥተኛ ኳሶች ላይ ተመስርተው ጥቃቶችን ሰንዝረዋል። በጨዋታው መጠናቀቂያ አካባቢም የመስመር አጥቂው ኤርምያስ ኃይሉ በመከላከያዎች ፍፁም ቅጣት ምት ክልል ውስጥ ተጠልፎ ሲወድቅ የፍፁም ቅጣት ምት ይገባን ነበር በማለት ተጨዋቾቹ ቅሬታቸውን በአልቢትር አሸብር ሰቦቃ ላይ አሰምትዋል ።
ጨዋታው ሊጠናቀቅ ሽርፍራፊ ሰከንዶች ሲቀሩት ኤርሚያስ ኃይሉ አክርሮ ከመከላከያዎች ሳጥን ጠርዝ ላይ የሞከረው እና አቤል ማሞ በድንቅ ብቃት ያመከነው ኳስ ለአፄዎቹ የምታስቆጭ አጋጣሚ ሆና አልፋለች። ይህም ኳስ መጀመሪያ በእጅ ተነክቶ ስለነበር ፍፁም ቅጣት ምት ተከልክለናል በማለት የዳኛው ውሳኔ አሁንም በአጼዎቹ ዘንድ ተቀባይነትን አላገኘም። በዚህም መሰረት አዝናኝ የነበረው የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ 4 ጎሎችን እና 1 አወዛጋቢ ቀይ ካርድ አስመልክቶን ተጠናቋል።
የጨዋታውን ውጤት ተከትሎ ፋሲል ከተማ በ20 ነጥብ 5ኛ ላይ ሲቀመጥ መከላከያ በ18 ነጥብ 7ኛ ላይ ተቀምጧል፡፡