ጋቦን 2017፡ ግብፅ ምድብ አራትን በመሪነት አጠናቅቃለች

​የቶታል 2017 የአፍሪካ ዋንጫ የምድብ ጨዋታዎች ዕረቡ ምሽት በተደረጉ ሁለት ጨዋታዎች ተጠናቅቀዋል፡፡ ግብፅ ጋናን በማሸነፍ ምድብ አራትን በመሪነት ስታጠናቅቅ ከዩጋንዳ ጋር ነጥብ የተጋራችው ማሊ ከምድብ ማለፍ አልቻለችም፡፡

ግብፅ ጋናን 1-0 በሆነ ውጤት በማሸነፍ ወደ ሩብ ፍፃሜው አምርታለች፡፡ ጋና አስቀድማ በማለፏ የማሸነፍ ወይም አቻ የመውጣት ጫና ውስጥ የነበሩት ፈርኦኖቹ ነበሩ፡፡ መሃመድ ሳላህ በቅጣት ምት ያስቆጠረው ግብ የቡድኖቹ ልዩነት ሆኗል፡፡ በሁለተኛው አጋማሽ ጋና ባዱ እና ጆርዳን አዩ ያደረጉት የግብ ማግባት ሙከራዎች በግብፁ ግብ ጠባቂ ኤሳም ኤል ሃዳሪ ጥረት ግብ ከመሆን ድነዋል፡፡ የግብፁ የመሃል ተከላካይ አህመድ ሄጋዚ የጨዋታው ኮከብ ተብሎ ተመርጧል፡፡ ውጤቱን ተከትሎ ግብፅ ጋናን በመብለጥ ምድቡን በመሪነት ጨርሳለች፡፡ ግብፅ አንድም ግብ ያላስተናገደች ብቸኛዋም ሃገር ነች፡፡

አስቀድማ መውደቋን ያረጋገጠችው ዩጋንዳ ከማሊ ጋር 1-1 ተለያይታለች፡፡ ከክሬንሶቹ እራሱን ለማግለል እያሰበ እንደሆነ የተነገረለትን ዴኒስ ኦኒያንጎ ተክቶ የቅዱስ ጊዮርጊሱ ሮበርት ኦዶንካራ የዩጋንዳን ግብ ጠብቋል፡፡ በመጀመሪያው አጋማሽ ውሃ በያዘው ሜዳ ላይ ቡድኖቹ ለመጫወት ሲቸገሩ ተስተውሏል፡፡ ፋሩክ ሚያ በ70ኛው ደቂቃ ዩጋንዳን መሪ ሲያደርግ የቪስ ቢሶማ ንስሮቹን ከሶስት ደቂቃ በኃላ በግሩም ግብ አቻ አድርጓል፡፡ ሁለቱም ሃገራት ከምድብ ማለፍ አልቻሉም፡፡ የዩጋንዳው ፋሩክ ሚያ የጨዋታው ኮከብ ተብሎ ተምረጧል፡፡

የሩብ ፍፃሜ ጨዋታዎች ቅዳሜ የሚጀምሩ ይሆናል፡፡

ቅዳሜ ጥር 20/2009

1፡00 – ቡርኪናፋሶ ከ ቱኒዚያ (ስታደ አሚቴ)

4፡00 – ሴኔጋል ከ ካሜሮን (ስታደ ፍራንስቪል)

ዕሁድ ጥር 21/2009

1፡00 – ዲ.ሪ. ኮንጎ ከ ጋና (ስታደ ኦየም)

4፡00 – ግብፅ ከ ሞሮኮ (ስታደ ፖርት ጀንትል)


የፎቶ ምንጭ፡ BackpagePix

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *