ፋሲል እና ሐዋሳ የሊጉ ተስተካካይ ጨዋታቸውን በድል ተወጥተዋል

የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የሁለተኛ ሳምንት ተስተካካይ ጨዋታዎች ዛሬ ጎንደር እና አዲስ አበባ ላይ ተደርገዋል፡፡ ፋሲል ከተማ ወደ መሪዎቹ የተጠጋበትን ድል ወላይታ ድቻ ላይ ሲያስመዘግብ ሐዋሳ ከተማ በበኩሉ ከወራጅ ቀጣናው የወጣበትን ወሳኝ ነጥብ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክን በማሸነፍ ማሳካት ችሏል፡፡

ፋሲለደስ ስታደየም ላይ ወላይታ ድቻን ያስተናገደው ፋሲል ከተማ 2-0 አሸንፏል፡፡ አፃዎቹ በጥር ወር መንሸራተትን ቢያሳዩም በተከታታይ በሜዳቸው ያደረጓቸውን ሁለት ጨዋታዎች ማሸነፋቸው ደረጃቸውን እንዲያሻሻሉ ረድቷቸዋል፡፡ ቁጥሩ የበዛ ተመልካች በተከታተለው ጨዋታ ይሳቅ መኩሪያ በ28ኛው ደቂቃ ፋሲልን መሪ ያደረገች ግን ከመረብ አዋህዷል፡፡ ከዕረፍት መልስ በወሩ ጥሩ እንቅስቃሴ በማድረግ ላይ የሚገኘው አብዱልራህማን ሙባረክ በ64ኛው ደቂቃ ኳስ እና መረብን አገናኝቶ አፃዎቹን ለድል አብቅቷል፡፡ ፋሲል ከተማ በደረጃ ሰንጠረዡ በ26 ነጥብ አዳማ ከተማን በግብ ክፍያ በመብለጥ ሶስተኛ ሆኗል፡፡ ከከፍተኛ ሊጉ ያደገው ክለቡ በዘንድሮው የሊግ ክስተት መሆኑን ቀጥሏል፡፡

ከወራጅ ቀጣናው ለመውጣት አዲስ አበባ ስታዲየም ላይ ሐዋሳ ከተማን የገጠመው ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ 2-0 ተሸንፏል፡፡ በተከታታይ ሽንፈቶችን ያስተናገደው ባንክ በመጀመሪያው አጋማሽ ከሐዋሳ የሚሰነዘሩበትን ጥቃቶች በመመለስ ጥሩ ነበር፡፡ ንግድ ባንክ በፒተር ንዋድኬ እንዲሁም ሐዋሳ በዳንኤል ደርቤ አማካኝነት ለግብነት የቀረቡ ሙከራዎች አድርገዋል፡፡ በሁለተኛው አጋማሽ የእንግዶቹ የመሃል ክፍል ወደፊት ተጠግቶ መጫወቱ ፍሬ አፍርቶ ታፈሰ ሰለሞን ከቀኝ መስመር ወደ አደጋ ክልሉ የላከውን ኳስ የንግድ ባንኩ የመሃል ተከላካይ ቢኒያም ሲራጅ በራሱ ግብ ላይ አስቆጥሯል፡፡ ከ12 ደቂቃዎች በኃላ ቶጎዋዊው አረፋት ጃኮ ሁለተኛውን ግብ አሁንም ከታፈሰ ሰለሞን የተቀበለውን ኳስ ተጠቅሞ አስመዝግቧል፡፡ ውጤቱን ተከትሎ ሐዋሳ ከተማ በ14 ነጥብ ከወራጅ ቀጠናው በአንድ ደረጃ ከፍ ብሎ 13ተኛ ሲሆን ጅማ አባ ቡና እና ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በእኩል 13 ነጥብ በግብ ክፍያ ተበላልጠው 14ኛ እና 15ኛ ደረጃ ላይ ይገኛሉ፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *