የሴቶች ዝውውር ፡ ድሬዳዋ ከተማ 11 ተጫዋቾችን አስፈርሟል  

በ2010 የሴቶች ፕሪምየር ሊግ በአዲሱ የመወዳደሪያ ደንብ መሰረት በአንደኛው ዲቪዚዮን የሚወዳደረው ድሬዳዋ ከተማ በዝውውር መስኮቱ በርካታ ተጨዋቾችን ማጣቱን ተከትሎ በርካታ አዳዲስ ተጫዋቾችን በማስፈረም ክፍተቱን ለመድፈን በመጣር ላይ ይገኛል፡፡

በአሰልጣኝ ፍስሀ ጥዑመልሳን የሚመሩት ድሬዳዋዎች 11 ተጨዋቾችን ማስፈረማቸው ሲገለፅ አሁንም ግን በሌሎች ክፍተት አለብን ብለው በሚያምኑበት ቦታዎች ላይ ተጨማሪ ተጨዋቾችን ለማስፈረም እንቅስቃሴ ላይ እንደሆኑ ለማወቅ ተችሏል።

ለክለቡ ፊርማቸውን ካኖሩ ተጫዋቾች መካከል በኢትዮጵያ ሴቶች እግርኳስ ላይ ስማቸው ጎልቶ ከሚነሱ ተጫዋቾች አንዷ የሆነችው ብዙሀን እንዳለ ትገኝበታለች፡፡ ከንግድ ባንክ ጋር 3 የፕሪምየር ሊግ ዋንጫን በአምበልነት ያነሳችውና የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን አምበል የነበረችው ብዙሀን ከአንድ ወር በፊት አምቦ ላይ በተሰጠ የካፍ ሴት አሰልጣኞች ሲ ላይሰንስ ስልጠና መካፈሏ የሚታወስ ነው፡፡

በተጠናቀቀው የውድድር አመት ሲዳማ ቡናን ለቃ አዲስ አበባን የተቀላቀለችውና የክለቡ ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪ ሆና ያጠናቀቀችው ተራማጅ ተስፋዬ እና በደደቢት ዘንድሮ በበርካታ ጨዋታዎች ቋሚ ሆና የተሰለፈችው ግብ ጠባቂዋ ፍሬወይኒ ገብሩ ሌሎች ለክለቡ የፈረሙ ልምድ ያላቸው ተጫዋቾች ናቸው፡፡

ድሬዳዋ ከላይ ከተጠቀሱት በተጨማሪ ከአርባምንጭ ከተማ ትዝታ ፈጠነ ፣ ቱፊት ካዲዮ እና መስከረም ኢሳያስን ሲያስፈርም ዘንድሮ ከኢትዮጵያ ወጣቶች ስፖርት አካዳሚ የስልጠና ጊዜያቸውን በማጠናቀቅ ተመርቀው የወጡት ነብያት ሀጎስ ፣ ያአብስራ ይታይህ ፣ ሰናይት መኩርያ ፣ ፀጋነሽ ተሾመ እና ዳሳሽ ሰውአገኝ ለክለቡ መፈረም ችለዋል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *