​ኢትዮ ኤሌክትሪክ እና መከላከያ በአቻ ውጤት አመቱን ጀምረዋል

የሊጉን የመጀመሪያ ጨዋታቸውን ያደረጉት ኢትዮ ኤሌክትሪክ እና መከላከያ ጥሩ ፉክክር ባሳዩበት ምሽት በተቆጠሩ ሁለት ማራኪ  ጎሎች 1-1 ተለያይተዋል 

የመሀል ሜዳ ላይ ፉክክር በርክቶበት የተጀመረው የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ የመጀመሪያ ሙከራ ለማስተናገድ ዘጠኝ ደቂቃዎችን ጠብቋል። የኤሌክትሪኩ የፊት አጥቂ ዲዲዬ ለብሪ በመከላከያ የግብ ክልል ውስጥ ከሞከረው እና ይድነቃቸው ካዳነበት ከዚህ አጋጣሚ በኃላ ግን ጨዋታው በሙከራዎች የታጀበ ሆኖ ቀጥሏል። የቡድኑ ጠንካራ ጎን ሆኖ ይታይ የነበረው የመስመር ተከላካዮች እና አማካዮች እንቅስቃሴ እንደወትሮው ሆኖ ያልታየበት መከላከያ በመጀመሪያው አጋማሽ የፈጠራቸው የግብ ዕድሎች በሙሉ ከሳጥኑ ውጪ የተገኙ ነበሩ።  ሳሙኤል ታዬ 17ኛው ደቂቃ ላይ እንዲሁም ምንይሉ ወንድሙ በ26ኛው ደቂቃ ላይ ከረጅም ርቀት ኢላማቸውን የጠበቁ ሁለት ሙከራዎች ሲያደርጉ ምንይሉ 28ኛው ደቂቃ ላይ የሞከራት ሌላ ኳስ ደግሞ ወደላይ ተነስታ ወጥታለች። የተሻለ የመሀል ሜዳ ብልጫ የነበራቸው ኤሌክትሪኮች በበኩላቸው ወደቀኝ ባደላ የማጥቃት እንቅስቃሴ በሁለቱ አዲስ ፈራሚዎቻቸው ዲዲዬ ለብሪ እና ካሉሺያ አልሀሰን ጥምረት በመጠቀም የጦሩን የተከላካይ ክፍል ፈትነዋል።

33ኛው ደቂቃ ላይ ኤሌክትሪክ መሪ ሲሆን ካሉሺያ በድንቅ አጨራረስ ላስቆጠረው ጎል ኳሷን አመቻችቶ ያቀበለው ዲዲዮ ለብሪ ነበር። በጨዋታው ጥሩ የተንቀሳቀሰው ግብ አስቆጣሪው ካሉሺያ በ14ኛው ደቂቃ ከሳጥን ውጪ ላይ ካደረገው ሙከራ በኃላ 19ኛው ደቂቃ ላይም የመታው ድንቅ ቅጣት ምት ይድነቃቸው ካዳነው በኃላ መስመር ማለፍ አለማለፉ አጨቃጫቂ ሆኖ የተመልካቹን ቀልብ የሳበ ነበር ።

ሁለተኛው አጋማሽ ጅማሮ ላይ መከላከያዎች በግምት 25 ሜትር ርቀት ላይ ያገኙትን  ቅጣት ምት ቴዎድሮስ ታፈሰ በአስደናቂ ሁኔታ በሱሊማን አቡ መረብ ላይ በማሳረፍ ቡድኑን አቻ አድርጓል ። ከዚህ በኃላም የመከላከያዎች ጫና ከመጀመሪያው አጋማሽ በተለየ ጨምሮ ታይቷል። በዚህም መሰረት 55ኛው ደቂቃ ላይ በግራ መስመር ሽመልስ ተገኝ የሻማው እና ሳሙኤል ታዬ ወደግብ ለመምታት አስቦ የጨረፈውን ኳስ ምንይሉ አግኝቶ ሲሞክር የግቡ አግዳሚ መልሶበታል ። ከሶስት ደቂቃዎች በኃላም ሽመልስ በግንባሩ ሞክሮት ወደውጪ የወጣበት ኳስም ተጠቃሽ ነበር ። ቀስ በቀስ የጨዋታ የበላይነቱ ወደ ቀያዮቹ አድልቶም ኤሌክትሪኮች በተደጋጋሚ በግራ መስመር እየሰበሩ በመግባት ሙከራዎችን ሲያደርጉ ተስተውሏል ። በተለይም 67ኛው ደቂቃ ላይ ዲዲዬ ከጎሉ አፋፍ ላይ ያመከነው ኳሱ ቡድኑ ሶስት ነጥብ ለማግኘት እጅግ የቀረበበት አጋጣሚ ሲሆን  በሀይሉ ተሻገር እና አዲስ ነጋሽ ከሳጥን ውጪ የሞከሯቸው ኳሶችም ተጠቃሽ ነበሩ።

88ኛው ደቂቃ ላይ ተቀይሮ የገባው ምንያህል ይመር እና ጥላሁን ወልዴ ከይድነቃቸው ፊት የያገኙት ሌላውዕድል እንዲሁ በሚያስቆጭ መልኩ ተስቷል ። በሱሊማን አቡ ጉዳት ምክንያት ሰባት ደቂቃዎች የተጨመሩበት የዕለቱ ብቸኛ ጨዋታ በዚህ መልኩ  እስከ መጨረሻው ብርቱ ፉክክር ታይቶበት በአቻ ውጤት ተጠናቋል ።
በሁለተኛው ሳምንት የሊጉ ጨዋታዎች ቅዳሜ 11 30 ላይ መከላከያ አዲስ አበባ ስታድየም ላይ ወላይታ ድቻን ሲያስተናግድ ኢትዮ ኤሌክትሪክ ከኢትዮጵያ ቡና ሊያደርግ የነበረው ጨዋታ ለሌላ ጊዜ ተራዝሟል፡፡

የአሰልጣኞች አስተያየት

አሰልጣኝ ብርሀኑ ባዩ

” ሁለተችንም አሸንፈን ለመውጣት ነው የገባነው ። የጎል ዕድሎችም በሁለተችንም በኩል ተፈጥረዋል ። በሁለተኛው አጋማሽ የአጥቂ አማካይ ቀይረን በማስገባት ተጫውተናል ። ኳሱን ብዙ አልሰጠናቸውም ስለዚህ ጥሩ ተንቀሳቅሰናል። ”

አሰልጣኝ ምንያምር ፀጋዬ

” የአመቱ የመጀመሪያ ጨዋታ እንደመሆኑ ሁለቱም ቡድኖች ለማሸነፍ ነበር የተጫወቱት ። እኛም ያገኘናቸውን ዕድሎች አልተጠቀምንም እነሱም እንደዛው ከዚህ አንፃር አቻው ፍትሀዊ ይመስላል ። “

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *