​ሪፖርት | ቅዱስ ጊዮርጊስ የውድድር አመቱን የመጀመርያ ሶስት ነጥብ አሳክቷል

በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 4ኛ ሳምንት ወደ ይርጋለም ተጉዞ የአመቱን ሁለተኛ ጨዋታ ያደረገው ቅዱስ ጊዮርጊስ ሲዳማ ቡናን 1-0 አሸንፏል። በጨዋታው እጅግ በርካታ ደጋፊዎች በስታድየሙ የታደሙ ሲሆን የእንግዶቹ ቅዱስ ጊዮርጊስ ደጋፊዎች ደማቅ ድባብም ታይቶበታል። 

ተመጣጣኝ እንቅስቃሴ በታየበት የመጀመሪያው የጨዋታ አጋማሽ የተጋጣሚን በር በመፈተሽ ሲዳማዎች ቀዳሚ ነበሩ። በ5ኛው ደቂቃ ላይ ፍፁም ተፈሪ ያሻገረውን ኳስ ባዬ ገዛኸኝ ሞክሮ ሮበርት በአስደናቂ ሁኔታ አውጥቶበታል፡፡ በቅዱስ ጊዮርጊስ በኩል አብዱልከሪም ኒኪማ የሚያሻግራቸው ተደጋጋሚ ኳሶች በሲዳማ ቡና ተከላካዮች ሲመክኑ የተስተዋለ ሲሆን በተለይም 10ኛው ደቂቃ ላይ ኒኪማ አሻምቷት አሜ መሀመድ ሞክሮ መሳይ አያና የመለሰበት ቀለል ያለች ሙከራ የቅዱስ ጊዮርጊስ ቀዳሚዋ አጋጣሚ ነበረች።

ሲዳማ ቡናዎች በተለይ በግራ መስመር ተጫዋቹ አብዱለጢፍ መሀመድ በኩል አመዝነው የተንቀሳቀሱ ሲሆን ተጫዋቹ በፈጣን እንቅስቃሴው እና በሚያሻግራቸው የመሬት ለመሬት ኳሶች አደጋ ቢፈጥርም ተሻጋሪ ኳሶቹ ስል አጥቂ በማጣት ሲመክኑ ተስተውሏል።

ከ20 ኛው ደቂቃ በኃላ በመጠነኛ ዝናብ የታጀበው ጨዋታ በተደጋጋሚ ጥፋቶች ሲቆራረጥ የተስተዋለ ሲሆን ፍፁም ተፈሪ በግምባር በመግጨት የግቡን ቋሚ ታኮ የወጣበት ሙከራ ሲዳማዎችን መሪ ሊያደርግ የሚችል እድል ነበር።

30ኛው ደቂቃ ላይ ሳላሀዲን ባርጊቾ ከራሱ የሜዳ አጋማሽ በረጅሙ ወደ ሲዳማ ቡና የግብ ክልል የላካትን ኳስ ቀድሞ ለማግኘት ከአሜ መሐመድ ጋር ሲታገል የነበረው ሙጃሂድ መሐመድ ኳሷን ለማውጣት ያደረገው ጥረት በተቀራኒው አቅጣጫዋን አስቀይሯት ከመረብ በማረፍ ቅዱስ ጊዮርጊስ ቀዳሚ መሆን ችሏል።

ከግቧ በኃላም ቅዱስ ጊዮርጊሶች ተጨማሪ ግብ ለማስቆጠር መልካም አጋጣሚ ማግኘት ችለው ነበር። ጋዲሳ መብራቴ ከምንተሰኖት ጋር ተቀባብሎ ወደ ግብ የላካት ኳስ ማይክል አናን በግንባሩ ገጭቶ በተመሳሳይ ወደ ራሱ ግብ ቢያመራም መሳይ አያኖ ይዞበታል። የመጀመሪያው አጋማሽ መገባደጃ ላይ ማይክል አናን ከግራ የግቡ ጠርዝ የተሻማውን ቅጣት ምት ሲመታት ፍፁም ተፈሪ በግንባሩ ጨርፎ ወደ ውጪ የወጣችበትም በሲዳማ በኩል የአቻነት ጎል ልትሆን የምትችል መልካም አጋጣሚ ነበረች።

ሁለተኛው አጋማሽ ሙሉ ለሙሉ የሲዳማ ቡና የበላይነት የታየበት እና ቅዱስ ጊዮርጊሶች ከመጀመሪያው አጋማሽ ተዳክመው የታዩበት ክፍለ ጊዜ ነበር። ሲዳማዎች በተለይም በመጨረሻዎቹ 30 ደቂቃዎች ሐብታሙ ገዛኸኝን በአምሀ በለጠ ቀይረው በማስገባት በፊት መስመር ላይ የቁጥር ብልጫ ለማግኘት ጥረት ያደረጉ ሲሆን በርካታ እድሎችን መፍጠርም ችለዋል። 49ኛው ደቂቃ ላይ ፍፁም ተፈሪ ወደ ግብ የመታት ኳስ ስትመለስ ኬኔዲ አሽሊ በቀጥታ መትቷት በጨዋታው ምርጥ የነበረው ሮበርት ኡዱንካራ የመለሰበት ፣ 62ኛው ደቂቃ ላይ ባዬ ገዛኸኝ ከሮበርት ጋር አንድ ለአንድ ተገነመኝቶ ያመከነው ፣ በ74ው ደቂቃ ፍፁም ተፈሪ ከሀብታሙ ገዛኸኝ አንድ ሁለት ተቀባብሎ ሳጥን ውስጥ የመታትን የቅዱስ ጊዮርጊስ ተከላካዮች ተረባርበው ያወጡበት ፣ በ77ኛው ከቅጣት ምት የተሻገረውን  ኳስ ተከላካዩ ማይክል አናን በግንባሩ ገጭቶ የግቡን አግዳሚ ገጭቶ ሲመለስ ፍፁም ተፈሪ በድጋሚ መትቶ አስቻለው ታመነ ተንሸራቶ ያወጣበት ሙከራዎች የሚጠቀሱ ነበሩ።

በቅዱስ ጊዮርጊሶች በኩል በጭማሪ ደቂቃ ላይ በመልሶ ማጥቃት የተገኘችውን መልካም አጋጣሚ በኃይሉ አሰፋ ግብ ጠባቂውን መሳይ አያኖን አልፎ አቀብሎት አሜ መሀመድ ሳይጠቀምበት ቀረ እንጂ ሻምፒዮኖቹ የግብ ልዩነታቸውን ሊያሰፉበት የሚችሉበት ወርቃማ አጋጣሚ ነበር። የአሜ ኳስ በወጣ ቅፅበትም መሳይ በረጅሙ የላካትን ኳስ ሐብታሙ ገዛኸኝ ቢያገኛትም ሮበርት በቀላሉ ተቆጣጥሮት ጨዋታው ተጠናቋል።

ድሉ ሁለተኛ ጨዋታውን ላደረገው የአምናው ቻምፒዮን ቅዱስ ጊዮርጊስ የአመቱ መጀመርያ ሶስት ነጥብ ሆኖ ሲመዘገብ በሲዳማ ቡና ያለመሸነፍ ክብሩንም ለ17ኛ ጨዋታ አራዝሟል። ሲዳማ ቡና በአንፃሩ ከአራት ጨዋታ ምንም ድል ባለማስመዝገብ ቀዝቃዛ የውድድር ዘመን ጅማሮ ለማድረግ ተገዷል።

የአሰልጣኞች አስተያየት 

አለማየሁ አባይነህ – ሲዳማ ቡና

“ይህ እግር ኳስ ነው። እግር ኳስን ተወዳጅ ያደረገውም ይህ ነው። እኛ ተጫወትን እኛው ራሳችን ላይ አገባን። ሙሉ ለሙሉ 90 ደቂቃውን በልጠን ብንጫወትም በግብ ጠባቂው ጥረት እና በግቡ ብረት ታግዘው አሸንፈው ወጥተዋል።  እንደ እንቅስቃሴያችን ቢሆን ግን ሰባት እና ስድስት ጎል አግብተን ማለቅ ነበረበት። ውጤቱ ጨዋታውን አይገልፀውም ፡፡

” በአራቱ ጨዋታ ላይ አለማሸነፋችን ቡድኔን ጫና ውስጥ አይከተውም። ከቋሚ ተሰላፊዎቼ አራት ወሳኝ ተጫዋቾች ሳይኖሩ ከትልቁ ጊዮርጊስ ጋር ተጫውቶ የተሻለ ተንቀሳቅሶ መውጣት በራሱ ጥሩ ነው። በቀጣይ ግን ወደ አሸናፊነት እንመጣለን ።በርግጠኝነት ይህን ማድረግ የሚችሉ ተጫዋቾችም አሉን።

” ግቧን ያስቆጠረው ሙጃይድ ወጣት ነው። ካለቦታው ተሰልፎ ጥሩ ተንቀሳቅሷል። ግብ ስላገባ ምክንያት አናደርግበትም ፤ ተቃውሞም የለኝም፡፡”

ፋሲል ተካልኝ – ቅዱስ ጊዮርጊስ (ረዳት አሰልጣኝ)

“በመጀመሪያ ወደዚህ ስንመጣ ጨዋታው ለኛ ከባድ እንደሚሆን ገምተን ነበር። በብሔራዊ ቡድን እና በጉዳት ያልነበሩ ተጫዋቾች በመኖራቸው ሜዳ ላይም አማራጮቻችንን ሊያሳጥሩ እንደሚችሉ እናውቅ ነበር። ነገር ግን ከዚህ ጨዋታ በዋነኝነት የምንፈልገው ሶስት ነጥብ ብቻ ነበር፡፡

” በሁለተኛው አጋማሽ ሲዳማዎች ከኛ የተሻሉ ነበሩ። ጥሩ ተጫውተዋል። የግብ እድልም መፍጠር ችለዋል። ሆኖም ተጫዋቾቻችን ሶስት ነጥብ አሳልፎ ላለመስጠት የነበራቸው ፍላጎት እጅግ ጥሩ የነበረ በመሆኑ በመጨረሻም ያን አሳክተን ወጥተናል።

” ከሜዳ ውጭ እንደመጫወታችን በሁለተኛው አርባአምስት ያንን ለማስጠበቅ ወደ ኃላ አፈግፍገን ተጫውተናል። ይህም ለሚመራ ቡድን ይህን አጨዋወት መከተል ግድ ነው።  እኛም በመጨረሻዎቹ ደቂቃዎች ላይ የግብ እድል ፈጥረናል።

” የተጋጣሚያችን ጥንካሬ በርግጥ ክፍተቶቻችንን አሳይቶናል።  ከማሸነፋችንም በዘለለ ብዙ ነገር ለቀጣይ አስተምሮናል።”

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *