አልጄሪያ የውጪ ተጫዋቾች በሊጓ እንዳይጫወቱ አገደች

ሰሜን አፍሪዊቷ አልጄሪያ የውጪ ሀገር ዜጋ የሆኑ ተጫዋቾች በቻምፒዮናት ናሽናል ለሚሳተፉ ክለቦች መፈረም እንደማይችሉ አሳወቀች። ህጉ ተግባራዊ መሆን የሚጀምረውም በቀጣዩ ዓመት አጋማሽ (የጥር የዝውውር መስኮት) በኋላ እንደሆነ ለማወቅ ተችሏል።

በአልጄሪያ ክለቦች እየተጫወቱ የሚገኙ እና በክረምቱ የዝውውር መስኮት ሊጉን የሚቀላቀሉ ተጫዋቾች በአዲሱ ህግ የተካተቱ ባይሆንም የኮንትራት ዘመናቸውን እንዳጠናቀቁ ግን ሃገሪቱን ለቀው የሚወጡ ይሆናል። በዚህም ሂደት ከሳምንታት በፊት የግብፁን ሃያል ክለብ አል አህሊ በመልቀቅ ኤምሲ አልጀርስን የተቀላቀለው ኢትዮጵያዊ አጥቂ ሳልሃዲን ሰይድ ከክለቡ ጋር የተፈራረመውን 3 ዓመት ከተጫወተ በኋላ ሌላ ክለብ ለመፈለግ ይገደዳል።

አልጄሪያ ከዚህ ህግ መፅደቅ በፊትም ቢሆን በውጪ ሃገራት ተጫዋቾች ቁጥር ላይ ጠበቅ ያለ ቁጥጥር ከሚያደርጉ ሃገራት አንዷ ነች። በአልጄሪያ ክለቦች 3 የውጪ ዜጎች መመዝገብ ሲችሉ ከነዚህም ውስጥ በአንድ ጨዋታ ላይ አብረው መጫወት የሚችሉት 2ቱ ብቻ ናቸው። ባለፈው አመት በጄኤስ ካባሊዬ ክለብ ይጫወት የነበረው ካሜሮናዊ አጥቂ አልበርት ኤቦሴ ከራሱ ደጋፊዎች በተወረወረ ድንጋይ ተመቶ ህይወቱ ካለፈ በኋላ የሊጉ የውጪ ተጫዋቾችን የመሳብ ብቃት እንደወረደም ይነገራል።

የአልጄሪያ እግርኳስ ፌዴሬሽን የክለቦቹ የፋይናንስ ጥንካሬ መዳከም እና የውጪ ምንዛሬ እጥረት፣ እንዲሁም በአንዳንድ የውጪ ዜጋ ተጫዋቾች እና ወኪሎች የሚታየው ያልተገባ አሠራር ይህንን ውሳኔ እንድወስን አስገድዶኛል በማለት ገልጿል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *