​ሪፖርት| ቅዱስ ጊዮርጊስ ከመከላከያ ያለ ግብ አቻ ተለያይተዋል

በ8ኛ ሳምንት የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የመጀመሪያ ቀን ውሎ አዲስአበባ ስታዲየም ላይ ቅዱስ ጊዮርጊስ ከመከላከያ ጋር 0-0 በሆነ የአቻ ውጤት ተለያይቷል። ፈረሰኞቹ ለወትሮው ፈታኝ ተጋጣሚው ሆኖ በሚቀርበው መከላከያ ነጥብ መጣሉን ተከትሎም ከደደቢት ያለውን የነጥብ ልዩነት የሚያጠብበት እድሉን አምክኗል።

ቅዱስ ጊዮርጊስ ባሳለፍነው ሳምንት ወደ አዲግራት አቅንቶ ከወልዋሎ አ.ዩ ጋር አቻ የተለያየውን የቡድን ስብስብ በተመሳሳይ በዛሬው እለት ሲጠቀም በአንፃሩ ከአስከፊ አጀማመሩ እያንሰራራ የሚገኘው መከላከያ ድሬዳዋ ከተማን 1-0 ካሸነፈው ቡድን ውስጥ አጥቂው አቅሌሲያስ ግርማን በማራኪ ወርቁ ብቻ በመተካት በተመሳሳይ ቅርፅ ጨዋታውን ጀምረዋል።

ቅዱስ ጊዮርጊስ በጨዋታው የመጀመሪያ ደቂቃዎች ላይ ከአዲሱ የፖርቹጋላዊ አሰልጣኝ መምጣት ጀምሮ ያደርጉት እንደነበረው በጥልቀት ከራሳቸው የሜዳ ክፍል ኳስን መስረተው ለመውጣት ጥረት ቢያደርጉም ፈጣኖቹ የመከላከያ አጥቂዎች ማራኪ ወርቁና ምንይሉ ወንድሙ በፍጥነት ኳስ የያዘውን ተጫዋች በማፈን የቅዱስ ጊዮርጊስ ተጫዋቾች በሚፈልጉት ደረጃ ከኳስ ጋር የሚኖራቸውን የማሰብያ ጊዜ በማሳጠር በተደጋጋሚ ኳሶችን ያለ አላማ ወደፊት እንዲልኩ ማስገደድ ችለው ነበር፡፡ በቁጥር በርከት በማለት ወደ ኃላ አፈግፍገው መከላከልን ቅድሚያ የሰጡ የሚመስሉት መከላከያዎች ከመከላከል ወደ ማጥቃት የሚያደርጉት ሽግግር ግን እጅግ ደካማ ነበር። በበርካታ አጋጣሚዎች በሜዳው የመሀከለኛው ክፍል ላይ ከተጋጣሚያቸው ላይ ኳሶቹን መንጠቅ ቢችሉም እንደ አጥቂዎቻቸው ፍጥነት በተለይ እንደ ቅዱስ ጊዮርጊስ አይነት የተከላካይ መስመሩን ወደ መሀል ሜዳው አስጠግቶ የሚከላከል ቡድን በተከላካይ ክፍሉና በግብ ጠባቂያቸው መካከል ያለውን ሰፊ ክፍተት መጠቀም ሳይችሉ ቀርተዋል፡፡

እምብዛም የጠሩ የግብ ሙከራዎች ባልታዩበት የመጀመሪያው አጋማሽ በቅዱስ ጊዮርጊስ በኩል በ4-3-3 ከሙሉአለም መስፍን በስተቀኝና ግራ የተሰለፉት አብዱልከሪም ዞኮና ምንተስኖት አዳነ በ4-1-3-2 ከተላካዮቹ ፊት በብቸኝነት የተሰለፈው በኃይሉ ግርማ ከፊት ለፊቱ ከነበሩት ተጫዋቾች በበቂ ሁኔታ ድጋፍ እንዳለማግኘቱ በሜዳው ስፋቱ በሁለቱም ወገን የነበረውን ሰፊ የሜዳ ክፍል እጅግ ደካማ በሆነው የቦታ አያያዛቸው ስህተት መሠረት በአግባቡ መጠቀም ባለመቻላቸው የቡድኑ የአጥቂ ተሰላፊዎች ከእነሱ የሚፈልጉትን በቂ ግልጋሎት ማግኘት ሳይችሉ ቀርተዋል፡፡

በዚሁ የመጀመሪያ አጋማሽ በሜዳው አግድመት እጅግ ለጥጠው የሚጫወቱት የቅዱስ ጊዮርጊስ የመስመር አጥቂዎችን እንቅስቃሴ ለመግታት በማሰብ የመከላከያ አራት ተከላካዮች የሜዳውን ስፋትን በማጥበብ በጥልቀት በመከላከል ስራ ላይ ተጠምደው ተስተውሏል። ነገርግን ከአራቱ ተከላካዮች ውስጥ በግራ የመስመር ተከላካይነት የተሰለፈው ታፈሰ ሰርካ እንቅስቃሴ በጨዋታው ጅማሮ ላይ በቀኝ የመስመር አጥቂነት በቅዱስ ጊዮርጊስ በኩል በተሰለፈው አቡበከር ሳኒ እንቅስቃሴ ላይ በእጅጉ የተመሰረተ በመሆኑ ኢብራሂማ ፎፋና በተወሰኑ አጋጣሚዎች ወደ ቀኝ መስመር ወጥቶ ኳሶችን ለመቀበልና ክፍተቶችን ለመፍጠር በሚጥርበት ወቅት በቀላሉ በአንድ ሁለት ቅብብል እየታለፈ በመጀመሪያው አጋማሽ ቅዱስ ጊዮርጊስ ለፈጠራቸው አስደንጋጭ የግብ ማግባት አጋጣሚዎች ምክንያት ሆኖ ነበር፡፡

ቅዱስ ጊዮርጊስ በመጀመርያው አጋማሽ ካደረጋቸው ሙከራዎች ውስጥ በ30ኛው ደቂቃ ላይ ጋዲሳ መብራቴ የመከላከያ ተጫዋቾች መዘናጋትን ተከትሎ ከቀኝ መስመር ወደ መሀል አጥብቦ በቀጥታ ከሳጥን ውጪ ወደ ግብ የላካትና አቤል ማሞ በአስደናቂ ሁኔታ ያዳነበት ኳስ በጣም አስቆጭዋ ነበረች፡፡

ደቂቃዎች እየገፉ በመጡ ቁጥር ቅዱስ ጊዮርጊስ ተጫዋቾች በተለይም የተከላካይ ስፍራ ተጫዋቾች ኳሱን ከመቀባበል ይልቅ በረጃጅሙ በቀጥተኛ አጨዋወት ኳሱን ለፊት መስመር ተሰላፊዎች ማድረስን ምርጫቸው አድርገዋል። በዚህ አጨዋወት በ39ኛው ደቂቃ ከተከላካዮች በቀጥታ የተላከለትን ኳስ ኢብራሂማ ፎፋና የመጀመሪያ ኳስ በማሸነፍ ለአብዱልከሪም ዞኮ ያቀበለውና ዞኮ በቀጥታ ሞክሮ አቤል ያዳነበት ኳስ ሌላኛው ተጠቃሽ ሙከራ ነበር፡፡

ለመከላከል ቅድሚያ ሰጥተው የገቡት መከላከያዎች በ35ኛው ደቂቃ ላይ ቴዎድሮስ ታፈሰ ከቋመ ኳስ ያሻማውንና ምንተስኖት ከበደ ተንሸራቶ ሞክሮ ለጥቂት ወደ ውጪ ከወጣበት ኳስ ውጭ ይህ ነው የሚባል ግብ እድል መፍጠር ሳይችሉ ቀርተዋል።

በሁለተኛው አጋማሽ የመጀመሪያ 10 ደቂቃዎች ላይ የቅዱስ ጊዮርጊስ ተጫዋቾች ከመጀመሪያው በባሰ መልኩ እጅግ አደገኛ በሆኑ ቀጠናዎች ላይ ከልክ ባለፈ የራስ መተማመንና በተቃራኒ ተጫዋቾች የሚደርስባቸውን ጫና መቋቋም ባለመቻላቸው በበርካታ አጋጣሚዎች ኳሶችን ቢነጠቁም ተጋጣሚያቸው ኳሶችን በሚያገኙበት ወቅት ለማጥቃት የሚያስችል ጥሩ ቁመና ላይ ባለመገኘታቸው መጠቀም ሳይችሉ ቀሩ እንጂ እጅግ አደገኛ ነበሩ፡፡

መከላከያዎች በ52ኛው ደቂቃ ላይ በጨዋታው ደካማ እንቅስቃሴ ሲያሳይ የነበረውን የመስመር አጥቂውን መስፍን ኪዳኔን አስወጥተው አማኑኤል ተሾመን በማስገባት እና ቅርፃቸውን ወደ 4-1-4-1 በመቀየር ተቀይሮ የገባው አማኑኤል ከተከላካይ ፊት ያለውን ስፍራ ይዞ ሲጫወት በሀይሉ ግርማ ከእሱ በጥቂት ርቀት ወደፊት ቀደም ብሎ ቢጫወትም ለአማኑኤል በቂ እገዛ እንዲያደርግ በመደረጉ ከመጀመሪያው በተሻለ መሀል ለመሀል የሚመጡ የማጥቃት እንቅስቃሴን ለመመከት አስችሏቸዋል፡፡ በመጀመሪያው አጋማሽ እንደታየው ሁሉ ቅዱስ ጊዮርጊስ በቀጥተኛ አጨዋወት ወደፊት በሚጣሉ ኳሶች ፈጣኑ አጥቂያቸው ኢብራሂማ ፎፋና ለሁለቱ የመከላከያ የመሀል ተከላካዮች ፈተና ሆኖ ተስተውሏል፡፡

በጨዋታው 65ኛው ደቂቃ ላይ ሰልሃዲን በርጌቾ ባጋጠመው የትከሻ ጉዳት የተነሳ በደጉ ደበበ ተቀይሮ ከሜዳ ለመውጣት ተገዷል፡፡ በ68ኛው ደቂቃ ላይ መከላከያዎች በፈጣን ከመከላከል ወደ ማጥቃት በተደረገ ሽግግር የተገኘውን ኳስ ማራኪ ወርቁ ያሻገረለትን ኳስ ምንይሉ ወንድሙ ተንሸራቶ የሞከረው ኳስ ለጥቂት የግቡን ቋሚ ታኮ ወደ ውጪ የወጣበት ኳስ በጣም የሚያስቆጭ አጋጣሚ ነበር፡፡
ቅዱስ ጊዮርጊሶች በመጨረሻ 15 ደቂቃዎች ላይ ምንተስኖት አዳነን በአዳነ ግርማ በመተካት ወደ ከግራ መስመር በተለይም በአበባው ቡጣቆ በተደጋጋሚ ወደ ሳጥን ይጣሉ የነበሩ ኳሶችን ለመጠቀም ያደረጉት ጥረት ሳይሳካ ቀርቷል፡፡ ጨዋታው ሊገባደድ ሰከንዶች በቀሩበት ወቅት ምንይሉ ወንድሙ የቅዱስ ጊዮርጊስ ተጫዋቾች ሙሉ ለሙሉ ለማጥቃት መውጣታቸውን ተከትሎ መከላከያዎች ያገኙትን እጅግ ወርቃማ አጋጣሚ ሳይጠቀምበት ቀረ እንጂ ጦሩ በስተመጨረሻ ወሳኝ ሶስት ነጥብ ሊያገኙበት የሚችሉበት አጋጣሚ ነበር፡፡

ጨዋታው በአቻ ውጤት መጠናቀቁን ተከትሎ ቅዱስ ጊዮርጊስ ከደደቢት በሁለት ጨዋታዎች ቢያንስም በ13 ነጥብ 3ኛ ደረጃ ላይ መቀመጥ ሲችል በአንጻሩ መከላከያ በ10 ነጥብ በነበረበት 10ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል።

የአሰልጣኞች አስተያየት

ሻምበል ምንያምር ፀጋዬ- መከላከያ

” ለበርካታ አመታት የሊጉ ቻምፒየን ከሆነው ቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር እንደመጫወታችን ጨዋታውን በጣም በጥንቃቄ ለመጫወት መርጠናል፡፡ ወደ ጨዋታው ስንገባ ከቅዱስ ጊዮርጊስ አንድ ነጥብ ማግኘትን አስበን ነበር የገባነው ይህንንም አሳክተናል፡፡ ብዙ ኳስ መቆጣጠር ነጥብ አያስገኝም። ስለዚህ ተከላክለን አንድ ነጥብ ይዘን ወጥተናል፡፡”

ፋሲል ተካልኝ- ቅዱስ ጊዮርጊስ

“እኛ ወደ ጨዋታው የገባነው ኳስ ተጫውተን ለማሸነፍ ነበር። ነገርግን ተጋጣሚያችን ኳስን መጫወት አልፈለጉም ነበር፡፡ ተጫዋቾቻችን ጨዋታውን ለማሸነፍ የተቻላቸውን አድርገዋል ፤ ነገርግን ምንም ማድረግ አልቻልንም፡፡ የሜዳው የመጨረሻ ክፍል ላይ የምንደርስበት መንገድና ከደረስን በኃላም ውሳኔዎቻችን ልክ አለመሆናቸው ከተጋጣሚያችን በጥልቀት ለመከላከል መፈለግ ጋር ተዳምረው ጨዋታውን አስቸጋሪ አድርጎብናል፡፡”

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *