​የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 9ኛ ሳምንት – የቅዳሜ ጨዋታዎች ቅድመ ዳሰሳ

በፕሪምየር ሊጉ 9ኛ ሳምንት የመጀመሪያ ቀን ውሎ ዛሬ ሦስት መርሀ ግብሮች ይከናወናሉ። እንደተለመደው በቅድመ ጨዋታ ዳሰሳችን በ4-4-2 አሰላለፍ ተጠቃሚነታቸው የምናውቃቸውን ጅማ አባ ጅፋር ፣ ድሬደዋ ከተማ እና መከላከያን 4-3-3ን ሲተገብሩ ከሚታዩት ወልዋሎ ዓ.ዩ ፣ ፋሲል ከተማ እና ቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር የሚያገናኙትን ጨዋታዎች ተመልክተናቸዋል።

ጅማ አባ ጅፋር ከ ወልዋሎ ዓ.ዩ

ሁለቱ የአምና የከፍተኛ ሊግ ፍፃሜ ተፋላሚዎች ዛሬ ጅማ ላይ ሲገናኙ በዕኩል 11 ነጥቦች ሶስተኛ እና አራተኛ ደረጃ ላይ በመቀመጥ ነው። ምንም እንኳን ለሊጉ አዲስ ቢሆኑም አባ ጅፋር በሰሞንኛ አቋሙ እንዲሁም ወልዋሎ በመጀመሪያዎቹ ወቅቶች በሰበሰቧቸው ነጥቦች ምክንያት ጨዋታው ትኩረትን እንዲስብ ሆኗል። ለአምስት ተከታታይ ጨዋታዎች ግብ ሳያስቆጥር የቆየው ጅማ አባ ጅፋር በናይጄሪያዊው አጥቂ ኦኪኪ አፎላቢ ፊት አውራሪነት ባለፉት ሁለት ጨዋታዎች አምስት ግቦችን ማግኘት መቻሉ መናጋገሪያ ሆኗል። በአንፃሩ ከአምስተኛው ሳምንት በኃላ ከድል የራቀው ወልዋሎ በመከላከያ ሲሸነፍ እንዲሁም ከቅዱስ ጊዮርጊስ ጋርም አቻ ሲለያይ ኳስን ከመረብ ጋር ማገናኘት ሳይችልም ጭምር ነው። በመሆኑም ቡድኖቹ ዛሬ 9 ሰዐት ላይ በጅማ ሲገናኙ ባለሜዳዎቹ አባጅፋሮች ሶስተኛ ተከታታይ ድላቸውን በማስመዝገብ ወደ ሁለተኛነት ከፍ ለማለት እንዲሁም ወልዋሎዎች ዳግም ወደ አሸናፊነታቸው በመመለስ ተመሳሳይ ነጥብ እና ደረጃ ላይ ለመገኘት እንደሚፋለሙ ይጠበቃል።

በጅማ አባ ጅፋር በኩል ለረጅም ጊዜ በጉዳት ዝርዝር ውስጥ ተካተው የቆዩት ጌቱ ረፌራ ፣ አሸናፊ ሽብሩ እና ዝናቡ ባፋአ አሁንም ወደ ጨዋታ ያልተመለሱ ሲሆን የግራ መስመር አማካዩ ኄኖክ ኢሳይያስም በዚህ ሳምንት የተቀላቀላቸው ተጫዋች ሆኗል። በወልዋሎ ዓ.ዩ በኩል ግን በመከላከያው ጨዋታ ከሳሙኤል ሳሊሶ ጋር ግብግብ ገጥሞ የቀይ ካርድ ሰለባ ከሆነው እንየው ካሳሁን ሌላ በጉዳት ለጨዋታው የማይደርስ ተጨዋች አለመኖሩን ሰምተናል።

ጅማ አባ ጅፋር እንደቡድን የሚያዋጣውን አጨዋወት ያገኘ ይመስላል። በ4-4-2 ከአሚኑ ነስሩ እና ይሁን እንዳሻው የመሀል አማካዮች ጥምረት ውጪ ዮናስ ገረመው እና በዚህ ጨዋታ ላይ የማይኖረው ሔኖክ ኢሳያስ ከሁለቱ መስመሮች በመነሳት የቡድኑ ዋነኛ የማጥቃት ምንጭ ሲሆኑ ይታያል። ፊት ላይ ያለው የኦኪኪ እና ተመስገን ጥምረትም በእንቅስቃሴ ለእነዚህ የመስመር አማካዮች እየቀረቡ መጫወት የቡድኑን የማጥቃት ሽግግር ፍጥነት ከመጨመር ባለፈ በተለይ የኦኪኪ አጨዋወት የተጋጣሚን የተከላካይ መስመር ከመረበሽ አንፃር ያለው ሚና እጅግ ከፍ ያለ ሆኗል። አሰልጣኝ ገ/መድህን ኃይሌ ከዚህ ጠንካራ የማጥቃት መስመራቸው ውስጥ የግራ መስመር አማካይ ሔኖክ ኢሳያስን በአግባቡ መተካት የሚጠበቅባቸው ሲሆን ተጋጣሚያቸው ወልዋሎ ዓ.ዩ የቀኝ መስመር የማጥቃት ሀይል ክብደት ደግሞ ለዚህ ቦታ የሚሰጡት ትኩረት ከፍ እንዲል የሚያደርጋቸው ነው። ፕሪንስ ሰቨሪንሆን በመስመር አጥቂነት እንዲሁም ሁለገቡን አሳሪ አልመሀዲን በመስመር ተከላካይ ቦታ ላይ እየተጠቀሙ የሚገኙት ወልዋሎዎች በቀኙ የአማካይ ክፍል ላይ ከሚያሰልፉት አፈወርቅ ኃይሉ ጋር ተደምሮ በቡድኑ የሜዳ ቁመት የቀኝ ክፍል የግብ ዕድሎችን ለመፍጠር ዋና አማራጭ እንዲሆን ምክንያት ሆኗል። በሌላ በኩል የግራ መስመር አጥቂው ከድር ሳሊህ ወደ መሀል አጥብቦ እና ለሙሉአለም ጥላሁን ቀርቦ መጫወትን ተከትሎ ከቀኝ መስመር የሚነሱ ኳሶችን ለመጨረስ ዕድል ቢፈጥርም ለተቃራኒ ቡድን የቀኝ መስመር ጥቃት በር ሲከፍት ይታያል። በመሆኑም በዚህ አቅጣጫ የሚሰለፈው የአባ ጅፋሩ የቀኝ መስመር አማካይ ዮናስ ገረመው ከክፍተቱ የሚያገኘው ነፃነት ኦኪኪኒ በቅብብሎች ለማግኘት የሚረዳው እንደሚሆን ይገመታል። ከመስመሮቹ በተጨማሪ በአማካይ መስመር ላይ የአሚኑ ነስሩ እና ይሁን እንዳሻው ጥምረት ከወልዋሎዎቹ የማጥቃት አማካዮች ዋለልኝ ገብሬ እና አፈወርቅ ኃይሉ ጋር የሚያደርጉት ፍልሚያ የጨዋታውን የሀይል ሚዛን በመወሰኑ ረገድ ዋሳኝ እንደሚሆን ይጠበቃል።

ድሬዳዋ ከተማ ከ ፋሲል ከተማ

አምና ከአራተኛው ሳምንት በኃላ ለስምንት ተከታታይ ጨዋታዎች ከሶስት ነጥብ ጋር ተለያይቶ የቆየው ድሬዳዋ ከተማ ፋሲል ከተማን ሜዳው ላይ አስተናግዶ በሀብታሙ ወልዴ የመጀመሪያ ደቂቃ ጎል ፋሲል በማሸነፍ ነበር ወደ ድል የተመለሰው። ዘንድሮም በተመሳሳይ ሁኔታ ከውጤት ርቀው የቆዩት ድሬዎች ከአሰልጣኝ ዘላለም ሽፈራው ስንብት ማግስት ፋሲል ከተማን ማግኘታቸው የአምናውን አጋጣሚ ስለመድገም እንዲያስቡ የሚያደርጋቸው ይመስላል። ሆኖም ፋሲል ከተማ እስካሁን በሊጉ ምንም አይነት ሽንፈት ያልደረሰበት ክለብ መሆኑ ፈተናውን ከባድ ያደርገዋል። አፄዎቹ ወላይታ ድቻን በሜዳቸው ከረቱ በኃላ ከአዳማ ከተማ እና ከሀዋሳ ከተማ ጋር ነጥብ ተጋርተዋል። ከዚህ በተጨማሪም ከደደቢት እና አዳማ ከተማ ጋር ባደረጓቸው ሁለት የመጨረሻ የሜዳ ውጪ ጨዋታዎች መረባቸውን ሳያስደፍሩ ነበር የተመለሱት። አንድ አንድ ቀሪ ጨዋታ ያላቸው ሁለቱ ቡድኖች ይህን ጨዋታ በድል ማጠናቀቅ ከቻሉ ፋሲል ከተማ ወደ ሁለተኝነት እንዲሁም ድሬደዋ ከተማም ከወራጅ ቀጠናው ይበልጥ ርቆ ወደ ዘጠነኛ ደረጃ ከፍ የማለት ዕድል ይኖራቸዋል።

ባለሜዳዎቹ ድሬደዋ ከተማዎች ግብ ጠባቂያቸው ሳምሶን አሰፋ በጣቱ ላይ በደረሰ ጉዳት ምክንያት ከጨዋታ ውጪ እንደሆነባቸው የሚታወስ ሲሆን ዘነበ ከበደ ፣ ሀብታሙ ወልዴ እና ሳምንት በመከላከያው ጨዋታ ላይ ተቀይሮ የወጣው ዮሴፍ ደሙዬም በጉዳት ምክንያት ፋሲልን ከሚገጥመው የቡድኑ ስብስብ ውጪ መሆናቸውን ሰምተናል። የረጅም ጊዜ ጉዳት ላይ ቆይቶ በማገገም ላይ የሚገኘው ያሬድ ባየህ ለአፄዎቹ አገልግሎት መስጠት ያልጀመረ ሲሆን ኤፍሬም አለሙ እና ሳምንት ከጉዳት ተመልሶ የነበረው ይስሀቅ መኩሪያ ሌሎች በጉዳት ሳቢያ ወደ ድሬ የማያመሩ ተጨዋቾች ሆነዋል።

በቀድሞው የኢትዮ ኤሌክትሪክ እና ኢትዮጵያ ቡና ድንቅ ተጨዋች እና ያሁኑ አሰልጣኝ ስምዖን አባይ መሪነት መከላከያን ሲገጥሙ ከወትሮው በተለየ መልኩ ማጥቃትን ምርጫቸው አድርገው በሁለተኛው የሜዳ አጋማሽ ገፍተው ሲጫወቱ የታዩት ድሬዎች በአጨዋወት ለውጥ ላይ እንዳሉ መታዘብ ይቻላል። ሆኖም የቡድኑ ዋነኛ የፈጠራ ምንጭ የነበረው የቀኝ መስመር አማካዩ ሱራፌል ዳንኤል ጭምር ወደ ግራ ያደላ የማጥቃት እንቅስቃሴ ቡድኑን ሙሉ ለሙሉ ወደ ግራ ያጋደለ እና ተገማች በማድረጉ በሚፈለገው መጠን የግብ ዕድሎችን ለመፍጠር እንዲቸገር አድርጎታል። በብዙሀኑ የሀገራችን ክለቦች እንደሚታየውም ቡድኑ ተጋጣሚ ክፍተት የሚፈጥርበትን የሜዳ ክፍል ከመጠቀም ይልቅ በራሱ የማጥቃት አቅጣጫ ምርጫ ላይ መመርኮዙ ለዚህ ችግር እንደረገው ታይቷል። ከፊት ያለው የአጥቂዎች ጥምረትም እንዲሁ ብዙ መሻሻል የሚጠበቅበት ነው። በዚህ ረገድ የሀብታሙ ወልዴ አለመኖር እና የዘካሪያስ ፍቅሬ በቋሚ አሰላለፍ ውስጥ አለመካተት ጋናዊው አጥቂ ኩዋሜ አትራም ሁነኛ አጣማሪ ላለማግኘቱ የሚነሱ ምክንያቶች ናቸው። 

ወደ ፋሲል ከተማ ስንመጣ የአማካዩ ዳዊት እስጢፋኖስ በመጀመሪያ አሰላለፍ ውስጥ መካተት መጀመር ቡድኑ በፈጣን የማጥቃት ሽግግር ወደ ተጋጣሚ የሜዳ ክልል በሚገባባቸው አጋጣሚዎች በተሳሳቱ ቅብብሎች ምክንያት ይመክኑበት የነበሩ ዕድሎችን ለመጠቀም እጅግ ወሳኝ ያደርገዋል። የተጨዋቹ የመከላከል ተሳትፎ እምብዛም ቢሆንም በማጥቃቱ ሂደት ላይ ግን ፋሲሎች አጥተውት የነበረውን ይመጨረሻ ዕድሎችን የመፍጠር ጥንካሬ ከተጨዋቹ ማግኘት እንድሚችሉ ይታመናል። ሌላው የፋሲሎች ጠንካራ ጎን የሆነው የመስመር አጥቂዎቻቸው እንቅስቃሴ በዚህ ጨዋታ የሚኖረው ሚና ቀላል አይሆንም ። ኳስን መስርቶ ለመጫወት ከሚሞክረው የድሬደዋ  ተከላካይ መስመር ጀርባ ለመግባት የአብዱርሀማን ሙባረክ እና ራምኬል ሎክ ፈጣን ማጥቃት ከድሬዎቹ መስመር ተከላካዮች ያሬድ ዘውድነህ እና አህመድ ረሺድ ጋር የሚገናኝበት አጋጣሚ ጨዋታውን የመወሰን ሀይል ይኖረዋል። መሀል ሜዳ ላይ የፋሲል ከተማ የማጥቃት አማካዮች ከፊቱ ከሚሰለፉ ሶስቱ አማካዮች በቂ ሽፋን ሲያገኝ ከማይታየው የድሬደዋው የተከላካይ አማካይ ኢማኑኤል ላርያ ግራ እና ቀኝ በሚኖሩት ቦታዎች ላይ የሚኖራቸው እንቅስቃሴ ቡድኑ ለሚፈጥራቸው ዕድሎች ወሳኝ ይሆናሉ ተብሎ ይጠበቃል። ሆኖም የፊት አጥቂው ፊሊፕ ዳውዝ እንደቀድሞው አለመሆን ለጠንካራው የብርቱካናማዎቹ የመሀል ተከላካይ ጥምረት የሚኖረው አስፈሪነት እምብዛም ነው።

ቅዱስ ጊዮርጊስ ከ መከላከያ

አሁንም ሁለት ቀሪ ጨዋታዎች ያሉት ቅዱስ ጊዮርጊስ በአራት ነጥቦች ዝቅ ብሎ ደደቢትን እየተከተለ ይገኛል። ሳምንት ከሜዳቸው ውጪ ከወልዋሎ ዓ.ዩ ጋር ያለ ግብ ተለያዩት ፈረሰኞቹ  በአምናው አስደናቂ አጀማመራቸው ወቅት መከላከያን 3-0 ማሸነፋቸው የሚታወስ ነው። ሆኖም የዘንድሮው መከላከያ ከአምናው በተሻለ ወቅታዊ አቋም ላይ ይገኛል። ቡድኑ ከሀዋሳ ከተማ ጋር ነጥብ ከተጋራ በኃላ ወልዋሎ ዓ.ዩ እና ድሬደዋ ከተማን በተከታታይ አሸንፎ ለዚህ ጨዋታ መድረሱ ይህን ነጥብ የሚያጠናክር ነው የሚሆነው። አሁን ላይ ምንም እንኳን በደረጃ ሰንጠረዡ ሁለተኛ እና አስረኛ ደረጃ ላይ ቢገኙም በቀደመው ጊዜ ሁለቱ የመዲናዋ ክለቦች  ዋነኛ የሊጉ ተፎካካሪዎች እንደነበሩ የሚታወስ ነው። በቅርብ ጊዜያትም በተገናኙባቸው አጋጣሚዎች በሜዳ ላይ እንቅስቃሴ የሚታየው የመሸናነፍ ትግል የዛሬውን ጨዋታ ተጠባቂነት ከፍ ያደርገዋል። ቅዱስ ጊዮርጊስ ይህን ጨዋታ ካሸነፈ ለዘላቂነቱ የነገውን የደደቢትን ውጤት ቢጠብቅም ሁለት ቀሪ ጨዋታዎችን ይዞ በአንድ ነጥብ ብቻ ከሊጉ መሪነት ጫፍ ላይ ሊደርስ ሲችል መከላከያ ባለ ድል ከሆነ ደግሞ ለሶስተኛ ተከታታይ ጨዋታ ሶስት ነጥብን በማሳካት የታህሳስ ወር መልካም አቋሙን ማስቀጠል የሚችልበት አጋጣሚ ይፈጠራል።

በቅዱስ ጊዮርጊስ በኩል ሳላዲን ሰይድ ፣ ናትናኤል ዘለቀ እና ታደለ መንገሻ የረጅም ጊዜ ጉዳት አሁንም የቀጠለ ሲሆን በኢትዮጽያ ቡናው ጨዋታ ጉዳት የገጠመው አሜ መሀመድም ወደ ጨዋታ ይመለሳል ተብሎ አይጠበቅም። በተመሳሳይ ለረጅም ጊዜ በጉዳት ከመከላከያ ስብስብ ውጪ የሆነው አዲሱ ተስፋዬ አሁንም ያልተመለሰ ሲሆን ሳሙኤል ታዬ በጉዳት እንዲሁም ሳሙኤል ሳሊሶ በቅጣት የቅዱስ ጊዮርጊሱ ጨዋታ ያልፋቸዋል። ከዚህ ውጪ ግዙፉ ተከላካይ ቴዎድሮስ በቀለ ከጉዳት ቢመለስም በስፖርታዊ ጨዋነት መጓደል ምክንያት በክለቡ የውስጥ ደንብ መሰረት ለቅጣት መዳረጉን ሰምተናል።

የቅዱስ ጊዮርጊስ አጨዋወት የለውጥ ሂደት አሁንም ብዙ ርቀት እንደሚቀረው ሳምንት ዓዲግራት ላይ የተካሄደው ጨዋታ አመላክቷል። ቡድኑ በጨዋታው በዋነኝነት ከተከላካይ መስመር ተሰላፊዎቹ በተደጋጋሚ ሲላኩ በሚታዩ ረጃጅም ኳሶች እና ከመስመር ተሻጋሪ ኳሶች መነሻነት ዕድሎችን ሲፈጥር ተስተውሏል። ይህ በቀድሞው የቡድኑ አጨዋወት ዙሪያ የተቃኘ የሚመስል አቀራረብ ምን አልባት ጨዋታው ከሜዳ ውጪ የተደረገ በመሆኑ ጥቅም ላይ እንደዋለ ማሰብ ቢቻለም ፖርቹጋላዊው አሰልጣኝ ቫስ ፒኒቶ ሊገነቡት ከሚያስቡት ቡድን አቀራረብ ጋር ተቃርኖው የጎላ ነው። በዛሬው የመከላከያ ጨዋታ ከሳምንቱ በተሻለ የኳስ ቁጥጥርን መሰረት አድርገው ወደ መጫወቱ እንደሚያደሉ የሚጠበቁት ጊዮርጊሶች ኢብራሂማ ፎፋናን በፊት መስመር አጥቂነት ሲጠቀሙ ቢታይም ከአማካይ ክፍሉ የሚነሱ ቅብብሎችን ወደ ኃላ ተስቦ በመቀበልም ሆነ በእንቅስቃሴ ለመስመር አጥቂዎቹ ክፍተትን በመስጠቱ በኩል ተጨዋቹ በዚህ ቦታ ላይ እያሳየ ያለው አቋም ጥያቄ የሚያስነሳ ነው። አቅሌሲያስ ግርማን በሁለተኛ አጥቂነት መጠቀም ከጀመሩ በኃላ የፊት መስመራቸው አስፈሪነት የተሻሻለው መከላከያዎች በምንይሉ ወንድሙ ግቦች ላይ ብቻ መመርኮዛቸው ትልቁ ደካማ ጎናቸው ነው ማለት ይቻላል። ክፍተት የነበረበት የቡድኑ የአማካይ መስመር አቅሌሲያስ ወደ መስመሮች እየወጣ በሚያደርገው እንቅስቃሴ መሻሻልን እያሳየ ሲመጣ በቀኝ መስመር አማካይነት ቦታ ላይም የአቤል ከበደ ጎልቶ መውጣት ለቡድኑ የማጥቃት ዑደት ተጨማሪ ሀይል ሆኖ ታይቷል። በዛሬው ጨዋታም አጥብበው በመጫወት የሚታወቁት የመከላከያ የመስመር አማካዮች  ከምንተስኖት አዳነ እና አብዱልከሪም ኒኪማ ጋር የሚገናኙባቸው አጋጣሚዎች እንዲሁም የቅዱስ ጊዮጊስ የመስመር አጥቂዎች ከመከላከያ የመስመር ተከላካዮች ጋር የሚያደርጉት ፍልሚያ የሚጠበቅ ይሆናል። በመከላከያ በኩል መሀል ለመሀል የቡድኑን የመከላከል እና የማጥቃት ሚዛን በመጠበቁ በኩል እየተሳካላቸው ያሉት በሀይሉ ግርማ እና ቴዎድሮስ ታፈሰም እስከ ሙሉአለም መስፍን ድረስ በሚኖረው የአማካይ መስመር ቦታ ላይ የሚኖራቸው ሚና በቅዱስ ጊዮርጊስ የአማካይ መስመር እንደሚፈተን ይጠበቃል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *