​አርባምንጭ ከተማ እዮብ ማለን በአሰልጣኝነት ሾመ

አርባምንጭ ከተማ ለ8 ሳምንታት ክለቡን የመሩት አሰልጣኝ ፀጋዬ ኪዳነማርያምን ከአሰልጣኝነት ካሰናበተ በኃላ ወልዲያን በገጠመበት የ9ኛ ሳምንት ጨዋታ በምክትል አሰልጣኙ በረከት ደሙ እየተመራ ወደ ሜዳ መግባቱ ይታወሳል፡፡  ትላንት ምሽት የክለቡ ቦርድ ባደረገው ረጅም ሰአት የፈጀ ውይይት ከቀረቡት ሰባት አሰልጣኞች መካከል የሀዲያ ሆሳዕና አሰልጣኝ እዮብ ማለን በዋና አሰልጣኝነት ሾሟል ፡፡ 

አርባምንጭ ከተማ ከዋና አሰልጣኙ ሹመት በተጨማሪነትም በርካታ ለውጦችን አድርጓል። ምክትል አሰልጣኙ በረከት ደሙን አሰናብቶ በምትኩ የብሔራዊ ሊጉ ክለብ  ጋሞ ጨንቻ ዋና አሰልጣኝ ማቲዮስ ለማን ሲቀጥር ክለቡ በሜዳው ደደቢትን በሚገጥምበት ጨዋታ አምበሉ አማኑኤል ጎበና እና ግብ ጠባቂው አንተነህ መሳ ቡድኑን ይመራሉ።

ክለቡን በስራ አሰኪያጅነት ሲመሩ የነበሩት አቶ ፀጋዬ ጌሌን አሰናብቶ ታዲዮስ ጨመሳን በስራ አስኪያጅ ሲሾም የቡድን መሪ የነበሩት አቶ መርከብ መለቆን ከቦታው አንስቶ አቶ ዋለልኝ ዮሀንስ በምትኩ መድቧል፡፡ የቴክኒክ ኮሚቴወረ አባላትን በሙሉ አንስቶ በቀድሞ ተጫዋቾች እና የዩኒቨርስቲ ምሁራን እንዲዋቀር አድርጓል፡፡

በዋና አሰልጣኝነት ክለቡን እንዲመሩ የተሾሙት አሰልጣኝ እዮብ ማለ ከሹመቱ በኃላ ከሶከር ኢትዮጵያ ጋር ባደረጉት አጭር ቆይታ በሹመቱ መሆናቸው እና በቀጣይም ክለቡን ካለበት ወደ ተሻለ ደረጃ ለማድረስ እንደሚሰሩ ገልፀዋል። ” በመጀመሪያ በክለቡ በመቀጠሬ ደስተኛ ነኝ። ከአሁን በኋላ በክለቡ ያሉ ክፍተቶችን ለመድፈንና በቀጣይ ካለበት ደረጃ ወደ ቀደመው ስሙ እንዲመለስ የተቻለኝን ከማድረግ ወደ ኋላ አልልም። ለዚህ የሁሉም እገዛ ግን ያስፈልገኛል፡፡ ” ብለዋል።

የቀድሞው የአርባምንጭ ከተማ ኮከብ ሀዲያ ሆሳዕናን በ8ኛ ሳሞንት ጨዋታ ለመጨረሻ ጊዜ ቡድኑን የሚመሩ ሲሆን ክለቡ (ሀዲያ ሆሳዕና) ለሰጣቸው እድልም አመስግነዋል። ” በተገፋሁበት ወቅት የሰበሰበኝ ሀዲያ ሆሳዕና ነው። እኔ የማስበው ስለ ነገ የሻሸመኔ ጨዋታ ነው። ብዙ ውለታ ከሀዲያ ሆሳዕና ጋር አለብኝ መለያየት ካለብኝ በህጋዊ መንገድ ነው። አርባምንጭን ወደ ፕሪምየር ሊግ ያስገባሁት እኔ ነኝ። ቢሆንም ማንም ባልረዳኝ ሰአት አምኖ የቀጠረኝን ሆሳዕናን ማመስገን እፈልጋለሁ። ህጋዊነቱን ጠብቆ በቀጣይ መከናወን ያለበት መሆን አለበት። እዚህ ውል አለብኝ ፤ በስምምነት እንጂ ዝም ብዬ ጥዬ ግን አልሄድም።” ብለዋል።

በሊጉ ግርጌ የሚገኘው አርባምንጭ ከተማን ለማሰልጠን በእጩነት ተይዘው ከነበሩት መካከል ከፍተኛ ግምት አግኝተው የነበሩት አሰልጣኝ መሳይ ተፈሪን ጨምሮ ዘላለም ሽፈራው፣ ጌትነት ቡታቆ እና ማትዮስ ለማ ይጠቀሳሉ፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *