​ኢትዮጵያ ቡና እና ወላይታ ድቻ አቻ ተለያይተዋል

የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 10ኛ ሳምንት መርሀ ግብሮች አካል የነበረው የዕለቱ የመጨረሻ ጨዋታ ኢትዮጵያ ቡናን እና ወላይታ ድቻን አገናኝቶ 1-1 በሆነ ውጤት ተጠናቋል።

ባለሜዳው ኢትዮጵያ ቡና ሳምንት በደደቢት ከተሸነፈበት ጨዋታ አማካይ ክፍሉ ላይ አክሊሉ ዋለልኝን በመስዑድ መሀመድ የተካ ሲሆን አማኑኤል ዮሀንስም የሚና ለውጥ በማድረግ በተከላካይ አማካይ ቦታ ላይ የተሰለፈ አምስተኛው የቡድኑ ተጨዋች ሆኗል። ወላይታ ድቻዎች በበኩላቸው በሳምንቱ መግቢያ ላይ ኢትዮ ኤሌክትሪክን ባሸነፈው ቡድናቸው ውስጥ ዳግም በቀለን በጨዋታው የቀይ ካርድ ተመልክቶ ቅጣት ላይ በሚገኘውን ተስፉ ኤልያስን ፋንታ ተጠቅመዋል። ከአሰልጣኝ መሳይ ስንብት በኃላም ቡድኑ በአራት የኃላ መስመር ተሰላፊዎች መጠቀሙን የቀጠለ ሲሆን ቅርፁም ወደ 4-1-4-1 የተጠጋ ነበር። ቡድኑ ጨዋታው በጀመረባቸው ደቂቃዎች ላይ ከበድ ያለ ጉዳት የገጠመውን አመርላ ደልታታን በዘላለም እያሱ ለመቀየር ተገዷል።

በኢትዮጵያ ቡና ወደ ግራ መስመር ያደላ የማጥቃት ሂደት የጀመረው የመጀመሪያው አጋማሽ የጨዋታ እንቅስቃሴ ለዕይታ ማራኪ ያልነበረ እና ሙከራዎች በርክተው ያልታዩበት ነበር። በተለይም የመጀመሪያዎቹ ሰላሳ ደቂቃዎች ቡድኖቹ በተቃራኒ ቡድን የግብ ክልል ውስጥ ለመግባት በእጅጉ ተቸግረው የታዩበት ነበር። አብዛኛውን የኳስ ቁጥጥር ይዘው በቆዩት ኢትዮጵያ ቡናዎች በኩል አራቱ የኃላ መስመር ተከላካዮች እና የተከላካይ አማካዩ አማኑኤል ዮሀንስ እንቅስቃሴ ከሌላው የቡድኑ ክፍሎች ተነጥሎ ይታይ ነበር። ይህም ወላይታ ድቻዎች ፊት ላይ በሚፈጥሩት ጫና የቡድኑን የኳስ ምስርታ ማዘግየት በሚችሉባቸው አጋጣሚዎች ተከትሎ የሚመጣ ነበር። ከዚህ ውጪ የድቻዎቹ ኃይማኖት ወርቁ እና በዛብህ መለዮ ለኤልያስ ማሞ እና ለመስዑድ መሀመድ የተጠጋ ቦታ አያያዝ ቡድኑ በቀላሉ መሀል ለመሀል እንዳይሰበር ምክንያት ነበር። የኢትዮጵያ ቡና የመስመር አጥቂዎችም በድቻ መስመር ተከላካዮች እይታ ውስጥ ሆነው ነበር አብዛኛውን ሰዐታቸውን ያጠፋት። ሌላው የጦና ንቦቹ አማካይ አብዱልሰመድ ዓሊም ከአማኑኤል የሚነሱ ኳሶች ወደ ሌሎቹ የቡና ተጨዋቾች እንዳይደርሱ ያደርግበት የነበረው መንገድ የቡድኑ የመከላከል አጨዋወት ሌላኛው ጥንካሬ ነበር። ይህን ይመስል በነበረው የድቻ የአማካይ መስመር አቀራረብ ምክንያት ክፍተት ያጡት ቡናዎች የተሻለ ወደሳጥን የቀረቡባቸው አጋጣሚዎች ላይ ድቻዎች የፊት መስመራቸውን ግፊት ተከትለው በመሀላቸው በተለይም በአማካይ እና በተከላካይ መሮቻቸው መሀከል የሚተውቱን ክፍተት በሚያሰፉባቸው አጋጣሚዎች መስዑድ እና ኤልያስ ነፃ ሆነው ሲታዩ ነበር። በዚህ ረገድ 33ኛው ደቂቃ ላይ ሳሙኤል ሳኑሚ ፣  40ኛው ደቂቃ ላይ ኤልያስ ማሞ እንዲሁም አማኑኤል ዮሀንስ በጭማሪ ደቂቃ ያደረጓቸውን ሙከራዎች ማንሳት ይቻላል። ከዚህ ውጪ የነበሩት የወንደሰን ገረመው የግብ ጠባቂነት ብቃት የታየባቸው እና ቡድኑ ለጎል ይበልጥ የቀረበባቸው የ22ኛ ደቂቃ የወንድይፍራው ጌታሁን እና የ33ኛ ደቂቃ የትዕግስቱ አበራ በግንባር የተገጩ ሙከራዎች ከተሻጋሪ ኳሶች የተገኙ ነበሩ። ኳስ በሚነጥቁባቸው አጋጣሚዎች በጃኮ አራፋት መሪነት ወደ መሀል ሜዳ ከተጠጋው የተጋጣሚያቸው የተከላካይ መስመር ጀርባ ለመግባት ጥረት ሲያደርጉ የታዩት ድቻዎችም በማጥቃት ሽግግር ወቅት በሁለተኛው የሜዳ ክፍል ላይ ከሚያስገቡት የተጨዋቾች ቁጥር አናሳነት የተነሳ አስፈሪ የጎል ዕድል መፍጠር አልቻሉም። 

ሁለተኛው አጋማሽ በጀመረባቸው ደቂቃዎች ኢትዮጵያ ቡናዎች ጫናቸው በጣም በርትቶ በማጥቃት ወረዳ ውስጥ ደጋግመው ሲገቡ ይታዩ ነበር። 49ኛው ደቂቃ ላይ ኤልያስ ማሞ ከቀኝ መስመር ይዞ የገባውን ኳስ ሳኑሚ ሞክሮ የግቡ አግዳሚ ሲመልስበት አስራት ቱንጆ ከሳጥን ውጪ  በቀጥታ ሲሞክር ወንደሰን ያዳነበት ሙከራዎችም የዚህ ጫና ውጤቶች ነበሩ። በኒዚህ ጊዜያት ይበልጥ አፈግፍገው የታዩት ድቻዎች በመከላከሉ ረገድ የነበራቸው ትኩረት ዝቅ ባለበት አጋጣሚ 62ኛው ደቂቃ ላይ ግብ አስተናግደዋል። ኤልያስ ማሞ እና አማኑኤል ዮሀንስ ቦታ በተቀያየሩበት ቅፅበት ከድቻዎች የሰው በሰው ማርኩንግ ነፃ ሆነው የተቀባበሉት ኳስ ሳጥን ውስጥ ለሳኑሚ ደርሶት ሳኑሚ ጠንካራ ሙከራ ባያደርግም ኳሷ በመሀል ተከላካዩ ተክሉ ታፈሰ ተጨርፋ ከመረብ አርፋለች። ከግቡ መቆጠር በኃላ የማጥቃት እና ገፍቶ የመጫወት ፍላጎት ያሳዩት ድቻዎች በቡና ሜዳ ላይ የሚያሳለፉት ሰዐት ሲጨምር ታይቷል። በዚህም ከካገኟቸው የቆሙ ኳሶች መሀከል የበዛብህ መለዮ የቀኝ መስመር ቅጣት ምት ኢላማዋን የጠበቀች ሙከራ ነበረች። በተቃራኒው የቡድኑ ደፈር ብሎ ማጥቃቱ 65ኛው ደቂቃ ላይ በመስዑድ መሀመድ እንደተከፈተባቸው አይነት መልሶ ማጥቃቶች ሲያጋልጣቸው ታይቷል። ይህን አጋጣሚ ወደ መጨረሻ ዕድል ከተቀየረ በኃላ መስዑድ ራሱ ከቅርብ ርቀት በመቀስ ምት ሞክሮ ማስቆጠር ሳይችል ቀርቷል። መሰል ጥቃቶች ቢደጋገሙባቸውም ወደፊት መሄዳቸውን የቀጠሉት ድቻዎች 74ኛው ደቂቃ ላይ ዳግም በቀለ በግራ መስመር ሰብሮ የገባውን ኳስ በግሩም አጨራረስ አስቆጥሮ አቻ አድርጓቸውል። በቀሩት ደቂቃዎችም ከመጀመሪያው በተለየ ክፍተቶችን ሲፈልጉ ቢታዩም ሰዐት በገፋ ቁጥር ግን  ድቻዎች ወደ ቀደመው ጥንቃቄን ወደሚያስቀድመው አጨዋወታቸው ማመዘናቸው አልቀረም። ይህም ቡናዎች ከሚፈጥሩት ጫና 80ኛው ደቂቃ ላይ ከታየው የኤልያስ ማሞ ቅጣት ምት ውጪ ሌላ ዕድል እንዳያገኙ በማድረግ ውጤት አስጠብቀው እንዲወጡ አድርጓቸዋል። ያፈገፈጉ ቡድኖችን የማስከፈት እና የሚፈጠሩ ዕድሎችን የመጠቀም ችግሩ የቀጠለው ኢትዮጵያ ቡና ውጤቱን ተከትሎ ወደ ስምንተኛ ደረጃ ሲወርድ ወሳኝ አንድ ነጥብ ማሳካት የቻሉት ወላይታ ድቻዎች ከወራጅ ቀጠናው በመውጣት ወደ 13ኛ ደረጃ መጥተዋል።

የአሰልጣኞች አስተያየት

ዲዲዬ ጎሜስ – ኢትዮጽያ ቡና

” በመጀመሪያ ለኢትዮጵያ ህዝብ እና ለደጋፊዎቻችን መልካም ገና ማለት ፈልጋለው። በጨዋታው አዝነናል። ጨዋታን መቆጣጠር ብቻውን ለድል አያበቃም። ተጋጣሚያችን አንድ የግብ ዕድል ብቻ ፈጥሯል እኛ ደግሞ ብዙ የማስቆጠሪያ አጋጣምዎችን ፈጥረን ነበር። ሆኖም ሳምንት እንደነበረው የደደቢት ጨዋታ አሁንም አንድ ግብ ብቻ ነው ማስቆጠር የቻልነው። ያ ደግሞ ለማሸነፍ በቂ አልነበረም። ኳስ ይዞ በመጫወት ለቡና አጨዋወት ይበልጥ እየቀረብን ይመስለኛል። ነገር ግን ግብ የማስቆጠር ችግር አለብን። ይህን ለማሻሻል በየቀኑ ጠንክረን ልምምዳችንን እየሰራን ነው። በእግር ኳስ እንዲህ አይነት ችግር ያጋጥማል። 

ዘነበ ፍሰሀ – ወላይታ ድቻ

ጨዋታው በጣም ከባድ ነበር። ቡና ምን አይነት አጨዋወት ይዞ እንደሚመጣ ስለምናውቅ  ከሜዳ ውጪ እንደመጫወታችን እና ጫና ውስጥ እንደመሆናችን  መጠን ያንን ለመመከት ነበር የገባነው። አልፎ አልፎ መቆራረጥ ቢኖርም ተጨዋቾቼ የሰጠዋቸውን ታክቲክ በሚገባ ተግብረዋል። ግብ እንዳይቆጠርብን ነበር ዋናው አላማችን። ከተቆጠረብን በኃላ ግን ጎሏን ለማካካስ ተጭነን ተጫውተን አንድ ግብ አስቆጥረናል። ወደፊት ብዙ የሚቀረን ነገር አለ። እዛ ላይ ሰርተን ተዘጋጅተን እንመጣለን ብዬ አስባለው። ከሜዳ ውጪ እንደመጫወታችን ግን አንድ ነጥብ ለኛ በጣም ጥሩ ነው።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *