​ሪፖርት | አርባምንጭ ከአምስት ተከታታይ ሽንፈት በኋላ ወደ ድል ተመልሷል

በኢትዮዽያ ፕሪምየር ሊግ 12ኛ ሳምንት አርባምንጭ ላይ አዳማ ከተማን ያስተናገደው አርባምንጭ ከተማ ከተከታታይ አምስት ጨዋታዎች ሸንፈት በኋላ የመጀመርያ ሦስት ነጥቡን አሳክቷል።

በውድድር አመቱ ካደረጋቸው 11 ጨዋታዎች በሰባት ተሸንፎ  በሦስት ጨዋታ አቻ ወጥቶ አንድ ጨዋታ (መከላከያን) ብቻ በማሸነፍ 6 ነጥብ በመያዝ የደረጃ ሰንጠረዡ ግርጌ የሚገኘው አርባምንጭ ከተማ ከሰባተኛው ሳምንት ጀምሮ ያደረጋቸውን አምስት ተከታታይ ጨዋታዎችን በሙሉ በመሸነፍ በከፍተኛ የውጤት ቀውስ ውስጥ ሆኖ ነው ለዛሬው ጨዋታ መድረስ የቻለው። በአንፃሩ አዳማ ከተማ ከተከታታይ አራት ጨዋታዎች የአቻ ውጤት ጉዞ በኋላ ኢትዮ ኤሌክትሪክ እና ኢትዮዽያ ቡናን አሸንፎ ደረጃውን በማሻሻል በጥሩ መነቃቃት ላይ ሆኖ ነበር ወደ አርባምንጭ ያመራው።

አርባምንጭ ከተማ ባሳለፍነው ሳምንት ወደ ወላይታ ሶዶ አቅንቶ በወላይታ ድቻ 1-0 በተረታበት የቡድን ስብስብ ውስጥ በታገል አበበ አስጨናቂ ፀጋዬን እንዲሁም በአማካዩቹ ምንተስኖት አበራ እና ወንድሜነህ ዘሪሁን ምትክ አማኑኤል ጎበና እና ፀጋዬ አበራን እንዲሁም በአጥቂ ስፍራ ላይ በላኪ ሳኒ ምትክ ተመስገን ካስትሮን በማካተት ወደ ጨዋታው ሲገባ በአንፃሩ አዳማ ከተማ በሜዳው በ11ኛው ሳምንት ኢትዮዽያ ቡናን አስተናግዶ 2-1 ካሸነፈበት ስብስቡ በበረከት ደስታ ሲሳይ ቶሊን እንዲሁም በቡልቻ ሹራ ከነአን ማርክነህን በመተካት ወደ ሜዳ ገብተዋል።

ኢንተርናሽናል ዳኛ ቴዎድሮስ ምትኩ በዋና ዳኝነት በመሩት በዚህ ጨዋታ በመጀመርያ አጋማሽ  የጨዋታው ክፍለ ጊዜ ባለሜዳዎቹ አርባምንጮች ከተጋጣሚያቸው በተሻለ ወደ ጎል በመድረስም ሆነ የጎል ሙከራ በማድረግ ብልጫ ወስደው ነበር። በተለይ ከተከላካይነት ሚናው በተለየ ሁኔታ አሰልጣኝ እዮብ ማለ በአጥቂነት ሚና የተጠቀሙበት ተመስገን ካስትሮ በመጀመሮያዎቹ 15 ደቂቃዎች ምንም እንኳ ጠንካራ የጎል ሙከራ ማድረግ ባይችልም የአዳማ ተከላካዮችን በእንቅስቃሴው ሲረብሻቸው ተመልክተናል። አርባምንጭ ከተማ በፈጠረው ጫና 20ኛው ደቂቃ ላይ በአንድ ሁለት ቅብብል ወደ አዳማ የግብ ክልል የገባውን ኳስ ተመስገን ካስትሮ መሬት ለመሬት መትቶ ግብ ጠባቂው ጃኮ ፔንዜ ሲተፋው ከኳሱ በቅርብ ርቀት የነበረው ፀጋዬ አበራ አግኝቶ ወደ ግብነት በመቀየር አርባምንጭ ከተማን ቀዳሚ ማድረግ ቻለ።
በጎሉ የተነቃቁት አዞዎቹ ተጨማሪ ጎል ሊሆን የሚችል አጋጣሚ በ24ኛው ደቂቃ ላይ አለልኝ አዘነ አግኝቶ ሳይጠቀምበት ቀርቷል። ብዙም እንደቡድንም ተደራጅተው ፣ በተናጥል በግል የሚደረግ ጥረት ያልታየባቸው አዳማዎች ወደ ጨዋታው እንቅስቃሴ ለመግባት 30 ደቂቃ ፈጅቶባቸዋል። በአንድ ደቂቃ ልዩነት ከነአን ማርክነህ እና ዳዋ ሁቴሳ ያደረጉት ሙከራም የሚጠቀስ ነበር ። 37ኛው ደቂቃ ላይ አንዳርጋቸው ይላቅ ከቀኝ መስመር ያሻገረውን ቅጣት ምት ዳዋ ሁቴሳ በግንባሩ ገጭቶ ግብጠባቂው ፅዮን ያዳነበትም በመጀመርያው አጋማሽ በአዳማ በኩል የታየ አስደንጋጭ ሙከራ ነበር።

ከእረፍት መልስ የነበረው የጨዋታ ክፍለ ጊዜ በአሰልቺ ሁኔታ የተጠናቀቀ ሲሆን ኳሱ ከአንድ ሁለት ቅብብል በላይ መሻገር አቅቶት ይቆራረጥ የነበረበት ፣ የጨዋታው እንቅስቃሴም ቢሆን ብዙም ሳቢ ያልነበረ ፣ በተደጋጋሚ በሚሰሩ ጥፋቶች ምክንያት ሰአት አላግባብ ሲባክን የነበረበት የጨዋታ ገፅታ ነበር። አርባምንጮች ጨዋታውን አሸንፎ ለመውጣት ከነበራቸው ከፍተኛ ፍላጎት የተነሳ በሙሉ የመጫወት ፍላጎት ሁለተኛውን አጋማሽ በራሳቸው የሜዳ ክፍል አፈግፍገው ሲከላከሉ የዋሉ ከመሆናቸው ባሻገር በሚሰሩት ተደጋጋሚ ጥፋት እንዲሁም ሰአት ለማባከን በሚያደርጉት ጥፈት በኢ/ዳኛ ቴዎድሮስ ምትኩ አማካኝነት አምስት ተጨዋቾች ቢጫ ካርድ ሊመለከቱ ችለዋል።

አዳማዎች ከመጀመርያው አጋማሽ በተሻለ ሁኔታ ወደ ጨዋታው ለመመለስ የሚያስችላቸውን የታክቲክ ለውጥ በማድረግ የተከላካይ ቁጥራቸውን በመቀነስ አላዛር ፋሲካ እንዲሁም ታፈሰ ተስፋዬን ደግሞ ወደ መጨረሻ ደቂቃ ቀይረው ቢያስገቡም ጠንካራ የጎል ሙከራ ማድረግ ተስኗቸው በአርባምንጭ ከተማ 1-0 ተሸንፈው ወተዋል  ።
ውጤቱን ተከትሎ አርባምንጭ ከተማ በአሰልጣኝ እዮብ ማለ ቡድኑን እየተመራ ባደረገው የመጀመርያ ጨዋታ ሦስት ነጥብ ሲያሳካ በደረጃ ሰንጠረጁ የደረጃ ለውጥ ማድረግ በይችልም ነጥቡን ወደ ዘጠኝ ከፍ ማድረግ ችሏል ።

በቀጣይ 13ኛ ሳምንት አርባምንጭ ከሜዳው ውጭ ሀዋሳ ከተማን ሲገጥም አዳማ ከተማ በአንፃሩ በሜዳው ከወልዋሎ ጋር የሚጫወት ይሆናል ።

የአሰልጣኞች አስተያየት 

እዮብ ማለ – አርባምንጭ ከተማ 

” የምንፈልገው ሦስት ነጥብ ነበር። እሱን አሳክተናል። ተጫዋቾቼ የተሰጣቸውን በሙሉ ሜዳ ላይ ተግብረውልኛል። በውጤቱ በጣም ደስተኛ ነኝ። ተጫዋቾቹ ታዳጊ ናቸው ፤ በጣም አቅም አላቸው። ሆኖም በተደጋጋሚ ሽንፈት ምክንያት ስነ ልቦናቸው ተጎድቶ ስለነበር በዚህ ጨዋታ አሸንፎ ለመውጣት ከነበረን ፍላጎት የተነሳ በሁለተኛው አጋማሽ አፈግፍገን መጫወታችን ለዛ ነው። ከዚህም በኋላ በተቻለ መጠን ደጋፊዎቻችንን ለማስደሰት እንጥራለን ። ተመስገን ካስትሮ ከዚህም በኋላ በአጥቂ ተጫዋችነቱ ይቀጥላል ።

ተገኔ ነጋሽ – አዳማ ከተማ 

ይህ በኳስ አለም ያለ ነው ፤ ውጤቶች ይለዋወጣሉ። የተጫዋቾቼ በበቂ ሁኔታ አለመሟላት እና የአየሩ ሁኔታ ተፅእኖ አድርጎብን የመጀመርያው አጋማሽ ጥሩ አልነበርንም። ከእረፍት በኋላ ነገሮችን ለማስተካከል ለውጥ አድርገን ገብተን ነበር አልተሳካም። አርባምንጭ አሸንፎ በመውጣቱ እድለኛ ነበር ማለት ይቻላል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *