​ሪፖርት | ሲዳማ ቡና ደረጃውን ያሻሻለበትን ድል ፋሲል ላይ አስመዝግቧል

በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 12ኛ ሳምንት ጨዋታ ሲዳማ ቡና በሜዳው ፋሲል ከተማን አስተናግዶ በእንቅስቃሴ የበላይነት ጭምር 3-0 በሆነ ውጤት በማሸነፍ ደረጃውን ማሻሻል ችሏል።

ሲዳማ ቡና ድሬዳዋን ከገጠመበት ጨዋታ በተጎዳው ፈቱዲን አወል ምትክ ዮናታን ፍስሀን ፤ በፍፁም ተፈሪ ምትክ ወንድሜነህ አይናለምን በማካተት ወደ ሜዳ ሲገባ ፋሲል ከተማ ይስሀቅ መኩርያን በፍፁም ከበደ ፣ ፊሊፕ ዳውዝን በዳዊት እስጢፋኖስ ምትክ በመጀመርያ አሰላለፍ በማካተት እንዲሁም የመሐል አማካዩ ኄኖክ ገምተሳን በቀኝ መስመር ተከላካይነት በማሰለፍ ነበር ጨዋታው የተጀመረው።

እንደወትሮው ሁሉ በኢትዮጵያ ህዝብ መዝሙር ታጅቦ በፌድራል ዳኛ ተካልኝ ለማ መሪነት በተጀመረው ጨዋታ ሙሉ ክፍለ ጊዜ የባለሜዳዎቹ የማጥቃት ኃይልን የተመለከትንበት ፤ በተቃራኒው ደግሞ የፋሲል ከተማ ደካማ የመከላከል አደረጃጀት የተስተዋለበት ነበር።

በፈጣን የጨዋታ እንቅሰቃሴ ታጅቦ የተጀመረው ጨዋታ ገና በ6ኛው ደቂቃ ላይ ነበር ግብ ያስመለከተን። ባዬ ገዛኸኝ በግራ የፋሲል ከተማ የግብ ክልል ጠርዝ ላይ ሁለት ተጫዋቾችን አልፎ ለታናሽ ወንድሙ ሐብታሙ ገዛኸኝ የሰጠውን ኳስ ወጣቱ አጥቂ አሾልኮለት ወንድሜነህ አይናለም ከመረብ በማዋሀድ ሲዳማ ቡናን ቀዳሚ ማድረግ ችሏል።

በጎሉ ይበልጥ የተጠናቀቁት ሲዳማ ቡናዎች በሁለቱም መስመሮች ባዬ፣ ወንድሜነህ፣”አዲስ እና ሐብታሙን ተጠቅመው ፈጣን ጥቃት በመሰንዘር የፋሲል የተከላካይ ክፍልን ሲፈትኑ ውለዋል። በ18ኛው ደቂቃ ላይ አዲስ ግደይ እና ባዬ ገዛኸኝ በአንድ ሁለት ቅብብል ወደ ፋሲል የግብ ክልል ይዘውት የገቡትን ኳስ አዲስ ግደይ ወደ ግብነት በመቀየር የሲዳማን የግብ መጠን ወደ ሁለት ከፍ አድርጓል።

ፋሲል ከተማዎች በራምኬል ሎክ እና ፊሊፕ ዳውዝ አማካኝነት ለግብ ለመቅረብ ጥረት ቢያደርጉም የጠራ አጋጣሚን ግን መፍጠር አልቻሉም። በአንፃሩ በሲዳማ በኩል በ27ኛው ደቂቃ ላይ በግምት ከ25-27 ሜትር ርቀት ላይ በእለቱ ከርቀት በሚመታቸው ኳሶች የፋሲሉ ግብ ጠባቂ ሚኬል ሳማኬን ሲረብሽ የዋለው የቀድሞው የደቡብ ፖሊስ እና ሀዋሳ ከተማ አማካይ ወንድሜነህ አይናለም እጅግ ማራኪ ግብ አስቆጥሮ የሲዳማን መሪነት ወደ 3-0 ከፍ አድርጓል። ከጎሉ መቆጠር በኋላ ጨዋታው የጠራ የጎል ሙከራ ያልታየበት ሲሆን የመጀመሪያው የጨዋታ አጋማሽም በሲዳማ ቡና መሪነት ተጠናቋል።

በሁለተኛው አጋማሽ ፋሲል ከተማዎች መጠነኛ መሻሻልን ቢያሳዩም በዚህም አጋማሽ ሲዳማ ቡናዎች የተሻሉ ነበሩ። በ46ኛው ደቂቃ አፄዎቹ በኤርሚያስ ኃይሉ አማካኝነት ግብ ቢያስቆጥሩም ከጨዋታ ውጭ ተብላ ተሽራለች። በ59ኛው ደቂቃ ላይ ፋሲሎች ኤፍሬም አለሙ ከማዕዘን ምት ያሻማውን ኳስ ራምኬል ሎክ ሞክሮ ለጥቂት የወጣበትም ፋሲሎች ልዩነቱን ለማጥበብ ላደረጉት ጥረት የሚጠቀስ ነው።

ሲዳማዎች በዚህኛው አጋማሽም በርካታ ግብ ሊሆኑ የሚችሉ አጋጣሚዎችን የፈጠሩ ሲሆን በተለይ በ64ኛው ደቂቃ ግሩም አሰፋ ከግራ መስመር ሰብሮ በመግባት ለአዲስ ግደይ ያመቻቸለትና አዲስ ሙሉ ለሙሉ ሳይመታው ወደ ውጪ የወጣበት እንዲሁም ሐብታሙ ገዛኸኝ ወደ ግብ ክልል እየገፋ ገብቶ መትቶ ሚኬል ሳማኬ ያወጣበት የሚጠቀሱ ሙከራዎች ናቸው።

ጨዋታው ወደ መገባደጃው ሲቃረብ በሀለለቱም በኩል ጥሩ እድሎች ተፈጥረዋል። በ86ኛው ደቂቃ ራምኬል ሎክ ከመሀመድ ናስር ያገኛትን ግልፅ የማግባት እድል በግብ ጠባቂው መሳይ አያኖ ሲከሽፍበት በ90ኛው ደቂቃ ራምኬል ሎክ ከቀኝ የግብ አቅጣጫ የላካትን ኳስ መሐመድ ናስር በግንባሩ ገጭቶ የግቡ ቋሚ መልሶበታል። በሲዳማ በኩል ደግሞ በ87ኛው እና 88ኛው አዲስ ግደይ በተከታታይ ያገኛቸው እድሎችን ሳይጠቀምባቸው ቀርቷል።

ጨዋታው በሲዳማ ቡና 3-0 አሸናፊነት መጠናቀቁን ተከትሎ የይርጋለሙ ክለብ የፋሲልን 6ኛ ደረጃ ሲረከብ ፋሲል ወደ 7ኛ ዝቅ ብሏል።

የአሰልጣኞት አስተያየቶች

አለማየሁ አባይነህ – ሲዳማ ቡና 

በጨዋታው የተሻለ አቅም ይዘን ነው የገባነው። ተጭነን እንደመጫወታችን ማሸነፋችን ይገባናል። ፋሲል በቅዱስ ጊዮርጊስ ከመሸነፉ ውጭ ጠንካራ ቡድን ነበር። ከባድ ጨዋታ እንደሚጠብቀንም እናውቅ ነበር። ያን ስለማናውቅ ቶሎ ቶሎ ወደ ግብ በመድረስ ማስቆጠር ነበረብን ፤ ያን አድርገናል። ቢሆንም ግን ብዙ ኳሶችን አምክነናል። ወደ ማሸነፍ እየመጣን ነው ፤ ቡድኑን ተነሳሽነቱ ጥሩ ነው። በየጫወታው ያገኘነውን አጋጣሚ ብንጠቀም ከዚህም በላይ ቡድኔ ባስቆጠረ ነበር።

ምንተስኖት ጌጡ – ፋሲል ከተማ

እኛ ጥሩ አልነበርንም። እንደ እንቅስቃሴያቸው እነሱ ውጤቱ ይገባቸዋል። በርካታ ተጫዋቾች በመጎዳታቸው ያለቦታቸው ተጫዋቾችን ተጠቅሜያለሁ። የተከላካይ ክፍተት ነበረብን። በቀጣይ ግን ያሬድ እና አይናለም ስለሚመለሱ ጥሩ ቡድን ይዘን እንቀርባለን። የስኳዱ ጥበት ከዚህ አንፃር ጎድቶናል። ለዚህ ውጤታችን ዋነኛው ምክንያት የጨዋታ መደራረብ ነው። በየሁለት ቀኑ ነበር የተጫወትነው። ኳስ ስለሆነ ይህን መቀበል ግን ግድ ነው። ጫናዎች የሉብኝም በቀጣይ ግን ይስተካከላል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *