ሪፖርት| ወላይታ ድቻ የቅዱስ ጊዮርጊስን ያለመሸነፍ ጉዞ ገቷል

በ13ኛው ሳምንት የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ቅዱስ ጊዮርጊስን በሜዳው ያስተናገደው ወላይታ ድቻ በበዛብህ መለዮ ጎሎች ታግዞ 2-1 ማሸነፍ ችሏል። (ሁለተኛው ግብ በቅዱስ ጊዮርጊስ ተከላካይ ተጨርፎ የገባ ቢሆንም ዳኛው ጎሉን ቅጣት ምቱን በመታው በበዛብህ መለዮ ስም ነው የመዘገበው)

ወላይታ ድቻዎች ከወልዋሎ ዓ.ዩ አቻ በተለያዩበት ጨዋታ የተጠቀሙባቸውን ተጨዋቾች ሳይቀይሩ ለ4-1-4-1 በቀረበ አሰላለፍ ጨዋታውን ሲጀምሩ ቅዱስ ጊዮርጊስ በተለመደው የ4-3-3 ቅርፅ ፋሲል ከተማን መርታት ከቻለው ስብስቡ ከጉዳት የተመለሰው አበባው ቡታቆን በመሀሪ መና በመተካት ነበር ወደ ሜዳ የገባው።

ጨዋታው ከመጀመሩ አስቀድሞ የኢትዮጵያ ብሔራዊ መዝሙር መዘመሩ እና በወላይታ ደጋፊዎች ማህበር ለቅዱስ ጊዮርጊስ ስፖርት ክለብ የተሰራው ‘እግር ኳስ የሠላም እና የፍቅር ተምሳሌት ነው’ የሚለው መልእክት የተካተተበት የእንኳን ደህና መጣችሁ ባነርም በከፍተኛ ደጋፊዎች ለተጨናነቀው ስታድየም ግሩም እግርኳሳዊ መንፈስ ያላበሰ ነበር።

የመጀመሪያው አጋማሽ የጨዋታ ክፍለ ጊዜ ሁለት አይነት መልክ ነበረው። የመጀመሪያዎቹ ሀያ ደቂቃዎች ግቦች የተቆጠሩባቸው እና በሁለቱም ቡድኖች በኩል የግብ ዕድሎች የተፈጠሩባቸው ነበሩ። ቀሪዎቹ ሀያ አምስት ደቂቃዎች ደግሞ ቡድኖቹ በጥቂት አጋጣሚዎች ብቻ ወደ ተጋጣሚያቸው የግብ ክልል የቀረቡባቸው እንዲሁም ጥቂት ሙከራዎች የታዩባቸው ነበሩ። ፈጠን ያለ ፉክክርን በተመለከትንባቸው የመጀመሪያ ደቂቃዎች ኳስ መስርተው ለመጫወት ሙከራ ሲያደርጉ የነበሩት ቅዱስ ጊዮርጊሶች የመጀመሪያ ሙከራቸውን ወደ ግብነት መቀየር ችለዋል። ከአስቻለው ታመነ በቀጥታ ከተሻገረ ኳስ የድቻ ተከላካዮችን መዘናጋት ተከትሎ በኃይሉ አሰፋ በተክክለኛው ቦታ ላይ በመገኘት በፋሲል ከተማ ላይ ካስቆጠረው ጎል ጋር በሚመሳሰል ሁኔታ ኳስን ከመረብ ማገናኘት ችሏል።

ግብ ከተቆጠረባቸው በኃላ ተነቃቅተው የታዩት ድቻዎች ወደ ቀኝ መስመር ባደላ ማጥቃት ጊዮርጊሶችን የፈተኑ ሲሆን ዘጠነኛው ደቂቃ ላይ ጃኮ አራፋት ከሳጥን ውስጥ ሞክሯት ሮበርት በቀላሉ የያዘበት ኳስም በዚሁ መስመር የተፈጠረች ዕድል ነበረች። ቡድኑ በቀኝ ጎኑ በእሸቱ መና እና ዘላለም እያሱ ቅንጅት መጫኑን ቀጥሎ ጃኮ አራፋት ከዛው አቅጣጫ ወደ መሀል ያሳለፈውን ኳስ ሙላአለም መስፍን ሲጨርፈው አግኝቶ በዛብህ መለዮ ከሳጥኑ ጭልፍ ላይ በቀጥታ በመምታት ከመረብ ማገናኘት ችሏል። ይህች ጎል ከሰባት ጨዋታዎች በኃላ በሮበርት ኦድንካራ ላይ ለመጀመሪያ ጊዜ የተቆጠረች ነበረች።

ወደ ተጋጣሚያቸው የሜዳ ክልል ገፍተው በመጫወት ምላሽ ለመስጠት የሞከሩት ቅዱስ ጊዮርጊሶች የድቻ ተሰላፊዎችን ደካማ የመከላከል ሽግግር በመጠቀም 15ኛው እና 16ኛው ደቂቃ ላይ ጥሩ ዕድሎችን ፈጥረው ነበር። ከአጋጣሚዎቹ በመነሳትም በኃይሉ የሞከረውን ኳስ ወንደሰን ገረመው ሲይዝበት ሙሉአለም ከግቡ ጥቂት ሜትሮች ርቀት ላይ የተቆጣጠረውን ሌላኛውን ኳስ ተከላካዮች አውጥተውበታል። ከእነዚህ ሙከራዎች በኃላ የሁለቱም ቡድኖች የማጥቃት ስትራቴጂዎች ከሁለተኛው የሜዳ ክፍል ማለፍ አልቻለም። ጨዋታውም በተጨዋቾች የሜዳ ላይ ግጭቶች እና የኢንተርናሽናል ዳኛ ለሚ ንጉሴን ውሳኔዎች ተከትሎ በሚነሱ ንትርኮች የቀጠለ ነበር። ይህን ተከትሎም በተለይ ወላይታ ድቻዎች በርካታ የቆሙ ኳሶችን ቢያገኙም 36ኛው ደቂቃ ላይ እሸቱ መና ከቀኝ መስመር አሻምቶት ሙባረክ ሽኩር በግንባሩ ሞክሮ ወደ ውጪ ከወጣበት ኳስ ውጪ ሌላ ዕድል መፍጠር አልቻሉም። ከመሀል ሜዳው ገባ ያሉ ቦታዎች ላይ በተደጋጋሚ ያገኟቸውን የቅጣት ምቶች በአግባቡ ሳይጠቀሙባቸው ቀርተዋል። በተመሳሳይ መልኩ በቅዱስ ጊዮርጊስ በኩል 32ኛው ደቂቃ ላይ አበባው ቡታቆ ከቀኝ መስመር ረጅም ርቀት ላይ ከሞከረው ቅጣት ምት ውጪ ሌላ ጠንካራ ሙከራ ሳይታይ ነበር እረፍት የወጡት።

በሁለተኛው አጋማሽ የቡድኖቹ አጨዋወት ግልፅ ሆኖ የታየበት ነበር። ሆኖም የፉክክር መንፈሱ ወደ መጀመሪያዎቹ ደቂቃዎች መመለስ ሳይችል አሰልቺነቱ ተባብሶ ታይቷል። እዚህ ላይ ለጨዋታው ፍሰት አልባነት እና መቆራረጥ የሜዳው የወረደ ጥራት ተፅዕኖ እንደነበረው መናገር ይቻላል። የተሻለ ተጭነው ለመጫወት የሞከሩት ቅዱስ ጊዮርጊሶች የኳስ ቁጥጥር የበላይነቱን መውሰድ ቢችሉም ጠንካራውን የወላይታ ድቻ የመከላከል አደረጃጀት ማለፍ ተስኗቸዋል። የኳስ ቁጥጥራቸው ሶስተኛው የሜዳ ክፍል ላይ ሲደርስም ከመስመር በሚላኩ ረዣዥም ኳሶች ሲቋጭ ተስተውሏል። ከድቻዎች የመከላከል ቅርፅ በተጨማሪም በጊዮርጊሶች የኳስ ቁጥጥር ወቅት ኳስ በያዘው ተጨዋች አቅራቢያ የተወሰኑ ተቀባይ ተጨዋቾች ኖረው የተቀሩት በርቀት እጅግ ጠባብ በነበረው የድቻ የተከላካይ እና የአማካይ መስመር መሀል መገኘትም ለረዣዥሞቹ ኳሶች መፈጠር ምክንያት ነበር። ተሻጋሪ ኳሶቹም እንደወትሮው ስኬታማ ባለመሆናቸው ሳቢያ ለጎል የቀረቡ ሊባሉ የሚችሉት የቡድኑ ሙከራዎች በአበባው ቡታቆ፣ ሙሉአለም መስፍን እና ምንተስኖት አዳነ አማካይነት ሲደረጉ ከግቡ ርቀው በመሆኑ ኢላማቸውን ሳይጠብቁ ሲቀሩ እና በወንደሰን በቀላሉ ሲመለሱ ቆይተዋል።

የወላይታ ድቻዎች አቀራረብ ስኬትም የግብ ዕድሎችን ከመፍጠር አንፃር ሲመዘን እንደተጋጣሚያቸው ሁሉ ደካማ ነበር። ጥንቃቄ ካዘለው እና ኳስ ከተቀሙ በኃላ በፍጥነት የመከላከል ቅርፃቸውን በመያዝ ላይ ትኩረት ያደረገው አጨዋወታቸው ወደ ራሳቸው ግብ ክልል ያስጠጋቸው የነበረ በመሆኑ የመልሶ ማጥቃት ዕድሎችን ሲያገኙ ለጃኮ አራፋት በቀጥታ ከመጣል ባለፈ በቁጥር ተበራክተው የጊዮርጊሶች የግብ ክልል ድረስ ለመግባት የሚያስችል አልነበረም። በዚህም ምክንያት ከረፍት መልስ የመጀመሪያ ሙከራ ያደረጉት 74ኛው ደቂቃ ላይ ሲሆን ከማዕዘን ምት መነሻነት አብዱልሰመድ በግንባሩ ያልተጠቀመውን ኳስ በዛብህ በድጋሜ አሻምቶት ጃኮ የሞከረበት ነበር። 81ኛው ደቂቃ ላይም በዛብህ ከርቀት ኢላማውን ያልጠበቀ ጥሩ ሙከራ ማድረግ ችሎ ነበር። ከዚህ በኃላ መደበኛው የጨዋታ ክፍለ ጊዜ ሊገባደደ በተቃረበበት ደቂቃ በዛብህ መለዮ ከቀኝ መስመር በቀጥታ ወደ ጎል የላካት የቅጣት ምት በቅዱስ ጊዮርጊስ ተከላካይ በግንባር ተጨርፋ ለወላይታ ድቻ የማሸነፊያ ግብ ሆና ተቆጥራለች። ግቧም የተያዘችው በበዛብህ መለዮ ስም መሆኑን ከዕለቱ አልቢትሮች ማረጋገጥ ችለናል። ጨዋታው በጭማሪ ደቂቃዎች ሌላ የተለየ እንቅስቃሴ ሳይታይበት በጦና ንቦቹ አሸናፊነት ሲደመደም ስታድየሙ በደስታ ባህር ሰጥሟል።

ውጤቱን ተከትሎም አሸናፊው ወላይታ ድቻ ደረጃውን ማሻሻሉን ገፍቶበት ወደ ሰባተኝነት ከፍ ሲል ከሁለተኛ ደራጃው ያልተንሸራተተው ቅዱስ ጊዮርጊስ ከደደቢት ጋር ያለውን ልዩነት ማጥበብ ሳይችል ቀርቷል።

የአሰልጣኞች አስተያየት

አሰልጣኝ ዘነበ ፍሰሀ – ወላይታ ድቻ

የዛሬው ጨዋታ ትንሽ ውጥረት የነበረበት ነው። ውጥረት ስል ቅዱስ ጊዮርጊስ ጠንካራ እና አንጋፋ እንደመሆኑ መጠን በእያንዳንዱን እንቅስቃሴ በትኩረት እና በጥንቃቄ ለመጫወት ነው ጥረት ያደረግነው። የሰራነውም በዛ መልኩ ነው። ቅዱስ ጊዮርጊሶች የተጠና ጨዋታ ነው የሚጫወቱት። እኛም ኳስ ይዘን መጫወትን ትኩረት አልሰጠንም። ያለከኳስ የሚንቀሳቀሱ ብዙ አደገኛ ልጆች ስላሉ ተጠንቅቀን ነው የተጫወትነው። ተጨዋቾቼ እንደነገርኳቸው ቦታቸውን ይዘው በዙሪያቸው ያሉ ተጋጣሚዎቻቸው ላይ ትኩረት አድርገው ነው የተጫወቱት። አንዳንድ ጊዜ ቡድኑ ውስጥ መዘናጋት ይታያል። ወደፊት እሱን አሻሽለን ለመቅረብ ጥረት እናደርጋለን። ነገር ግን ተጨዋቾቼ ትልቅ መስዋትነት ነው የከፈሉት። አቅማቸውን አውጥተው ነው የተጫወቱት። ደጋፊውን እጅግ በጣም አመሰግናለው። ውጤቱንም ለደጋፊው ሰጥቻለው።

 ም/አሰልጣኝ ፋሲል ተካልኝ – ቅዱስ ጊዮርጊስ

ጥሩ ጨዋታ ነበር በመጨረሻ ሰዐት በገባብን ጎል ተሸንፈናል። በዘንድሮ አመት ስንሸነፍ የመጀመሪያችን ነው። ደስ ባይለንም ከስህተታችን የምንማርበት ይሆናል። ሁለተኛው ግብ ላይ ግልፅ የመከላከል ስህተት ሰርተናል። ያ ደግሞ ዋጋ አስከፍሎናል። ከኢንተርናሽናል ውድድር በፊት ከደደቢት ጋር ያለንን የነጥብ ልዩነት ለማጥበብ አስበን ነበር። ግን ይሄ በጣም የሚያስጨንቀን አይሆንም። ውድድሩ ገና ረዥም ነው። ከደደቢት ጋርም ጨዋታ አለን። አሸንፈን መጠጋት እንችላለን። አሁን ትኩረት አርገን የምንሰራው በዛሬው ጨዋታ ላይ ነው። ሜዳው ያሰብነውን ጨዋታ እንዳንጫወት አርጎናል ብዬ አስባለው። ተጋጣሚያችን በመጨረሻ ሰዐት ዕድለኛ ሆኗል እንኳን ደስ አላችሁ እላለው።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *